በሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ አዲስ አበባ እና ኢትዮጵያ ቡና አቻ ሲለያዩ የወራጅ ቀጠናውም አዲስ ክለብ አግኝቷል።
በ26ኛ ሳምንት አዳማ ከተማ እና ወላይታ ድቻን በአንድ ጎል ልዩነት ያሸነፉት ቡና እና አዲስ አበባ ሦስት ነጥብ ካሳኩበት ፍልሚያ አንድም ተጫዋች ሳይቀይሩ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
በዝናባማ የዐየር ሁኔታ ሞቅ ብሎ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና በ2ኛው ደቂቃ አማኑኤል ዮሐንስ ለአቡበከር ናስር አመቻችቶለት ወጣቱ አጥቂ ለጥቂት ባመከነው ኳስ የመጀመሪያ ሙከራ አስተናግዶ ኢትዮጵያ ቡናን ቀዳሚ ሊያደርግ ነበር። ቀድሞ በተሰነዘረባቸው ሙከራ ያልተደናገጡት አዲስ አበባዎች በ11ኛው ደቂቃ ሪችሞንድ አዶንጎ ከፍፁም ጥላሁን ተቀብሎ ወደ ላይ በጎነው ኳስ አፀፋዊ ምላሽ ሰጥተው ተመልሰዋል።
የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው መንቀሳቀስ የያዙት ኢትዮጵያ ቡናዎች በጨዋታው ሩብ ደቂቃ አማኑኤል ከረጅም ርቀት መሬት ለመሬት በሞከረው ኳስ መሪ ለመሆን ጥረዋል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን እጅግ ለግብ የቀረበ ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል። በዚህም አዲስ አበባዎች ፍፁም ጥላሁን ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን የቅጣት ምት በሮቤል ግርማ አማካኝነት አሻምተውት አዩብ በቃተ በግንባሩ ሞክሮት የግቡ አግዳሚ መልሶታል።
በፍላጎት ደረጃ ከቡናማዎቹ የተሻሉት አዲስ አበቤዎች
ከውሀ እረፍት በኋላ ሌላ ጥቃት ልከው ነበር። በዚህም ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ፍፁም ዐየር ላይ የተላከለትን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ በደረቱ ተቆጣጥሮ በግራ እግሩ ቢመታውም የግብ ዘቡ በረከት አማረ እና የግቡ ቋሚ ተባብረው አምክነውበታል። እንደ አጀማመራቸው መዝለቅ ያልቻሉት ኢትዮጽያ ቡናዎች አጋማሹ ሊጠናቀቅ አስር ደቂቃዎች ሲቀሩት ግብ አስተናግደዋል። በዚህም በተደጋጋሚ የላይኛው የሜዳ ክልል በፈጣን ሽግግሮች እና ያልረዘሙ ቅብብሎች ሲደርሱት የነበሩት አዲስ አበባዎች ፍፁም አሻምቶት እንዳለ ከበደ በግንባሩ ከወራጅ ቀጠናው የሚያወጣቸውን ጎል አስቆጥሮላቸዋል። በቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎች ሌላ ሙከራ ሳይደረግ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተው የነበሩት ቡናማዎቹ ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ወዲያው ወደ ጨዋታው የሚመለሱበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። በዚህም አቡበከር ናስር ራሱ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የፍፁም ቅጣት ምት በጥሩ መረጋጋት ወደ ግብነት ቀይሮታል።
ወደ ጨዋታው የተመለሱት የአሠልጣኝ ካሣዬ አራጌ ተጫዋቾች ግብ ካገኙ ከደቂቃዎች በኋላም በአስራት ቱንጆ አማካኝነት እጅግ ስል ሙከራ አድርገው ነበር። በእጃቸው የነበረው ሦስት ነጥብ በአቻነቱ ግብ ያመለጣቸው አዲስ አበባዎች በሪችሞንድ ሁለት ኳሶች ዳግም ወደ መሪነግ ሊሸጋገሩ ነበር። በተለይ በ56ኛው ደቂቃ ፍፁም ከሳጥን ውጪ አጥቦ በመግባት የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው በረከት ሲመልሰው አግኝቶ የመታው ኳስ ለግብ የቀረበ ነበር።
አቻ ያረጋቸውን አቡበከር ያማከለ አጨዋወት መከተል የቀጠሉት ቡናዎች በ70ኛው ደቂቃ ተጫዋቹ ከተከላካዮች አፈትልኮ ወጥቶ ጥሩ ሙከራ አድርጎላቸዋል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከጨዋታው የሚገኘውን የተሻለ ነጥብ ለማግኘት መጣር የያዙት አዲስ አበባዎች ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን ቢፈጥሩም ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። በተለይ ግብ ጠባቂው በረከት ኳስ ለማፅዳት መውጣቱን ተከትሎ ከርቀት ኤሊያስ የሞከረው እንዲሁም ይሁ ተጫዋች በተከላካዮች መከከል ተቀይሮ ወደ ሜዳ ለገባው መሐመድ አበራ ላኮ ግብ ጠባቂው ክልሉን በድጋሜ ለቆ ያመከነው አጋጣሚ ቡድኑን አሸናፊ ሊያደርጉ የተቃረቡ ነበሩ። በሁለቱ የመዲናይቱ ክለቦች የተደረገው ጨዋታም ሌላ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን 41 በማድረስ የነበረበት 5ኛ ደረጃ ላይ ፀንቶ ሲቀመጥ ዘለግ ላሉ ቀናት በወራጅ ቀጠናው የከረመው አዲስ አበባ ከተማ ግን ነጥቡን ወደ 29 አሳድጎ ቦታውን ለድሬዳዋ ከተማ አስረክቧል።