ፌዴሬሽኑ ለፕሪሚየር ሊጉ አክስዮን ማህበር የሰጠውን ኃላፊነት ሽሯል

ወቅታዊ የእግርኳሱ ርዕስ በሆነው የጌታነህ ከበደ ጉዳይ መነሻነት የእግርኳሱ የበላይ አካል የሆነው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለፕሪሚየር ሊጉ አክስዮን ማህበር የሰጠውን ኃላፊነት አንስቷል።

የጌታነህ ከበደ ቅጣት ይሻር አይሻርም በሚል በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና በፕሪሚየር ሊጉ አክስዮን ማህበር መካከል ከሰሞኑ መካረር መፈጠሩ ይታወቃል። የፌዴሬሽኑ ዲሲፒሊን ኮሚቴ የጌታነህ ቅጣት እንዲነሳ የወሰነው ውሳኔ በሊጉ አክስዮን ማህበር ተቀባይነት አለማግኘቱን ተከትሎ ፌዴሬሽኑ በሁኔታው ደስተኛ የሆነ አይመስልም። በዚህ መነሻነት አሁን በደረሰን መረጃ የእግርኳሱ የበላይ አካል የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለፕሪሚየር ሊጉ አክስዮን ማህበር የትዕዛዝ ደብዳቤ ልኳል።

ፌዴሬሽኑ በሊጉ ጨዋታዎች ላይ ለሚከሰቱ የዲስፕሊን ጉዳዮች የዲስፕሊን መመሪያውን እና የውድድር ደንቡን በተከተለ መልኩ አፋጣኝ ውሳኔዎችን እንዲወስን ለሊጉ አክሲዮን ማህበር ኃላፊነት እንደሰጠ አስታውሷል። ከዚህ በተጨማሪ በውድድር ስፍራው አንድ ተወካይ በመመደብ በጠቅላላ ጉባኤው ስልጣን ከተሰጠው የፍትህ አካል ጋር በመናበብ እንዲሰራ ታሳቢ አድርጎ እንደነበርም ገልጿል።

ሆኖም ግን ፌዴሬሽኑ እንዳለው የሊጉ የውድድር እና ሥነስርዓት ኮሚቴ ከተሰጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት ውጪ የፍትህ አካላትን ውሳኔ እንደማይቀበል በደብዳቤ በማሳወቁ ከዛሬ ጀምሮ የሊጉ የውድድር ሥነ ስርዓት ኮሚቴ የቢጫ እና የቀይ ካርድ ቅጣትን ካልሆነ በቀር የዲሲፒሊን ጉዳዮችን የመመልከት ሥልጣኑ እንደተነሳ እና የዲሲፒሊን ጥሰቶችን ሪፖርት መርምሮ ውሳኔ የሚሰጠው የፌዴሬሽኑ ዲሲፒሊን ኮሚቴ መሆኑን አሳውቋል።

ከቀናት በፊት በአንድ ጨዋታ ላይ በተፈጠረ ክስተት መነሻውን ያደረገው ጉዳይ አሁን ላይ የሀገሪቱን ሁለት ትላልቅ የእግርኳስ አካላት ማፋጠጡ አስገራሚ ሆኗል። በቀጣይ ጉዳዩ ከዚህ ባለፈ ይዞ የሚመጣቸው አዳዲስ ነገሮች እንደሚኖሩም ይጠበቃል።

ያጋሩ