ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የመጨረሻው ፅሁፋችን ደግሞ በዚህኛው ሳምንት ያስተዋልናቸው ሌሎች ትኩረት የሚስቡ ጉዳዮች የቀረቡበት ነው።

👉 ድንቅ ግቦች የተቆጠሩበት ሳምንት

በ27ኛ የጨዋታ ሳምንት በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች መካከል ሁለት በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ለዓመቱ ምርጥ ግብ መፎካከር የሚችሉ ግቦች የተመለከትንበት ነበር።

ሀዋሳ ከተማ ባህር ዳር ከተማን 2-0 በረታበት ጨዋታ ላይ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ‘አዲሱ አቡበከር ናስር’ ሲሉ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ያሞካሹት ብሩክ በየነ በግራ የሳጥን ጠርዝ ያገኘውን ኳስ ተረጋግቶ አንድ የባህር ዳር ተጫዋች አልፎ በግሩም ሁኔታ ከሳጥን ጠርዝ ወደ ግብ ሲልካት የቀኙን የግቡ አግዳሚ ለትማ ከመረብ የተዋሀደችበት መንገድ እጅግ አስደናቂ ግብ አድርጓታል።

በተመሳሳይ ሲዳማ ቡና ጅማ አባ ጅፋርን በረታበት ሌላው የጨዋታ ሳምንቱ መርሃግብር እንዲሁ አንጋፋው አጥቂ ሳልሀዲን ሰዒድ ከርቀት ያገኘውን የቆመ ኳስ አጋጣሚ በግሩም ሁኔታ አክርሮ በመምታት ከመረብ ያዋሀደበት መንገድ እንዲሁ ትኩረት የሚስብ ነው።

ብዙዎች ገና የውድድር ዘመኑ ሳይጠናቀቅ ከወዲሁ የኢትዮጵያ ቡና አማካይ ሮቤል ተክለሚካኤል ሰበታ ከተማ ላይ ከመሀል ሜዳ ያስቆጠራት ግብ የውድድር ዘመኑ ምርጥ ግብ ትሆናለች እያሉ ቢገኙም በዚህ ሳምንት የተመለከትናቸው ሁለቱ ግቦች ግን ለውድድር የሚበቁ ይመስላል።

👉 የተሻለው ነገር ግን ሥራዎች የሚፈልገው የባህር ዳር ስታዲየም የፍሳሽ አወጋገድ

የክረምቱ ወቅት እየገባ እንደመገኘቱ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ በመጣል ላይ ይገኛል። ታድያ ዝናብ እና የሀገራችን ስታዲየሞች የመጫወቻ ሜዳዎች ነገር ደግሞ ላለመታረቅ ቃል ያላቸው እስኪመስል ዝናብ በጣለ ቁጥጥር መሳቀቃችን ቀጥሏል።

በባህር ዳር ስታዲየም ላይ እየተደረገ በሚገኘው የሊጉ ውድድር በ27ኛ የጨዋታ ሳምንት እንኳን ወላይታ ድቻ ከመከላከያ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ያደረጓቸው ጨዋታዎች በከፍተኛ ዝናብ ታጅበው የተደረጉ ነበሩ። በዚህ ወቅት ጨዋታዎችን እያስተናገደ የሚገኘው የባህር ዳር ስታዲየም ግን ከሌሎች የሀገራችን የመጫወቻ ሜዳዎች ፍፁም የተሻለ የውሃ አወጋገድ ስርዓት ባለቤት መሆኑን በሚገባ እየተመለከትን እንገኛለን።

በዝናብ ወቅት ሆነ ቀጥሎ በሚኖሩ ጊዜያት ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን እያስተናገደ የሚገኘው ሜዳው በሁለቱ ግቦች ትይዩ ባለው የሜዳ ክፍል በመጠኑ የመበላሸት ምልክቶችን ከማሳየት ውጭ ፍፁም በተሻለ አቅም ጨዋታዎችን እያስተናገደ ይገኛል።

ከዚህ አንፃር ዝናብ በጣለ ቁጥር ረግረጋማ ገፅታን ከሚላበሱት አብዛኞቹ የሀገራችን ስታዲየሞች አንፃር የተሻለ እንደሆነ ዳግም ያስመሰከረው የባህር ዳር ስታዲየም አሁንም መጫወቻ ሜዳውን ለዓለምዓቀፍ ውድድሮች በሚበቃ መልኩ ዝግጁ ለማድረግ የፍሳሽ አወጋገዱም ሆነ አጠቃላይ የመጫወቻ ሜዳው ነገር ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራበት ይገባል።

👉 የሜዳ ጠርዝ ማስታወቂያዎች ተጫዋቾችን ለጉዳት…

ሊጉ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን ማግኘቱን ተከትሎ ከዚህ ቀደም በአንዳንድ ሜዳዎች አለፍ አለፍ ብለው ተቀምጠው እንመለከታቸው የነበሩ የሜዳ ጠርዝ ማስታወቂያዎች አሁን ላይ በስፋት እየተመለከትናቸው እንገኛለን።

በተለይም ከቴሌቪዥን ስርጭቱ ትሩፋት ለመቋደስ ተቋማት ይበልጥ ራሳቸው ለመሸጥ በሜዳው ጠርዝ መልእክቶቻቸውን እያስቀመጡ ይገኛል። ታድያ በዚህ ሂደት ግን ለዚህ አግልግሎት ተብለው የተቀመጡት እና ከብረት መዋቅር የተሰሩት የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ተጫዋቾች ላይ ጉዳት እያደረሱ ይገኛል።

በቅርብ ሳምንታት ውስጥ እንኳን ጅማ አባ ጅፋር ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ የአዲስ አበባው የመስመር ተከላካይ የሆነው ሮቤል ግርማ በሁለተኛው አጋማሽ እግሩ እዚህ ማስታወቂያ ሰሌዳ ውስጥ መግባቱን ተክሎ ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ ለመውጣት የተገደደ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማው አማካይ ሙሉቀን አዲሱም እንዲሁ ከቡድን አጋሩ የደረሰውን ኳስ ለመቆጣጠር ባደረገው ጥረት መጠነኛ ጉዳት አስተናግዶ ከጉዳት ጋር ሆኖ ጨዋታውን ለመጨረስ መገደዱን ተመልክተናል።

ለአብነት እነዚህን ሁለት አጋጣሚዎችን አነሳን እንጂ በሊጉ 27 የጨዋታ ሳምንታት ጉዞ ውስጥ እንዲሁ በርከት ያሉ መሰል አጋጣሚዎችን ተመልክተናል። በመሆኑም እነዚህ ሰሌዳዎች የሚቀመጡበት ቦታ ሆነ የሚሰሩበት ቁስ ላይ ጥንቃቄዎች ሊደረጉ እንደሚገባ የጠቆሙ አጋጣሚዎች ሆነው አልፈዋል።

👉 ደግአረግ ይግዛው በጨዋታ ተንታኝነት

የቀድሞው የወልቂጤ ከተማ እና በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ደግሞ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተካፋይ የነበረውን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በዋና አሰልጣኝነት የመራሩት ደግአረግ ይግዛው በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ወልቂጤ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያረጉትን ጨዋታ በሱፐር ስፖርት በተንታኝነት አቅርበዋል።

አምና በተወሰነ መልኩ ተጀምሮ የነበረው እና ዘንድሮ ደግሞ በስፋት እየተመለከትነው እንደምንገኘው የቀድሞ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች በሱፐር ስፖርት የቀጥታ የጨዋታ ስርጭቶች ላይ በተንታኝነት የመቅረባቸው ጉዳይ አሁን ከዚህ በተሻለ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ልምምድ ነው።

👉 የጌታነህ ከበደ ውዝግብ

በጨዋታ ሳምንቱ አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች ቀዳሚው የነበረው የጌታነህ ከበደ ጉዳይ ነበር።

በ25ኛ የጨዋታ ሳምንት ወልቂጤ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ካደረጉት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የጨዋታ አመራሮችን በንግግር ዘልፏል በሚል በቀረበበት ክስ የሦስት ጨዋታዎች ዕገዳ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም ለፌደሬሽኑ የፍትህ አካላት ባቀረበው አቤቱታ ውሳኔ ቢቀለበስም ሂደቱ በፌደሬሽኑ እና በሊጉ እክሲዮን ማህበር መካከል መቃቃርን የፈጠረ ነበር።

ክለቡ የፌደሬሽኑ ውሳኔ ገዢ መሆኑን ጠቅሶ ጌታነህም በጊዮርጊሱ ጨዋታ እንዲሰለፍ ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም በክለቡ በኩል የተሰጠን አቅጣጫ አላስፈፀሙም በሚል የክለቡ የቡድን መሪም እንዲሁ ከክለቡ የተሰናበቱበት አጋጣሚም ተፈጥሯል። በሌላ በኩል አክሲዮን ማህበሩ የፌዴሬሽኑን ውሳኔ መልሶ መቀልበሱን ተከትሎ ፌዴሬሽኑ ሰጥቶት የነበረው የሲስፕሊን ጉዳዮችን የመመልከት ኃላፊነትን መልሶ ወስዷል።

በሁለቱ አካላት መካከል ባለፉት ሁለት ዓመታት ጤናማ የስራ ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን የጌታነህ ከበደ ጉዳይ በሁለቱ አካላት መካከል መቃቃርን የፈጠረ ሆኗል። ከዚህ ሂደት ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ብዥታ ለማጥራት አክሲዮን ማህበሩ ትላንት ጋዜጣዊ መግለጫ ጠርቶ የነበረ ቢሆንም በድጋሚ መግለጫውን ላልተወሰነ ጊዜ አስተላልፎታል። እጅግ ሲያወዛግብ የሰነበተው ይህ ጉዳይ እስካሁን መቋጫ ያላገኘ ሲሆን በቀጣይ ሂደቱ ወዴት ያመራል የሚለው ነገርም ይጠበቃል።

ያጋሩ