የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 0-0 መከላከያ

በዕለቱ ቀዳሚ በነበረው እና ያለ ግብ በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

ስለጨዋታው

“ጨዋታው እንደጠበቅነው እነሱ ጠንክረው ነበር የገቡት ፤ ጥሩ ቡድን ነው። በተጨማሪም ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ከባድ ፈተና እንደሚገጥመን ገምተን ነበር። ሜዳ ላይም የገጠመን ተመሳሳይ ነገር ነው ፤ በተለይም በመጀመሪያ አጋማሽ። ነገር ግን በሁለተኛው አጋማሽ የተከላካይ ቁጥር ቀንሰን ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ለማጥቃት ሞክረናል። በአጠቃላይ አቅም በፈቀደ መልኩ የቻልነውን አድርገናል።

ወደ አሸናፊነት መመለስ ስለመቸገራቸው

“በዋነኝነት ከአጥቂዎቻችን ጉዳት ጋር የሚያያዝ ነው። ስለዚህ በቀሪ ጨዋታዎች የተጫዋቾች አደራደራችን በመለወጥ በዛሬው ጨዋታ እንደተመለከታችሁት ሞክረን ነበር ግን አልተሳካም። አሁንም ቢሆን በአቅማችን ልክ ነው ቡድን ለመገንባት እየጣርን የምንገኘው ከኳስ ውጪ ያለን ነገር ጥሩ ነው። ነገር ግን ኳስ ስንይዝ ያለን ማጥቃት መታረም የሚገባው ነው።”

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ – መከላከያ

ስለጨዋታው

“ጥሩ ጨዋታ ነበር። ሦስት ነጥብ ማግኘት ባንችልም የተሻለ ተጫውተናል ብለን እናስባለን። ዕድሎችን አግኘተን መጨረስ አልቻልንም ፤ ነገር ግን ከዝናቡ እና ሌሎች ሁኔታዎች አንፃር ጥሩ ነው ብለን እንወስዳለን።

በመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ስላለመቻላቸው

“መጨረስ….፤ ሌላውንማ ያያችሁት ነው ጎል አካባቢ ሳጥን ውስጥ እንደርሳለን ፣ በሦስቱም ጨዋታዎች ከተጋጣሚ በተሻለ አጥቀተን ተጫውተናል ግን በሦስቱም ጨዋታዎች ዕድሎችን መጨረስ አልቻልንም።

ስለቀሪ ሦስት ጨዋታዎቻቸው (ሁለቱ ላለመውረድ የሚጫወቱ መሆናቸው)

“ላለመውረድ ጥረት የሚጀመረው ገና ከመጀመሪያው ጨዋታ ነው። አሁን ወደ መጨረሻው ያለው ነገር ለመትረፍ እንጂ ላለመውረድ አይደለም። ገና ከመጀመሪያው እንደተናገርኩት የዘንድሮው ውድድር በጣም ከባድ ነው። ዋንጫ የሚወስደውም ሆነ የሚወርደው በእኔ ግምት በመጨረሻው ጨዋታ የሚታወቅ ነው። ስለዚህ ማድረግ የሚገባን የራሳችንን ሥራ ሰርተን ቡድናችንን በሊጉ ማቆየት ነው እንጂ በሁለተኛው ዙር የምታደርገው የትኛውም ጨዋታ በጣም ወሳኝ ነው። እኛም ሆንን ሌሎች ቡድኖች መጀመሪያ ጨርሰን መጥተን ቢሆን ኖሮ እዚህ ነገር ውስጥ አንገባም ነበር። ሊጉ ደስ የሚል ሂደት ላይ ይገኛል። እናንተም እንደምትሉት አብዛኞቹ አሰልጣኞች እኔንም ጨምሮ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ላይ ሆነን ሳንተኛ ቁጭ ብለን ነጥብ ስንደምር እና ስንቀንስ አያደርን ነው።”

ያጋሩ