ሪፖርት | ወላይታ ድቻ እና መከላከያ ነጥብ ተጋርተዋል

እንደ አየር ፀባዩ ሁሉ እጅግ ቀዝቃዛ የነበረው የወላይታ ድቻ እና መከላከያ ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ወላይታ ድቻዎች በአዲስ አበባ ከተማ ከተሸነፈው ስብስብ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ የቀረቡ ሲሆን በአንፃሩ መከላከያዎች ደግሞ ከወልቂጤ አቻ ከተለያየው ስብስብ ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች ገናናው ረጋሳ እና ቅጣት ያለበት ኢማኑኤል ላርዬን አስወጥተው በምትካቸው ኢብራሂም ሁሴን እና ግሩም ሀጎስን ተክተው አስገብተዋል።

ቀዝቀዝ ባለ የአየር ንብረት ታጅቦ በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ወላይታ ድቻዎች በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ጨዋታውን የጀመሩ ሲሆን በዚህም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ምንም እንኳን ኢላማቸውን ወደጠበቁ የግብ ሙከራዎች መቀየር ባይችሉም ሦስት አደገኛ አጋጣሚዎችን በቃልኪዳን ዘላለም በተሰለፈበት የግራ መስመር በኩል መፍጠር ችለዋል።

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ራሳቸው ማስገባት የጀመሩት መከላከያዎች በቀጣይ በተከታታይ አደገኛ የግብ ሙከራዎችን ሲሰነዝሩ ተመልክተናል ፤ በተለይም ቢኒያም በላይ ከተሰለፈበት የግራ መስመር በኩል መነሻቸውን ያደረጉ ጥቃቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ። መከላከያዎች በ13ኛ ደቂቃ ላይ ቢኒያም በላይ በግራ የሳጥን ጠርዝ በረከት ወ/ዮሐንስን አልፎ ያደረገው እና ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታካ በወጣችበት ሙከራ ጥረታቸቅን አንድ ብለው ጀምረዋል።

በ16ኛው ደቂቃ ላይ እስራኤል እሸቱ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ያሻማው ኳስ ቢኒያም በላይ ሳይደርስበት የቀረው እንዲሁም በ20ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም በላይ በግሩም ሁኔታ ከግራ መስመር ያደረሰውን ኳስ ከቀኝ የሳጥን ጠርዝ ሰብሮ የገባው ተሻመ በላቸው ግሩም ሙከራ ቢያደርግም ኳሷ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችበት ሙከራ ተጠቃሽ ናቸው። ጥቃት መሰንዘራቸውን የቀጠሉት መከላከያዎች በ25ኛው ደቂቃ ደግሞ ፍፁም ያለቀለትን አጋጣሚ አምክነዋል። ክሌመንት ቦዬ በረጅሙ ያደረሰውን ኳስ እስራኤል እሸቱ ከወላይታ ድቻ ተከላካዮች አፈትልኮ በማምልጥ ከቢኒያም ገነቱ ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም እስራኤል ግን ያገኘውን ፍፁም ያለቀለት አጋጣሚን አምክኗል።

እጅግ ከፍተኛ በሆነ ዝናብ ውስጥ መካሄዱን በቀጠለው ጨዋታ መከላከያዎች ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉበት ነበር። በ33ኛው ደቂቃ ቢኒያም በላይ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ምንተስኖት አዳነ በግንባሩ ገጭቶ የሞከረው እንዲሁም በ44ኛው ደቂቃ ላይ አዲሱ አቱላ ከመልስ ውርወራ የተቀበለውን ኳስ አንድ ተጫዋች አልፎ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በቢኒያም ገነቱ ቅልጥፍና ድናበታለች።

ሁለተኛው አጋማሽም እንደ መጀመሪያው ሁሉ በእንቅስቃሴ ረገድ ተመጣጣኝ ይዘት የነበረው ቢመስልም ወደ ተጋጣሚም የማጥቃት ሲሶ በመድረስ ረገድ ግን መከላከያዎች በተወሰነ መልኩ ብልጫ ነበራቸው። በማጥቃቱ ረገድ ፍፁም ደካማ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ሦስቱ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች ከተቀሩት የቡድኑ አባላት ድጋፍ ማግኘት አለመቻላቸውን ተከትሎ በጨዋታው አጥቂዎቹ በአመዛኙ ሜዳ ላይ ሲባክኑ ተመልከተናል። በአንፃሩ መከላከያዎች ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ፊት የመሄድ ፍላጎታቸውን በዚህኛው አጋማሽም የቀጠለ ቢመስልም የቢኒያም በላይ ተፅዕኖ መደብዘዝን ተከትሎ ዕድሎችን ለማፍጠር በጣም ተቸግረው አስተውለናል።

በሙከራዎች ረገድ በመጀመሪያ አጋማሽ ደካማ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በሁለተኛው አጋማሽ ግን የተሻሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል። በ53ኛው ደቂቃ ወላይታ ድቻዎች በክሌመንት ቦዬ ስህተት ካገኙት የማዕዘን ምት አጋጣሚ የተሻማውን ኳስ ስንታየሁ መንግሥቱ በግንባሩ ገጭቶ ያደረው ሙከራ በአዲሱ አቱላ ሲመለስ በቅርብ ርቀት የነበረው ደጉ ደበበ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ ሲመለስባቸው በ85ኛው ደቂቃ ደግሞ ስንታየሁ መንግሥቱ ከግራ መስመር የደረሰውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ሆኖ በመቀበል በርከት ያሉ የመከላከያ ተጫዋቾችን አልፎ ያደረገው ሙከራ በክሌመንት ቦዬ ድኖበታል።

ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ወላይታ ድቻዎች በ38 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ሲረጉ በአንፃሩ መከላከያዎች ደግሞ ነጥባቸውን ወደ 33 እንዲሁም ደረጃቸውን ደግሞ ወደ 8ኛ አሳድገዋል።