የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መሪው ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባለ ድል ሆነዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ቀን የ14ተኛ ሳምንት ሦስት ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ መሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲያሸንፉ ባህርዳር እና አዲስ አበባ ያለ ጎል ፈፅመዋል፡፡

ባህር ዳር ከተማ 0-0 አዲስ አበባ ከተማ

3፡00 ሰዓት ላይ ባህር ዳር ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚው መርሀግብር ተጀምሯል፡፡ በኳስ ቁጥጥሩ ተመሳሳይ የሆነ መልክን ብናይበትም የጎል ሙከራዎችን እምብዛም ባላሳየን የመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኖቹ መሀል ሜዳ ላይ ጥቅጥቅ ብለው መጫወት መቻላቸው ወደ ጎል ክልል እንዳይደርሱ ዕክል ሆኖባቸው ከርሟል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ 3ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ክፍሉ ሰንጣቂ ኳስ የደረሳት አሪያት ኦዶንግ ከግብ ጠባቂዋ ባንቺአየው ደመላሽ ጋር ተገናኝታ ወደ ግብነት ለወጠችው ሲባል በሳተቻት ሙከራ ቀዳሚ ሆነዋል፡፡

በአጋማሹ የተመለከትነው ሌላኛዋ ሙከራ አሁንም በአዲስ አበባ ከተማ የተደረገ ነበር፡፡ አጥቂዋ አሪያት ኦዶንግ ወደ መልበሻ ክፍል ለማምራት ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ያመከነችዋ ሌላኛዋ ሙከራ ነበረች፡፡ በዚህኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ባህርዳሮች በእንቅስቃሴ የተሻሉ ሆነው ሜዳ ላይ የታዩ ይምሰል እንጂ ወደ ከጎል ጋር የሚገናኙበት መንገድ ስኬት አልነበረም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ በአመዛኙ ልቀው መገኘት የቻሉት የአሰልጣኝ ሰርካዲስ ዕውነቱው ባህርዳር ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የታየባቸውን ቀርፈው ወደ ሜዳ ተመልሰዋል፡፡ በአንፃሩ በየሺሀረግ ለገሰ የሚመራው የመዲናይቱ ክለብ በመልሶ ማጥቃት የጨዋታ ቅኝት አቀራረባቸውን በማድረግ በተለይ ወደ ባህር ዳር የግራ መስመር በኩል ለመጫወት ሁነኛ መንገዳቸው ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ 54ኛው ደቂቃ ላይ ዘይነ ሰይድ በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ከአሪያት ኦዶንግ የደረሳትን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ መታው ግብ ጠባቂዋ ባንቺአየው ያዳነችባት አዲስ አበባን ቀዳሚ የግብ አጋጣሚን ፈጣሪ ቡድን አድርጎታል፡፡
ሳባ ኃይለሚካኤልን ቀይሮ ካስገባ በኋላ ተጫዋቿ በተደጋጋሚ በምታሻግረው ተሻጋሪ ኳሶች ልዩነት ለመፍጠር የጣና ሞገደኞቹ እንስቶች ጥረት አድርገው ታይተዋል፡፡ ሳባ ከርቀት አክርራ መትታ ለጥቂት የወጣባት አዳነች ጌታቸው ከቅጣት ምት አሻምታ ትዕግስት ወርቁ በግንባር ገጭታ ሊወጣ የቻለባት የባህር ዳርን የመሻሻል ሂደቶች ያሳዩ ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባዎች በኩል ከቅጣት ምት በሻዱ ረጋሳ አክርራ መትታ በግብ ጠባቂ የተመለሰባት እና ጨዋታው ሊገባድ ሲል ሰላማዊት ኃይሌ ያደረገችው የሚጠቀሱ ቢሆንም ጨዋታው ያለ ጎል ተጠናቋል፡፡

ኢትዮ ኤሌክትሪክ 4-2 ቅዱስ ጊዮርጊስ

እጅግ ማራኪ የሜዳ ላይ ፉክክርን ባስተዋልንበት የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የ8፡00 ሰዓት ጨዋታ የተሻለ ንቃት በመጀመሪያው አጋማሽ የሚታይባቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች 14ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን የቅብብል ሂደት በፍቅርአዲስ ገዛኸኝ ጎል መሪ መሆን ቢችሉም 42ኛው ደቂቃ ላይ ምንትዋብ ዮሐንስ ከቀኝ አቅጣጫ ወደ ግብ ክልል ስታሻማ ተከላካይዋ አረጋሽ ፀጋ በግንባር በመግጨት አስቆጥራ ኤሌክትሪክን አቻ ማድረግ ችላለች፡፡

ከዕረፍት መልስ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ወደ ጨዋታ መንፈስ በደንብ መግባት የቻሉት ኤሌክትሪኮች በተደጋጋሚ በዓይናለም አሳምነው ተቀይራ በገባችው ትንቢት ሳሙኤል እና ሰላማዊት ጎሳዬ አማካኝነት ያለቀላቸውን ዕድሎች መፍጠር ችለዋል፡፡ ቤተልሄም ዘውዴ ተቀይራ ከገባች ሁለት ያህል ደቂቃ እንደሆናት ለዓይናለም ሰጥታት ዓይናለም ነፃ ለነበረችው ሰላማዊት አቀብላት አጥቂዋ ኤሌክትሪክ ወደ መራነት አሸጋግራለች፡፡ የረዳት ዳኞች ያለ መናበብ ጎልቶ መታየት የቻለበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በቤተልሔም መንተሎ ጎል ጊዮርጊሶች ወደ 2-2 ተሸጋግረው የነበረ ቢሆንም አረጋሽ ፀጋ እና ሰላማዊት ጎሳዬ ተጨማሪ ጎሎችን አክለው ጨዋታው 4-2 በኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

አርባምንጭ ከተማ 0-2 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ፕሪምየር ሊጉን እየመራ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአርባምንጭ ከተማ ተፈትኖም ቢሆን ድል አድርጓል፡፡ ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ አቅምን ባየንበት ጨዋታ የአርባምንጭ ከተማ የመልሶ ማጥቃት እና ተሻጋሪ ኳሶች ትኩረትን ይስቡ ነበር፡፡ ነገር ግን ሎዛ አበራ ከቅጣት ምት አስደናቂ ጎል ከመረብ አሳርፋ ባንክን መሪ አድርጋለች፡፡ በወርቅነሽ ሜልሜላ እና ሰርካለም ባሳ አማካኝነት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ የነበሩት አርባምንጭ ከተማዎች መረጋጋት ተስኗቸው በቀላሉ ማስቆጠር የሚችሉትን ጎሎች በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ አግኝተው መጠቀም አልቻሉም፡፡

በሂደት የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ብርቱካን ገብረክርስቶስን እና ሰናይት ቦጋለን ከዕረፍት መልስ በማጣመር ብልጫ ለመውሰድ የሞከሩት የብርሀኑ ግዛው ንግድ ባንኮች 54ኛው ደቂቃ የሰናይት ቦጋለ እና የሎዛ ቅብብል ሰምሮ ሎዛ ነፃ ለነበረችው መዲና ዐወል አቀብላት አጥቂዋም ወደ ጎልነት ለውጣው ጨዋታው በንግድ ባንክ 2-0 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡