ሪፖርት | ሙጂብ ቃሲም ዐፄዎቹን በዋንጫ ፉክክር አቆይቷል

በዕለቱ የመጀመሪያ በነበረው ጨዋታ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ ወዲህ ከግብ ርቆ የሰነበተው ሙጂብ ቃሲም ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ፋሲል ከነማ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን ልዩነት አስጠብቆ እንዲቀጥል አስችሏል።

አዳማ ከተማዎች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ከተረታው ስብስብ ባደረጓቸው ለውጦች ፀጋአብ ዮሴፍ እና ቅጣት ያለበት ቶማስ ስምረቱን በዮሴፍ ዮሐንስ እና እዮብ ማቲዎስን ተክተው ያስገቡ ሲሆን በአንፃሩ ሰበታ ከተማን አሸንፈው የመጡት ፋሲል ከነማዎች ደግሞ ከድር ኩሊባሊ ፣ በዛብህ መለዮ እና ጉዳት ያገኘው ኦኪኪ አፎላቢን አስወጥተው በምትካቸው አስቻለው ታመነ ፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና በረከት ደስታን ተክተው በማስገባት የዛሬውን ጨዋታ አድርገዋል።

እጅግ ቀዝቃዛ አጀማመር ባስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአመዛኙ አዳማ ከተማዎች ከኳስ ጀርባ በጥንቃቄ ለመከላከል ጥረት ያደረጉበት እንዲሁም ፋሲል ከተማዎች ደግሞ ይህን የአዳማን የመከላከል ውቅር ለመስበር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የተመለከትንበት ነበር። ፋሲሎች በርከት ያሉ የኳስ ቅብብሎችን በማድረግ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ተደጋጋሚ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም በተለይ በቀኝ መስመር በኩል የነበራቸው አፈፃፀም በንፅፅር የተሻለ ሆኖ ተመልክተናል።

በ9ኛው እና 14ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ከተሻማ ኳስ በረከት ደስታ ሁለት አጋጣሚዎችን ቢያገኝም ኳሶቹን መጠቀም ሳይችል የቀረ ሲሆን ከዚህ ውጪ በአንድ አጋጣሚ ሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥን ውጪ ካደረገው ሙከራ ሌላ በአዳማ የሜዳ አጋማሽ እንዳሳለፉት ደቂቃ ፋሲሎች በቂ ዕድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ምንም እንኳን ፋሲሎች በአጋማሹ ዕድሎችን ለመፍጠር ሙከራዎችን ሲያደርጉ የተመለከትን ቢሆንም አዳማዎች ግን በቁጥር በርከት ብለው ለመከላከል ሲያደርጉት የነበረው ጥረት እና ትጋት የሚደነቅ ነበር። በአጋማሹ በፋሲሎች በኩል የተሻለ የሚባሉት ሁለት ተከታታይ ሙከራዎች የተደረጉት በ42ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። በቅድሚያ አምሳሉ ጥላሁን ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም ካሻማው የቆመ ኳስ ያሬድ ባየህ ያደረገው ሙከራ በሳኩቡ ካማራ ሲድንበት ከተመለሰው ኳስ በረከት ደስታ ያሻማውን ኳስ አስቻለው ታመነ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ ወጥታበታለች።

ከዕረፍት መልስም በተመሳሳይ ይዘት በቀጠለው ጨዋታ 56ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ከመሀል ሜዳ አካባቢ ያሳለፈተለትን ድንቅ ኳስ ከተከላካዮች አፈትልኮ የወጣው ሙጂብ ቃሲም በመጀመሪያ ንክኪ ተንሸራቶ በማስቆጠር ውጥረት ውስጥ የነበሩትን የክለቡ ደጋፊዎች ወደ ተለየ የደስታ ስሜት ውስጥ መክተት የቻለችን ግብ አስቆጥሯል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ አሁን ሳይጣደፉ ጥቃቶችን መሰንዘራቸውን የቀጠሉት ፋሲሎች በተለይ በረከት ደስታ ከተሰለፈበት የግራ መስመር መነሻቸውን ያደረጉ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን መፈፀማቸውን የቀጠሉ ቢሆንም አጋጣሚዎቹን ወደ ግብነት መቀየር ግን ሳይችሉ ቀርተዋል። ግብ ካስተናገዱ ወዲህ በተወሰነ መልኩ ወደ ፊት ገፍተው ይጫወታሉ ተብለው የጠበቁት አዳማ ከተማዎች በ71ኛው ደቂቃ ከቆመ ኳስ መነሻውን ባደረገ ማጥቃት አዲስ ተስፋዬ ከቀኝ መስመር የሳጥን ጠርዝ ወደ ውስጥ ያሻማውን ኳስ ደስታ ዮሐንስ በግንባሩ ገጭቶ ሳማኬ ካዳነበት አጋጣሚ ውጪ ተጠቃሽ ሙከራዎችን ለማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። በፋሲል በኩል ግን ወደ ኢትዮጵያ ዳግም ከተመለሰ የመጀመሪያ ግቡን በጨዋታው ያገኘው ሙጂብ ቃሲም በ78ኛው ደቂቃ አምሳሉ ጥላሁን ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም ከቆመ ኳስ ያሻማውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት የቡድኑን መሪነት ማሳደግ ችሏል።

ከሁለተኛው ግብ መቆጠር በኋላ በነበሩት ደቂቃዎች አዳማ ከተማዎች የማጥቃት ኃይላቸውን ለማሻሻል አዎንታዊ ለውጦችን በማድረግ ጥረት ያደረጉ ሲሆን በአንፃሩ ፋሲሎችን እንዲሁ በተመሳሳይ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ቢያደርጉም ትኩረት የሚስቡ ሙከራዎችን ሳንመለከት ጨዋታውን ፍፃሜውን አግኝቷል።

ፋሲል ከነማዎች ድል ማድረጋቸውን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ 55 በማሳደግ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የነበራቸውን የሦስት ነጥብ ልዩነት ሲያስቀጥሉ በአንፃሩ ተከታታይ ሽንፈት ያስተናገዱት አዳማ ከተማዎች ደግሞ በ30 ነጥብ አሁንም 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።