ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መከላከያ እና አዳማ ድል ሲቀናቸው ሀዋሳ እና ድሬዳዋ ነጥብ ተጋርቷል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዙር የ14ኛ ሳምንት ሦስት ጨዋታዎች በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ተካሂደው መከላከያ ቦሌን ፣ አዳማ አቃቂን በማሸነፍ ሦስት ነጥብ ሲያሳኩ ሀዋሳ እና ድሬዳዋ ያለ ጎል አጠናቀዋል፡፡

መከላከያ 2-0 ቦሌ ክፍለ ከተማ

የሁለተኛው ዙር የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በመከላከያ እና ቦሌ ክፍለ ከተማ ጨዋታ ተጀምሯል፡፡ በፈረንሳይ ሀገር የማውሪስ ሪቪሎ ከ21 ዓመት በታች የወንዶች ጨዋታን መርታ በያዝነው ሳምንት የተመለሰችው ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ እየመራችው ጅምሩን ያደረገው ይህ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ብዙም በጎል ሙከራ የታጀበ መሆን ባይችልም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ግን ሳቢ ሆኖ ተስተውሏል፡፡ በአሰልጣኝ ቻለው ለሜቻ የሚመራው ቦሌ ከግብ ክልላቸው በሚደረግ መነሻ የፊት አጥቂዋን ንግስት በቀለን የትኩረት ማዕከል በማድረግ ለመንቀሳቀስ ሲሞክሩ በአመዛኙ መከላከያዎች በመስመር አጨዋወት ሴናፍ እና ረሂማን ለመጠቀም ብርቱ ጥረት አድርገዋል፡፡

ጨዋታው 9ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ከእጅ ውርወራ መስከረም ካንኮ ለመሳይ ተመስገን ሰጥታት ተጫዋቿም ወደ ግብ ክልል ስትልከው አጥቂዋ ረሂማ ዘርጋው እና ግብ ጠባቂዋ ማህሌት ሽፈራው ለመሻማት ጥረት ሲያደርጉ ረሂማ ነካ በማድረግ ወደ ጎልነት ለውጣዋለች፡፡ ደብዘዝ ያለ ፉክክር በተስተዋለባቸው ቀሪዎቹ ደቂቃዎች ቦሌዎች በተሻለ መነቃቃት በተደጋጋሚ ወደ ግብ ቢደረሱም ስንታየው ሂርኮ እና ንግስት በቀለ በተደጋጋሚ በመከላከያ የተከላካይ ክፍል ተጠምደው ጎል ለማስቆጠር አልታደሉም፡፡ በአንፃሩ መከላከያዎች በረጃጅም ኳሶች መስመር ተኮር ጥቃት በመሰንዘር ጥረት ቢያደርጉም ተጨማሪ ግብ ሳንመለከት በዕንስቶቹ ጦረኞች 1-0 መሪነት ተገባዷል፡፡

ሁለተኛው አርባ አምስትን ከፍ ባለ ንቃት የጀመሩት ቦሌዎች ኳስን በመቆጣጠር በተጋጣሚያቸው ላይ ብልጫን በአጋማሹ ማሳየት ቢችሉም የጎል ክልል ሲደርሱ እጅጉን አፈፃፀማቸው ደካማ ነበር፡፡ በአንፃሩ ቀዳሚውን አጋማሽ በመሪነት ያገባደዱት መከላከያዎች የኋላ መስመራቸውን በተወሰነ መልኩ በማስጠበቅ በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ ለማከል ሞክረዋል፡፡ 52ኛው ደቂቃ ላይ ልማደኛዋ ንግስት በቀለ ከቀኝ አቅጣጫ ያገኘችውን ኳስ ወደ ጎል በሞከረችበት አጋጣሚ ቦሌዎች በሙከራ ቀዳሚ መሆን ችለዋል፡፡ የመሀል ክፍሉ ላይ ብልጫ እንደተወሰደባቸው የተረዱት መከላከያዎች ማዕድን ሳህሉን ቀይሮ በማስገባት በተወሰነ መልኩ ቅርፅ ለመያዝ ጥረቶች አድርገዋል፡፡

69ኛው ደቂቃ ላይ መከላከያዎች መሪነታቸውን ያሰፉበትን ጎል ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ የቦሌዋ ግብ ጠባቂ ማህሌት ሽፈራው ኳስ ለቡድን አጋሮቿ ለማቀበል ብላ ስትመታ በቅርብ ርቀት የነበረችሁ አማካይዋ ቤዛዊት ተስፋዬ ከመረብ አሳርፋው ቡድኗን ወደ 2-0 መሪነት አሸጋግራለች፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች ቦሌዎች በሜላት ጌታቸው ፣ ጤናዬ ለታሞ እና ንግስት በቀለ አማካኝነት በርካታ ያለቀላቸውን አጋጣሚዎች በሳጥን ውስጥ እየገቡ ጭምር ቢፈጥሩም ወደ ጎልነት መለወጥ ላይ በታየባቸው ድክመት 2-0 ተሸንፈው ወጥተዋል፡፡

አቃቂ ቃሊቲ 0-3 አዳማ ከተማ

8፡00 ሰዓት ላይ የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር በአቃቂ ቃሊቲ እና አዳማ ከተማ መካከል የተደረገ ነበር፡፡ አቃቂ ቃሊቲ አሰልጣኝ ዮናስ ወርቁን በማሰናበት በምክትል አሰልጣኙ ጥበቡ ወርቁ መሪነት ወደ ሜዳ የገባበት ይህ ጨዋታ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ተመጣጣኝ የሆነ ፉክክርን መመልከት የቻልንበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ በአመዛኙ መሀል ሜዳው ላይ ሁለቱ ቡድኖች ያደረጉት ፍትጊያ እጅጉን የላቀ ሆኖ ቢታይም ደካማ የነበረው የጎል ውሳኔዎቻቸው እንደ ነበራቸው ብርቱ ፉክክር ጎሎችን እንዳንመለከት አድርጎናል፡፡

ዓይናለም መኮንንን የትኩረት ማዕከል ባደረገ የግራ መስመር አጨዋወት ለመጫወት አቃቂዎች ጥረት ያደረጉ ሲሆን ተጫዋቿ ወደ ሳጥን ውስጥ ሦስት ጊዜ ገብታ ሳትጠቀምባቸው የቀረችባቸው ቅፅበቶች እጅጉን አስገራሚዎች ነበሩ፡፡ 35ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል ከሀና ቱርጋ ያገኘችውን ኳስ ወደ ሳጥን እየገፋች ገብታ ግልፅ የማስቆጠር ዕድልን መጠቀም ያልቻለችበት ሂደት ከተደረጉት ሙከራዎች ላቅ ያለውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በሄለን እሸቱ እና ምርቃት ፈለቀ የሚመራው የአዳማ የአጥቂ ክፍል የአቃቂ ቃሊቲ የግብ ክልል በመድረሱ ረገድ የሚታሙ ባይሆኑም ኳስን ከመረብ ማገናኘት ባለመቻላቸው አጋማሹ ያለ ጎል ተገባዷል፡፡

ተመሳሳይ የጨዋታ መንገድን ያየንበት ነገር ግን አዳማ ከተማዎች ስል በመሆኑ ከመጀመሪያው አጋማሽ ትምህርት ወስደው ብቅ ባሉበት ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በእንቅስቃሴ ተመሳሳይ ይዘትን ማስተዋል ብንችልም ደካማ የነበረው የአቃቂ የተከላካይ ክፍል የኋላ ኋላ ዋጋ የከፈለበት ሆኗል፡፡ 68ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ ከገባች ሁለት ያህል ደቂቃ ብቻ የሞላት ዮዲት መኮንን ግብ አስቆጥራ አዳማን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡ በሂደት ቶሎ ቶሎ በምርቃት ፈለቀ ፣ ሰርካዲስ ጉታ እና ሄለን እሸቱ አማካኝነት ጥቃት መሰንዘራቸውን አጠናክረው የቀጠሉት አዳማዎች ሰርካዲስ ጉታ ከምርቃት በደረሳት ኳስ 72ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ጎል በማከል የቡድኗን የግብ መጠን ከፍ አድርጋለች፡፡ ትዕግስት ሽኩር ካደረገችው ሙከራ በዘለለ ወደ አዳማ የግብ ክልል ለመድረስ የተፍረከረከው አቃቂ ልዩነቱን ሳያጠብ 78ኛ ደቂቃ ላይ ሄለን እሸቱ ሦስተኛ ጎል ከመረብ አሳርፋ ጨዋታው በአዳማ 3-0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ 0-0 ሀዋሳ ከተማ

ከአሰልጣኝ ብዙአየው ጀምበሩ ጋር የተለያየው ድሬዳዋ ከተማ በምክትል አሰልጣኙ እዮብ ተዋበ መሪነት ሀዋሳን ገጥሞ ያለ ጎል አጠናቋል፡፡ እጅግ ጠንካራ የማጥቃትም ሆነ የመከላከል አደረጃጀትን ማየት በቻልንበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አርባ አምስት እጅግ ለጎል የቀረቡ አጋጣሚዎችን የተመለከትንበት ፣ የድሬዳዋ አጥቂ ቤተልሄም ታምሩ ልዩነት ፈጣሪነትም የጎላበት ሆኗል፡፡ ሀዋሳዎች ገና 8ኛ ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ተከላካይ ብርቄ አማረ በሳጥን ውስጥ በእጅ ኳስ ነክታለች በማለት የዕለቱ ዳኛ ሲሳይ ራያ የሰጠችውን የፍፁም ቅጣት ምት ዙፋን ደፈርሻ ብትመታውም የግቡ ቋሚ ብረት መልሶባታል፡፡

በሂደት የድሬዳዋ አጥቂ ቤተልሄም ታምሩ ከቅጣት ምት አክርራ መትታ ግብ ጠባቂዋ ፍሬወይኒ ገብሩ በአስደናቂ መልኩ ያወጣችባት በድጋሚ ራሷ ፍሬወይኒ 30ኛ ደቂቃ ላይ የሀዋሳን የተከላካይ ክፍል ስህተት ተመልክታ ወደ ጎል መትታ ፍሬወይኒ በድጋሚ አውጥታባታለች፡፡ ሀዋሳዎች በበኩላቸው መንደሪን ክንዲሁን ከግራ አቅጣጫ ስታሻማ አምበሏ ቅድስት ዘለቀ በግንባር ገጭታ የግቡ አግዳሚ የመለሰባት ተጠቃሽ ሙከራ ነበር፡፡

ከዕረፍት መልስ ሀዋሳ ከተማዎች በርካታ የግብ አጋጣሚን ለመፍጠር ቢዳዱም ድሬዎች በግብ ጠባቂዋ አበባየው ጣሰው ጥንካሬ ታግዘው ግብ ሳያስተናግዱ ጨዋታውን 0-0 አጠናቀዋል፡፡