ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | 26ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ26ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በአንፃራዊነት የተሻለ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾችን ያካተትንበት ምርጥ ቡድናችን የሚከተለው ነው።

ግብ ጠባቂ


አላዛር ማርቆስ – ጅማ አባ ጅፋር

ከአንድ ጨዋታ ቅጣት በኋላ ዳግም የጅማን ግብ ለመጠበቅ በብረቶቹ መሐከል የቆመው አላዛር እንደ ሁል ጊዜው ደምቆ ታይቷል። ቁመታሙ የግብ ዘብ ቡድኑ ሀዲያ ሆሳዕናን አንድ ለምንም በረታበት ጨዋታ በቁጥር 8 ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች አምክኗል። አንዳንዶቹን እንደውም በጥሩ የእጅ እና የእግር ቅልጥፍና ሲያመክን የነበረበት መንገድ የሚያስደንቀው ነበር።

ተከላካዮች

ያሬድ ባየህ – ፋሲል ከነማ

የወቅቱ የሊጉ ዋንጫ ባለቤት ፋሲል ከነማ ከሰበታ ሦስት ነጥብ አግኝቶ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን ልዩነት ወደ ሦስት እንዲያጠብ የሚያስችል ብቸኛ ጎል ያስቆጠረው አምበሉ ያሬድ ባየህ ነው። ተጫዋቹ ውዷን ግብ ራሱን ነፃ አድርጎ በመቆም በግራ እግሩ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ዋና ሀላፊነቱ የሆነው የመከላከል ሥራ አምብዛም ባይበዛበትም ሰበታዎች በመልሶ ማጥቃት ለመውጣት የጣሩባቸውን ቅፅበቶች ሲያመክን ነበር።

ላውረንስ ላርቴ – ሀዋሳ ከተማ

ቀልጣፋው ተከላካይ በጉዳት ከሜዳ ርቆ በነበረባቸው ያለፉት 3 ጨዋታዎች ላይ ብቻ 7 ግቦችን ያስተናገዱት ሀይቆቹ በዚህኛው ሳምንት የኋላ ክፍሉን መሪያቸውን ሲያገኙ የተረጋጉ መስለዋል። ላውረንስ ያን ያህል በድሬዳዋ አጥቂዎች ባይፈተንም የዐየር እና መሬት የአንድ ለአንድ ፍልሚያዎችን እየረታ ቡድኑን ሲጠቅም ታይቷል። ይህንን ተከትሎም በምርጥ ቡድናችን አስገብተነዋል።

ወልደአማኑኤል ጌቱ – ሰበታ ከተማ

የተሟላ የጋራ ልምምድ ሳያደርጉ ሊጉን የጀመሩት ሰበታዎች ከኳስ ውጪ ለመንቀሳቀስ በመረጡት አጨዋወት ጉልህ ድርሻ የነበረው ተጫዋች ወልደአማኑኤል ነው። ግባቸውን አለማስደፈር ተቀዳሚ ዓላማ አድርገው ሲጫወት በነበረው ስብስብ ውስጥም ተከላካዩ ፈጣኖቹን የፋሲል አጥቂዎች ለመቆጣጠር የጣረበት መንገድ ጥሩ ነበር።

አማካዮች

ዳንኤል ደርቤ – ሀዋሳ ከተማ

በቀኝ መስመር ተመላላች እና ተከላላይ ሚና የተዋጣለት የሀዋሳው አምበል ዳንኤል በድሬዳዋው ጨዋታ ያሳየው ብቃት በምርጥ ቡድናችን እንዲገባ አድርጎታል። ተጫዋቹ ብሩክ በየነ ያስቆጠረውን ሁለተኛ ኳስ አመቻችቶ ከማቀበሉ በተጨማሪ ሌሎች የማጥቃት ቅፅበቶች የነበሩት ሲሆን ከኳስ ውጪ ብዙ ለቆየው ቡድኑም ጥሩ የመከላከል ጥንካሬ ሲሰጥ ነበር።

እንዳልካቸው መስፍን – አርባምንጭ ከተማ

በአርባምንጭ ቤት ብዙ ደቂቃዎችን (2104 ደቂቃዎችን) ግልጋሎት የሰጠው እንዳልካቸው መስፍን ባሳለፍነው ሳምንት ጎልተው ከታዩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። ከወትሮ በተለይ ለተጋጣሚ ሳጥን ተጠግቶ እንዲጫወት ሀላፊነት የተሰጠው ተጫዋቹም በ33ኛው ደቂቃ ኤሪክ ካፓይቶ ላስቆጠረው ጎል የበኩሉን ተወጥቶ የመጨረሻ ኳስ ልኳል።

መስዑድ መሐመድ – ጅማ አባ ጅፋር

በጅማ አባ ጅፋር የአማካይ መስመር ጥንካሬ ጉልህ ድርሻ የሚወስደው መስዑድ መሐመድ ቡድኑ ሀዲያን በረታበት ፍልሚያ ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጪ ጥሩ ብቃት አሳይቷል። በተለይ ቡድኑ ከኳስ ጋር ጊዜ በማሳለፍ የተጋጣሚን ክፍተቶች ለማፈንፈን በሚሞክርበት ሰዓት የመስዑድ መኖር አስፈላጊ ነው። አልፎም ከርከት የሚሞክራቸው ሙከራዎች እና የመጨረሻ ኳሶችም ለከቤራዎቹ ፈተናን ሲለግሱ ታይቷል።

ኤፍሬም አሻሞ – ሀዋሳ ከተማ

ፈጣኑ ተጫዋች ቡድኑ ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር እንዲታረቅ በጥሩ ሁኔታ ሲታትር ተስተውሏል። ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረውን የቡድኑን እንቅስቃሴም በጎል እንዲታጀብ በማድረግ የመክፈቻውን ጎል በስሙ አስመዝግቧል። ተባረክን በ73ኛው ደቂቃ ቀይሮ እስከ ወጣበት ጊዜ ድረስም ወረቀት ላይ ከተሰለፈበት የአጥቂነት ሚና እየወረደ ቡድኑን ጠጣራ ለማድረግ ሞክሯል።

አጥቂዎች


ብሩክ በየነ – ሀዋሳ ከተማ

ብሩክ ቡድኑ ሀዋሳ ድሬዳዋን ሲረታ የውድድር ዓመቱ 10ኛ እና 11ኛ ጎሉን በግራ እና ቀኝ እግሩ አስቆጥሯል። በተጋጣሚ ሳጥን አይምሬ ሆኖ በጨዋታው የታየው ብሩክ ኤፍሬም ያስቆጠረውንም ግብ በመስመሮች መካከል ተገኝቶ አመቻችቶ አቀብሏል። በዋናነት ደግሞ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከተከላካዮች ጀርባ እና መሀል እየገባ አደጋዎችን ለመፍጠር ያደረገው ጥረት በቡድናችን ቦታ እንዲያገኝ አድርጎታል።

ኤሪክ ካፓይቶ – አርባምንጭ ከተማ

አርባምንጭ ከአስጊው ቀጠና ራቅ እንዲል ያደረገበትን ውጤት ሲዳማ ቡና ላይ ሲቀዳጅ የኬኒያዊው አጥቂ ብቃት ወሳኝ ነው። ተጫዋቹ የክለቡ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነበትን ቀን ሲያሳልፍ ለሲዳማ ተከላካዮች ፈተና ነበር። ከግቦቹ በተጨማሪም ያኩቡ መሐመድ በ57ኛው ደቂቃ ከሜዳ እንዲወጣ ምክንያት ሆኗል። በዕለቱ ያሳየውን ብቃት ተከትሎም የምርጥ ቡድናችን አጋፋሪ አድርገነዋል።

አቡበከር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና

የወቅቱ የሀገራችን ምርጥ ተጫዋች የሆነው አቡበከር በተጠናቀቀው ሳምንት ከብዙዎች ዘንድ አድናቆት እንዲቸረው ያስቻለውን ሌላ የብቃት ልዕልና አስመልክቷል። ተጫዋቹ ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ አዳማን ሲረታ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን ከተከላካዮች አፈትልኮ በመውጣት ሲያደርጋቸው የነበሩ ጥቃቶችም ለግብነት የቀረቡ ነበሩ። ከምንም በላይ ደግሞ በ78ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል በግርምት የብዙዎች ቅንድብ ወደ ላይ እንዲሰቀል ያደረገች ነበረች።

አሠልጣኝ


ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

በጨዋታ ሳምንቱ ቡድናቸው ድል እንዲያደርግ ጥሩ የሜዳ ላይ ስራ የከወኑ አሠልጣኞች የኖሩ ቢሆንም የኢትዮጵያ ቡናውን አለቃ በምርጥ ቡድናችን መርጠናል። አሠልጣኙ በአዳማ ገና በጊዜ ግብ አስተናግዶ የነበረው ቡድናቸው በትዕግስት ወደ ጨዋታው እንዲመለስበት ያደረጉበት መንገድ ድንቅ ነበር። በተለይ በእረፍት ሰዓት ተሻሽሎ ወደ ሜዳ የገባው ቡድኑ ወደ ራሱ ሜዳ ወረድ ብሎ ሲከላከል የነበረውን የአዳማ ስብስብ ለማስከፈት መፍትሔዎች ነበሩት። ከመመራት ተነስቶም ድል እንዲገኝ ስላደረጉ የምርጥ ቡድናችን መሪ አድርገናቸዋል።

ተጠባባቂ

መሳይ አያኖ
በርናንድ ኦቺንግ
ኦሴ ማውሊ
አቡበከር ሻሚል
አለልኝ አዘነ
አላዛር ሽመልስ
አስራት ቱንጆ