የአሠልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 2-1 ጅማ አባ ጅፋር

ሲዳማ ቡና ጅማ አባ ጅፋርን ሁለት ለአንድ ከረታበት ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከአሠልጣኞች አስተያየት ተቀብሏል።

አሰልጣኝ ወንድምአገኝ ተሾመ – ሲዳማ ቡና

ጨዋታው እንዴት ነበር…?

ጨዋታው በጣም ከጠበኩት በላይ ነው። ውጤቱ ስለሚያስፈልገን ለውጤቱ ነበር ትልቅ ትኩረት ያደረግነው። ውጤቱን ይዤ በመውጣቴም ደስ ብሎኛል።

የተከላካይ መስመር ተጫዋቾቹ በተከታታይ ጨዋታ በቀይ ካርደ ስለመውጣታቸው…?

የተከላካይ ክፍሉ ላይ የጊት እና ያኩቡ አለመኖር ትንሽ ክፍተት እንደሚፈጥርብን የታወቀ ነው። ይሄንን ለማስተካከል የተጠቀምነው ታክቲካል ለውጥ ነበር። ያም ሆኖ ኳሳዊ ሂደቶች ናቸው የተፈጠሩት። ነገም የሚፈጠር ነው። ነገርግን ከመቀነስ አኳያ ለመስራት እንሞክራለን።

ጅማ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ስለነበረው ጭንቀት…?

በጎዶሎ መጫወት ምን ያህል ጫና እንዳለው የሚታወቅ ነው። ይሄንን ጫና ተቋቁመን ውጤት አስጠብቀን መውጣታችን የእኛ ኬሊቲ ነው።

ስለተጋጣሚ ቡድን ጥንካሬ…?

መጀመሪያም የታወቀ ነው። ወራጅ ቀጠና ውስጥ ያለ ቡድን ሁሌ ራሱን የተሻለ ቦታ ለማምጣት እና በእንቅስቃሴ ደረጃ እይታ ውስጥ ለመግባት የሚያደርገው ጥረት የሚጠበቅ ነው። ይህንን ተከትሎ ጠንካራ ውድድር እንደነበር መጀመሪያም ተናግሬ ነበር።

ስለሦስተኛ ደረጃ…?

ምንም ጥርጥር የሌለው ነው። የሦስተኝነት ቦታን 100 በ100 እንፈልገዋለን።

አሰልጣኝ የሱፍ ዓሊ – ጅማ አባ ጅፋር

ጨዋታው እንዴት ነበር…?

በመጀመሪያው አጋማሽ እነርሱ የተሻሉ ነበሩ። እኛ ኳስ ቁጥጥሩ ላይ ነበር ትኩረታችን። እነርሱ ያገኙትን አጋጣሚ ተጠቅመዋል። እኛ ጋር እንደ ስህተት የነበረው ኳሱን መቆጣጠር ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጋችን ነው።

ሲዳማ ቡና በቀይ ካርድ ምክንያት ተጫዋቾ ጎሎበት አጋጣሚውን ስላለመጠቀማቸው…?

ከቀዩ ካርዱ በኋላ እንደ አጨዋወታችን ከሆነ ብዙ ወደ ፊት አንሄድም ነበር። በተደጋጋሚ እየተናገርን ነበር። ይሄ ነበር ስህተቱ። የውጤቱም መንስኤ ይሄ ነው።

ስለቀጣይ ጨዋታዎች

ከፈጣሪ ጋር ማሸነፍ ላይ ትኩረት አድርገን መጨረሻውን ማየት ነው። ውድድሩ አላለቀም። ገና ነው። እንደሚታየው ደግሞ ከእኛ ጋር የሚፎካከሩ ቡድኖች በአብዛኞቹ ነጥብ እየጣሉ ነው። እኛ ደግሞ የተሻለውን ውጤት ለማምጣት እንሞክራለን። መጨረሻውን ማየት ነው።

ከሌሎቹ በወራጅ ቀጠናው የሚገኙ ክለቦች አንፃር ስለሚያደርጉት እንቅስቃሴ…?

እንደምናየው ከሆነ ላለመውረድ የሚጫወት ቡድን አይደለም። የተሻለ ነገር አለው። አጋጣሚዎች እና በፊት የነበሩ ስህተቶች ተደምረው ነው ለዚህ መንስኤ የሆነው።