ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ጅማን በመርታት ከሀዋሳ የ3ኛነት ደረጃውን አስመልሷል

በዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሲዳማ ቡና በጅማ አባ ጅፋር ላይ ያሳካውን የ2-1 ድል ተከትሎ ደረጃውን ሲያሻሽል ጅማ ይበልጥ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።

ሲዳማ ቡና ከአርባምንጭ ከተማው ሽንፈት ባደረጋቸው ለውጦች ሰለሞን ሀብቴን በመሀሪ መና እንዲሁም ቅጣት ያለበት ያኩቡ መሐመድን ለዋናው ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ባደረገው በመኳንንት ካሳ ለውጧል። ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ ሀዲያ ሆሳዕናን ካሻነፈበት ጨዋታ ባደረገው ብቸኛ ለውጥ የአራት ጨዋታዎች ቅጣት የተላለፈበት እዮብ ዓለማየሁን በወንድምአገኝ ማርቆስ ተክቷል።

በጨዋታው ጅማሮ ጅማ አባ ጅፋር በመሐመድኑር ናስር የግንባር ኳስ በሙከራ ቀዳሚ መሆን ቢችልም ሲዳማ ቡናዎች የማጥቃት የበላይነቱን ይዘው ዘልቀዋል። ቡድኑ ወደ ግብ በደረሰበት ቀዳሚ አጋጣሚም 9ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ በግሩም ሁኔታ ያሳለፈለትን ተንጠልጣይ ኳስ ይዞ ሳጥን ውስጥ የደረሰው ይገዙ ቦጋለ ሙከራው ወደ ውጪ ወጥቷል። ይሁን እንጂ ሲዳማዎች እምብዛም ሳይቆዩ ጎል አግኝተዋል። በዚህም 13ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ሰዒድ ግሩም የቅጣት ምት ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ከግቡ በኋላ ጅማ አባ ጅፋሮች የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በመያዝ በተሻለ ሁኔታ የሲዳማ ቡና ሜዳ ላይ አመዝነው መንቀሳቀስ ችለዋል። 21ኛው ደቂቃ ላይ አስጨናቂ ፀጋዬ ከበላይ ዓባይነህ የማዕዘን ምት በግንባሩ ሞክሮት ወደ ውጪ የወጣውን እና 24ኛው ደቂቃ ላይ የዳዊት እስጢፋኖስ ቅጣት ምት በተከላካዮች ሲደረብ አግኝቶ አካሉ አትሞ ከሳጥን ውጪ መቶት መክብብ ደገፉ የያዘበትን ኳስም ሞክረዋል።

ከዉሃ ዕረፍቱ በኋላ የጅማዎች የኳስ ቁጥጥር ጫና ይበልጥ ከፍ ያለ መስሎ ታይቷል። ሆኖም ቡድኑ 32ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት እስጢፋኖስ ከቅጣት ምት ካደረገው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሌላ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻለም። ከኳስ ውጪ በጥሩ አደረጃጀት ከጅማ አማካዮች የሚነሱ ኳሶችን በማቋረጥ ጥሩ አጋማሽ ያሳለፉት ሲዳማዎችም ፈጠን ባሉ ጥቃቶች ወደ ግብ ለመድረስ ቢሞክሩም ሌላ የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ ጨዋታው ተጋምሷል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች በተሻለ የጨዋታ ቁጥጥር የጀመሩት ነበር። ሆኖም ቡድኑ በበሂደት ዝግ ወዳለ የኳስ ቁጥጥር ማዘንበሉ ለጅማ መልሶ ማጥቃት ሲያጋልጠው ታይቷል። 52ኛው ደቂቃ ላይ ጅማዎች ሳጥን ውስጥ በቁጥር በርክተው የተገኙበት ቅፅበት ባይጠቀሙበትም በዚህ ረገድ የሚጠቀስ ሲሆን መስዑድ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ በመሞከር ዳዊት እስጢፋኖስ ደግሞ ወደ መሐመድኑር ተንጠልጣይ ኳስ በመላክ የሲዳማን የመከላከል ወረዳ ፈትሸዋል።

ጨዋታው በሁለቱ ሳጥኖች ለግብ በቀረበባቸው አጋጣሚዎች ደግሞ 61ኛው ደቂቃ ላይ ይገዙ ቦጋለ ከቀኝ ከአማኑኤል እንዳለ የተቀበለውን ኳስ ከሀብታሙ ገዛኸኝ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ሲወጣበት 63ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በሌላኛው የግብ ክልል መክብብ ደገፉ ጅማዎች በፈጣን ጥቃት ሳጥን ውስጥ በደረሱበት እና በቅድሚያ ተስፋዬ መላኩ በመቀጠል ዳዊት እስጢፋኖስ የሞከሯቸውን ተከታታይ ኳሶች አድኗል። የጨዋታው ትኩረት ሳቢነት በቀጣዩ ደቂቃም ቀጥሎ ወጣቱ የሲዳማ ቡና የመሀል ተከላካይ መኳንንት ካሳ መሐመድኑር ናስር ላይ በስራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

የጨዋታው ግለት እየጨመረ በመጣባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች የሲዳማ ቡና ፈጣን ጥቃቶች እና የጅማ ሰንጣቂ ኳሶች መታየታቸውን ቀጥለዋል። ሆኖም በጎዶሎም ሆነው ጥቃታቸው ያልቀነሰው ሲዳማዎች በተሻለ ሁኔታ ጫና መፍጠር ሲችሉ 75ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል።

ይገዙ ቦጋለ ፍሬው ሰለሞን በጥሩ ሁኔታ ያሳለፈለትን ኳስ ሳጥን ውስጥ ተቆጣጥሮ በእርጋታ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል። ቀሪ ደቂቃዎች ሲዳማ ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ይጨርሳል ተብሎ ቢጠበቅም ጨዋታው ይበልጥ በፉክክር የተሞላ ሆኗል። ጅማ አባ ጅፍሮች ምላሽ ለመስጠት በቅብብሎች ወደ ሲዳማ ሜዳ አድልተው ባደረጉት ጥረት 81ኛው ደቂቃ ላይ ቦና ዓሊ ከቀኝ መስማር ያሳለፈውን ኳስ ምስጋናው መላኩ በግንባሩ በመጭረፍ ግብ አድርጎታል።

ከዚህ በኋላ ዘጠና ደቂቃው አልቆ 6 ደቂቃዎች በተጨመሩበት ጨዋታ ጅማዎች ሁሉንም ነገር ወደ ፊት ወርውረዋል። ሆኖም 86ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዐወል ከሳጥኑ መግቢያ ከመከረው እና መክብብ ከያዘበት ኳስ ውጪ ሲዳማ ቡናዎች በብርቱ በመከላከል ጨዋታውን በድል መወጣት ችለዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና በ43 ነጥቦች ወደ 3ኛ ደረጃ ሲመለስ ጅማ አባ ጅፋር በ23 ነጥቦች በወራጅ ቀጠና ውስጥ ለመቆየት ተገዷል።