ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

ሦስተኛው የትኩረታችን ክፍል ደግሞ አሰልጣኞች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ይሆናል።

👉 የዮሐንስ ሳህሌ ግልፅነት የተሞላበት አስተያየት

በድህረ ጨዋታ ቃለ መጠይቆች ወቅት የሀገራችን አሰልጣኞች በአብዛኛው በግልፅነት ሀሳቦችን ከመስጠት ይልቅ በተድበሰበሰ መልኩ ነገሮችን አለባብሰው ማለፍ የተለመደ መንገድ ነው።

ነገር ግን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት መከላከያ ከወላይታ ድቻ ካለ ግብ በአቻ ውጤት ከፈፀሙት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ለወትሮውም ቢሆን በግልፅነት ሀሳብ ለመስጠት ችግር የሌለባቸው አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በግልፅነት የሰነዘሩትን አስተያየት አድምጠናል።

በቀጣይ ቡድኑ ስለሚጠብቁት ቀሪ ሦስት ጨዋታዎች እና በሊጉ ለመቆየት ቡድናቸው ስላለው ዕድል የተጠየቁት አሰልጣኙ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

“ላለመውረድ ጥረት የሚጀመረው ገና ከመጀመሪያው ጨዋታ ነው ፤ አሁን ወደ መጨረሻው ያለው ነገር ለመትረፍ እንጂ ላለመውረድ አይደለም።”

“…..ስለዚህ ማድረግ የሚገባን የራሳችንን ስራ ሰርተን ቡድናችንን በሊጉ ማቆየት ነው እንጂ በሁለተኛው ዙር የምታደርገው የትኛውም ጨዋታ በጣም ወሳኝ ነው ፤ እኛም ሆነ ሌሎች ቡድኖች መጀመሪያ ጨርሰን መጥተን ቢሆን ኖሮ እዚህ ነገር ውስጥ አንገባም ነበር።”

“ሊጉ ደስ የሚል ሂደት ላይ ይገኛል እናንተም እንደምትሉት አብዛኞቹ አሰልጣኞች እኔንም ጨምሮ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ላይ ሆነን ሳንተኛ ቁጭ ብለን ነጥብ ስንደምር እና ስንቀንስ አያደርን ነው።”

አሰልጣኙ በአስተያየታቸው በዚህ ወቅት በወራጅ ቀጠናው ውስጥ እና በአካባቢው
በመገኘታቸው ከፍተኛ ስጋት የተጋረጠባቸው ቡድኖች አሰልጣኞች እያሳለፉት ስለሚገኙት አስቸጋሪ ጊዜ በዚህ መልኩ በግልፅነት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

የመከላከያው አሰልጣኝ ይህን ይበሉ እንጂ ሁሌም ቢሆን አነጋጋሪ ሀሳቦችን በመናገር የሚታወቁት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ለዚህ ሀሳብ ምላሽ ሰጥተዋል ፤ አሰልጣኙ ሲናገሩም “ለምንድነው እንቅልፍ የማጣው ? በታሪክ እንቅልፍ የሚያሳጣኝ የለም፡፡ ገምቶ የመጣ ሰው እንቅልፍ ሊያጣ ይችላል፡፡ እኔ በመሀል መጥቻለሁ ፣ ይሄን ቡድን አቀናጅቼ በፕሪምየር ሊጉ እዛው እንዲቆይ ለማድረግ ነው እንደውም ዘና ብዬ እንቅልፍ ሰዓቴን ጨምሪያለሁ፡፡” ሲሉ ተደምጠዋል።

👉 ካሳዬ አራጌ እና የክለቡ ቦርድ

በ2011 ክረምት ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከተመለሰ ወዲህ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በሂደት ከክለቡ አመራሮች ጋር ያለው ግንኙነት የላላ ይመስላል።

ከተጫዋቾች ምልመላ ጋር በተያያዙ ጉዳዮችም ሆነ ከምክትል አሰልጣኝ ምርጫ ጋር በሚገናኙ ጉዳዮች በአሰልጣኙ እና የክለቡ አመራሮች መካከል ልዩነቶች ስለመኖራቸው በስፋት ሲነገር የቆየ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ካደረገው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኙ የሰጠው አስተያየት ይህን ጥርጣሬ ይበልጥ የሚያረጋግጥ ይመስላል።

ከአዲስ አበባ ከተማው ጨዋታ በኋላ ወደ ደቡብ አፍሪካው ክለብ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የሚያደርገውን ዝውውር ለማጠናቀቅ የቡድን ስብስብ ለቆ ወደ አዲስ አበባ ስለሚያቀናው አቡበከር ናስር እና እሱን ሰለተመተካት ሂደት የተጠየቀው አሰልጣኙ ይህን ብሏል።

“ለእኔ ግልፅ የሆነ ነገር የለም፡፡ እስከ አሁን ድረስ ግልፅ የሆነ ከክለቡ ጋር በምን ዓይነት መልኩ ነው የሚሄደው የሚለው እስከ ስንት ጨዋታ ድረስ እኛ ጋር ይቆያል ስለሚለው ጉዳይ የማውቀው ነገር ስለሌለ ምንም ማለት አልችልም፡፡”

ከዚህ ቀደምም ተጫዋቹ በሊጉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲያመራም አሰልጣኙ በተመሳሳይ መልኩ ከክለቡ አመራሮች በግልፅ የደረሰው ነገር እንደሌለ ሲናገር ያደመጥን ሲሆን አሁን ላይ ደግሞ ከላይ የጠቀስነውን ሀሳብ መስጠቱ በሁለቱ አካላት መካከል ስላለው ግንኙነት የሚነገረን ነገር ይኖራል።

ታዲያ በዚህ ከመተማመን ይልቅ በጥርጣሬ የተሞላ በሚመስለው የስራ ከባቢ በሁለቱ አካላት መካከል በመሰል ዝርዝር ጉዳዮች ዙሪያ መናበብ አለ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። መቼም ለኢትዮጵያ ቡና በዚህ ወቅት ከአቡበከር ናስር በላይ አንገብጋቢ ጉዳይ አለ ብሎ ለመውሰድ በሚያስቸግርበት በዚህ ወቅት በሁለቱ አካላት መካከል ቀጥተኛ የመረጃ ልውውጥ አለመኖሩ ግን በጣም የሚያስገርም ነው።

👉 “እኔ ግማሽ ላይ ነው የመጣሁት…”

ለአንድ አሰልጣኝ በሚፈልገው መንገድ ቡድኑን እንዲገነባ ቢያንስ ሙሉ የቅድመ ውድድር ጊዜ እና የተሟላ የዝውውር መስኮት በትንሹ ስለማስፈለጉ ምንም ጥርጥር የሌለው ጉዳይ ነው።

ታድያ ይህ እውነታ እንዳለ ሆኖ በውድድር ዘመን አጋማሽ ቡድኖችን በተለይ በአሁን ወቅት ላለመውረድ እየተጫወቱ የሚገኙ ቡድኖችን የተረከቡ አሰልጣኞች ከጥቂት ሳምንታት በፊት ስለለወጡት ነገር ሲዘረዝሩ ቢቆዩም አሁን ላይ በተወሰነ መልኩ ውድድር መሀል ላይ መምጣታቸውን እንደማምልጫ የመጠቀም ሙከራዎችን እየተመለከትን እንገኛለን።

ከአዲስ አሰልጣኝ ቅጥር ጋር ተያይዞ የሚኖረውን መነቃቃት (New Manager Bounce) ወቅት ቡድኑን ‘በዚህ በዚህ ረገድ አሻሽለናል’ ብለው አድናቆቶችን በሙሉ ሲጠቀልሉ ከነበሩት አሰልጣኞች የተወሰኑት አሁን ላይ ውጤት ጠፋ ሲል ‘እኛ በአጋማሽ ስለመጣን’ የሚል ማምለጫ መንገድ ለማዘጋጀት ጥረት እያደረጉ ይገኛል።

በውጤት ማጣት ውስጥ የነበረውን ክለብ አሰልጣኞቹ ሲረከቡ በቀጣይ የሚኖሩ ውጤቶች በሁለቱ ፅንፍ ሊሄዱ እንደሚችሉ አምነው እንደመሆኑ አውንታዊ ውጤቶችን ተከትሎ ተፅዕኗቸውን ለማጉላት እና መወድስ ለማግኘት እንደሚሽቀዳደሙት ውጤት ሲጠፋም በቅድሚያ ትችቱን መቀበል ሲገባቸው ፤ ውጤት ሲመጣ ‘እኔ’ ማለት በአንፃሩ ሲጠፋ ሌሎች ላይ ጣት መቀሰር እና ‘እኔ በዚህ ጊዜ ስለመጣሁ…’ የሚለውን አካሄድ መምረጥ ውሃ የሚያነሳ አይደለም።