የ27ኛ ሳምንት የነገ ሦስት ጨዋታዎች የተቃኙበት ፅሁፋችን እንደሚከተለው ተሰናድቷል።
ወላይታ ድቻ ከ መከላከያ
የዕለቱን መርሐ-ግብሮች የሚያስከፍተው የወላይታ ድቻ እና መከላከያ ጨዋታ ሁለት ተመሳሳይ የአጨዋወት መንገድ የሚከተሉ ቡድኖች የሚያደርጉት ፍልሚያ ነው። ካለፉት 10 ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 30 ነጥቦች 6ቱን ብቻ ያሳካው ወላይታ ድቻ ከድል ጋር ለመታረቅ ጨዋታውን ሲፈልገው ከሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል በኋላ ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች ያላሸነፈው መከላከያም ዳግም የአሸናፊነትን መንገድ ለማግኘት እንደሚጥር ይታመናል።
ሊጉ አዳማ ላይ ሲከናወን የመጀመሪያውን ጨዋታ ብቻ አሸንፈው ተከታታይ መረታት እና አቻ መውጣት የያዙት ድቻዎች ከውጤት ባለፈም በእንቅስቃሴ ደረጃ የወረደ ብቃት ላይ ይመስላሉ። ለወትሮ በጥብቅ መከላከል በመንቀሳቀስ በረጃጅም እና የመልሶ ማጥቃቶች ለመጫወት የሚጥረው ቡድኑም በጠቀስናቸው 10 ጨዋታዎች ጠንካራ ጎኑ በመጠኑ ቀድቶት ታይቷል። እርግጥ ግቦችን በማስተናገድ ረገድ ያን ያህል እየተቸገረ ባይሆንም በላይኛው ሳጥን ግን ስልነቱ ቀንሷል። ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት በጉዳት አቷቸው የነበሩትን አጥቂዎች ቢያገኝም አዲስ አበባ ላይ ከአንድ የበለጠ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ አልቻለም ነበር። ተጋጣሚያቸው ለጥንቃቄ ቅድሚያ ሰጥቶ የነበረ በመሆኑ ከሌላ ጊዜው የተሻለ አንፃራዊ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢኖራቸውም ኳሱን ወደ ግብነት ለመቀየር አልታደሉም። ይህ የማጥቃት አጨዋወት ነገ ተሻሽሎ መቅረብ ካልቻለ ግን መከላከልን እንደ ስማቸው ጠንቅቀው በሚያቁት ተጫዋቾች ሊፈተን ይችላል።
ዋና አሠልጣኙ ዮሐንስ ሳህሌን ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ሜዳ ያገኘው መከላከያ በጨዋታው የተሻለ ብልጫ ወስዶ ለመንቀሳቀስ ቢሞክርም ግብ ፊት የነበረው የጨራሽነት ችግር አገርሽቶበት ሦስት ነጥብ ሳያሳካ ወጥቷል። እስካሁን በሊጉ መክረሙን በአስተማማኝ ሁኔታ ያላረጋገጠው ቡድኑ ያለ ዋና አሠልጣኙ ሜዳ ላይ የሚታይ መሻሻል አምጥቶ ቀና ለማለት እየሞከረ ቢመስልም ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች ከ2 የዘለለ ነጥብ ማሳካት አልቻለም። ከሦስቱ ጨዋታዎች በወልቂጤው ፍልሚያ የተሻለ ዕድሎችን የፈጠረው ቡድኑም ከላይ በገለፅነው መልኩ አለመጠቀሙ ትልቁ ድክመቱ ነበር። የነገው ተጋጣሚ ድቻ ደግሞ ሦስተኛው የሊጉ ትንሽ ጎል ያስተናገደ ቡድን ስለሆነ እንደ ወልቂጤው ጨዋታ ጎል ፊት መድረስ ቀላል ላይሆንለት ይችላል። ስለዚህ ዕድሎችን ዐይንን ሳያሹ መጠቀም ግድ ይላል። በመከላከሉ ረገድ ደግሞ ድቻ ብዙ ጊዜ የሚጠቀመውን ተሻጋሪ ኳሶች እና የመልሶ ማጥቃቶች ለመመከት የሚያስችል ቁመና ላይ መገኘት የግድ ይላል።
ባሳለፍነው ሳምንት አንተነህ ጉግሳን በቅጣት ምክንያት አጥቶ የነበረው ወላይታ ድቻ በዚህ ሳምንት የተከላካዩን ግልጋሎት ያገኛል። መከላከያ ግን አሁንም ከጉዳቱ ያልተመለሰው ብሩክ ሰሙ እና ቅጣት ላይ የሚገኘው ኢማኑኤል ላርዬን የማያሰልፍ ይሆናል።
የጨዋታው ዳኞች – ሀብታሙ መንግስቴ፣ ተመስገን ሳሙኤል፣ አበራ አብርደው፣ ተፈሪ አለባቸው
ተጨማሪ ዳኞች – ሀብተወልድ ካሣ እና ትንሳኤ ፈለቀ
እርስ በርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች 13 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 6 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መከላከያ 3 ጊዜ አሸንፏል። በቀሪዎቹ 4 ግንኙነቶች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። የጦና ንቦች 15 ፣ ጦሩ 12 ግቦችን በእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ማስቆጠር ችለዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወላይታ ድቻ (4-3-3)
ቢኒያም ገነቱ
በረከት ወልደዮሐንስ – አንተነህ ጉግሳ – ደጉ ደበበ – አናጋው ባደግ
ሀብታሙ ንጉሴ – ንጋቱ ገብረስላሴ – እንድሪስ ሰዒድ
ምንይሉ ወንድሙ – ስንታየሁ መንግስቱ – ቃልኪዳን ዘላለም
መከላከያ (4-2-3-1)
ክሌመንት ቦዬ
ገናናው ረጋሳ – አሌክስ ተሰማ – አሚን ነስሩ – ዳዊት ማሞ
ግሩም ሀጎስ – ምንተስኖት አዳነ
ተሾመ በላቸው – አዲሱ አቱላ – ቢኒያም በላይ
እስራኤል እሸቱ
ድሬዳዋ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ
በወራጅ ቀጠናው ትልቅ ትርጉም ከሚሰጡ እና ከወገብ በታች የሚገኙ ክለቦች በትኩረት ከሚመለከቱት ጨዋታዎች መካከል የነገ ምሳ ሰዓቱ ጨዋታ ተጠቃሽ ነው። ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ እና ደረጃ ብቻ ከፍ ብሎ የተቀመጠው ድሬዳዋ ከተማ ሦስት ነጥብ ካገኘ ሦስት ጨዋታዎች ስላለፉት የነገውን ፍልሚያ ረቶ ነጥቡን ወደ ሠላሳዎቹ ውስጥ ለመክተት እንደሚጥር ይጠበቃል። ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ያልተረታው እና ቀስ በቀስ ከታችኛው ቀጠና እየወጣ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ ነጥቡን አሳድጎ ወደ አስተማማኝ ደረጃ ለመጠጋት የነገው ጨዋታ ያስፈልገዋል።
ወጥ ያልሆነ ውጤት እና እንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ከፊቱ ያሉትን ጨዋታዎች ማሸነፍ የሌሎቹን ውጤት ሳይሰማ በሊጉ እንዲቆይ ያደርገዋል። ባለፉት ጨዋታዎች ቀጥተኛ ተገዳዳሪዎቹ የሆኑትን አዲስ አበባ እና መከላከያ መርታት ያልቻለው ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት ሀዋሳ ከተማ ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ድል ሲያገኝበት በእንቅስቃሴ ደረጃ አጀማመሩ መጥፎ አልነበረም። ነገርግን ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር የነበረውን አንፃራዊ ብልጫ በውጤት ማሳጀብ ተስኖት እጅ ሰጥቶ ከሜዳ ወጥቷል። በተለይ የወሰደውን የኳስ ቁጥጥር በዓላማ በማድረግ በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ መገኘት ሳይችል ቀርቷል። እርግጥ አሠልጣኝ ሳምሶን በጉዳት የሳሳው ስብስባቸው እንዳለ ሆኖ በተጠቀሙት የአደራደር እና የተጫዋች ባህሪ ቡድኑ ትንሽ ድፍረት አጥቶ ነበር። ከእረፍት መልስ የማጥቃት አጨዋወታቸውን ለማሻሻል ለውጦችን ቢያደርጉም በጨዋታው ለመመለስ ዘግይተው ነበር። ያሉበት ቦታ አስጊ ከመሆኑ አንፃር ግን ነገ ማጥቃት ላይ የተመረኮዘ አጨዋወት መከተላቸው የማይቀር ነው።
አካላዊ አጨዋወትን አዘውትሮ ሲከተል የሚታየው አርባምንጭ ከተማ ሲዳማን 2ለ1 ሲረታ መጠነኛ የአጨዋወት ለውጥ አድርጎ ታይቷል። ለወትሮ ኳስን ለማንሸራሸር ፍላጎት የማይታይባቸው ተጫዋቾቹ ወደ መጨረሻ የጨዋታው ውጤት ከእጃቸው እንዳይወጣ አፈገፈጉ እንጂ በግልፅ የጨዋታውን የሀይል ሚዛን በኳስ ቁጥጥር ውስጥ ለመያዝ ሞክረው ነበር። በዚህ የአጨዋወት ሂደት ደግሞ አማካዮቹ እንዳልካቸው መስፍን እና አቡበከር ሻሚል እንዲሁም አጥቂው ኤሪክ ካፓይቶ ምቾት ተሰምቷቸው ሲጫወቱና ተፅዕኖ ሲፈጥሩ ታይቷል። ይህ አጨዋወት አሠልጣኙ በድህረ-ጨዋታ አስተያየት እንዳሉት አድጎ የሚመጣ ከሆነ ደግሞ በአማካይ መስመር በቁጥር በዝተው ወደ ሜዳ ሊገቡ የሚችሉትን የድሬ ተጫዋቾች እጅ ሊያሰጥ ይችላል። ከምንም በላይ ግን ቡድኑ ወደ ቅይጥ አጨዋወት መምጣቱ በእንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዳይገመት ያደርገዋል።
ድሬዳዋ ከተማ ጉዳት ላይ የነበሩትን ፍሬው ጌታሁን፣ መሳይ ጻውሎስ እና ሙኸዲን ሙሳን በነገው ጨዋታ ሲያገኝ አርባምንጭ ከተማ ግን አሁንም የሳምሶን አሰፋን ግልጋሎት አያገኝም። በላይ ገዛኸኝ ግን ከጉዳቱ አገግሞ መመለሱ ተጠቁሟል።
የጨዋታው ዳኞች – ሔኖክ አክሊሉ፣ ትግል ግዛው፣ ሸዋንግዛው ከበደ፣ አባይነህ ሙላት
ተጨማሪ ዳኞች – ዘሪሁን ኪዳኔ እና ዳንኤል ጥበቡ
እርስ በርስ ግንኙነት
– ቡድኖቹ ዘጠኝ ጊዜ ተገናኝተው አርባምንጭ 3 ሲያሸንፍ ድሬዳዋ 2 አሸንፏል ፤ 4 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ አርባምንጭ 7 ፣ ድሬዳዋ ደግሞ 5 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)
ፍሬው ጌታሁን
እንየው ካሣሁን – አውዱ ናፊዩ – መሳይ ጳውሎስ – አብዱለጢፍ መሐመድ
ዳንኤል ደምሴ – ብሩክ ቃልቦሬ
አብዱርሀማን ሙባረክ – ሙኸዲን ሙሳ – ጋዲሳ መብራቴ
ሄኖክ አየለ
አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)
ይስሀቅ ተገኝ
ወርቅይታደስ አበበ – አሸናፊ ፊዳ – በርናንድ ኦቼንግ – መላኩ ኤሊያስ
ሙና በቀለ – አቡበከር ሸሚል – እንዳልካቸው መስፍን – ሱራፌል ዳንኤል
አህመድ ሁሴን – ኤሪክ ካፓይቶ
ሲዳማ ቡና ከ ጅማ አባ ጅፋር
በሊጉ የመጀመሪያ 19 ጨዋታዎች ካስመዘገበው ሽንፈት እጥፍ ባለፉት 7 ጨዋታዎች ብቻ ያስተናገደው ሲዳማ ቡና በሀዋሳ የተነጠቀውን የሦስተኛ ደረጃ ነግ ጅማን በመርታት ዳግም ለማግኘት እንደሚጥር ይታሰባል። በወራጅ ቀጠናው የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ ለከርሞ በሊጉ ለመቆየት ከፊቱ ከባድ ፈተና ቢጠብቀውም የሌሎቹን ውጤት እየጠበቀም ቢሆን የራሱን የቤት ስራ መስራትን እያሰበ ጨዋታውን ይከውናል።
ሲዳማ ቡና ዋና አሠልጣኙ ገብረመድህን ኃይሌን ካሰናበተ በኋላ በጊዜያዊ አሠልጣኙ ወንድማገኝ ተሾመ እየተመራ ሦስት ጨዋታዎችን ያከናወነ ሲሆን በመጨረሻው የአርባምንጭ ጨዋታ ተረቷል። በዕለቱ በብዙ መስፈትቶ ቡድኑ ብልጫ ተወስዶበት ሁለት ግቦችን ማስተናገዱ የሚታወስ ሲሆን በዋናነት ደግሞ ከወገብ በታች በተከላካይ መስመሩ ላይ የነበረው ክፍተት እንዲሸነፍ ያደረገው ዋነኛ ምክንያት ነበር። በተለይ የወሳኝ ተከላካዩ ጊት ጋትኩት በቅጣት ምክንያት አለመኖር በመስመሩ መረጋጋት እንዳይኖር ያደረገው ይመስላል። ነገም ተጫዋቹ አለመኖሩ ሲታወስ እና ሌላኛው ተከላካይ ያኩቡ መሐመድም በቅጣት እንደማይሰለፍ ታሳቢ ሲደረግ ስስ ጎኑ የበለጠ እንዳይጋለጥ አስግቷል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት የሚፎካከር አጥቂ ያለው ቡድኑ ከወገብ በታች አስተማማኝ ነገር ባይኖረውም በተቃራኒ ሳጥን ግን ያለው ግርማ ሞገስ ለጅማዎች ፈተና መሆኑ የማይቀር ነው።
ባሳለፍነው ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕናን አንድ ለምንም የረታው እና በሊጉ ለመትረፍ ትንሽ ከበድ ያለ ዕድል ያለው ጅማ የራሱን የቤት ሥራ አድምቶ ይሰራል ተብሎ በሚጠበቅበት ሰዓት ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ተጫዋቾቹ ትናንት እና ዛሬ ልምምድ አልሰሩም። እርግጥ ተጫዋቾቹ ጨዋታውን ሜዳ ገብተው እንደሚከውኑ ቢገለፅም ይህ የሜዳ ውጪ አስተዳደራዊ ክፍተት ወደ ኋላ የቀረውን ቡድን ይባስ እንዳይጎትተው ያሰጋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ቡድኑ ድል ባደረገበት ጨዋታ ግን በጥሩ ሁኔታ ማጥቃቱንም መከላከሉንም ሲከውን ነበር። በአራቱም ዲፓርትመንቶች የነበሩት ተጫዋቾች የነበራቸው ፍላጎትም የሚደነቅ ነበር። ይህ ፍላጎት እና ተነሳሽነት በነገው ጨዋታም የሚደገም ከሆነ የተሻለ ነገር ከጨዋታው ሊያገኙ ይችላሉ። የሊጉ ሁለተኛው ብዙ ግብ ያስተናገደ ክለብ የሆነው ጅማ የሚተማመንበት የኋላ መስመር እስካሁን የለውም። እንደውም በግብ ዘቡ አላዛር ማርቆስ ብቃት ታገዘ እንጂ ከዚህም በላይ ግቦችን ባስተናገደ ነበር። ይህ የኋላ ክፍል ሜዳውን ለጥጦ በመጫወትም ሆነ ከመሐል የሚነሱ ኳሶችን በመላክ ለማይታውም የሲዳማ የፊት መስመር ጥሩ ምላች ማዘጋጀት አለበት።
እንደገለፅነው ሁለቱን የመሀል ተከላካዮች ጊትጋት ኩት እና ያኩቡ መሐመድን በቅጣት የሚያጣው ሲዳማ ቡና ምንም የጉዳት ዜና የለበትም። ጅማ አባ ጅፋር በበኩሉ ኢዮብ ዓለማየሁን በቅጣት እንዲሁም ሽመልስ ተገኝ እና አልሳህሪ አልማህዲን በፍቃድ ምክንያት አያገኝም።
የጨዋታው ዳኞች – በላይ ታደሠ፣ ሙሉነህ በዳዳ፣ ለዓለም ዋሲሁን፣ ኃይለየሱስ ባዘዘው
ተጨማሪ ዳኞች – ሸዋንግዛው ተባበል እና ወጋየሁ አየለ
እርስ በርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ሰባት ጊዜ ተገናኝተው ጅማ አባ ጅፋር ሦስቱን ሲዳማ ቡና ደግሞ ሁለት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችለዋል። ቀሪዎቹ ሁለቱ ጨዋታዎች ያለ ጎል በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ጅማ 6 ፣ ሲዳማ 7 ጎል አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሲዳማ ቡና (4-1-4-1)
ተክለማርያም ሻንቆ
አማኑኤል እንዳለ – ምንተስኖት ከበደ – ተስፋዬ በቀለ – ሰለሞን ሀብቴ
ሙሉዓለም መስፍን
ሀብታሙ ገዛኸኝ – ዳዊት ተፈራ – ፍሬው ሰለሞን – ይገዙ ቦጋለ
ሳላዲን ሰዒድ
ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)
አላዛር ማርቆስ
በላይ አባይነህ – ኢያሱ ለገሠ – የአብስራ ተስፋዬ – ተስፋዬ መላኩ
መስዑድ መሐመድ – አስጨናቂ ፀጋዬ – ዳዊት እስቲፋኖስ
አድናን ረሻድ – መሐመድኑር ናስር – ሱራፌል ዐወል