የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 0-2 ፋሲል ከነማ

ሙጂብ ቃሲም በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆራቸው ሁለት ግቦች ፋሲሎች በፉክክሩ መቆየታቸውን ያረጋገጡበትን ውጤት ካስመዘገቡበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሁለቱ አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ

ስለጨዋታው

“የመጀመሪያው አጋማሽ በፈለግነው መንገድ የሄደ ነበር ነገርግን በሁለተኛው አጋማሽ ግን የተወሰኑ መዘናጋቶች ነበሩ ፤ እነሱም ያገኙትን አጋጣሚዎች መጠቀማቸው ውጤታማ አድርጓቸዋል።”

ለመከላከል ቅድሚያ መስጠታቸው ዋጋ ስላስፈለጋቸው

“ከመሰል ተጋጣሚ ጋር ስትጫወት ጥንቃቄ ማድረግ የሚጠበቅ ነው ግን በጥንቃቄ ውስጥ ሆነን የፈጠርናቸው እድሎችን መጠቀም አለመቻላችን ዋጋ አስከፍሎናል።”

ሁለተኛው ግብ ካስተናገዱ በኃላ በማጥቃቱ ረገድ ስለመሻሻላቸው

“ግብ ካገቡብን ወዲህ ወደ እነሱ ሜዳ ገብተን ለመጫወት ችለን ነበር ፤ ይህንን ከመጀመሪያው ማረግ እንችል ነበር እነሱ በረጃጅም በሚጣሉ ኳሶች ከጀርባ ለመሄድ ይሞክሩ ነበር በመሆኑም ይህን ተጠንቅቀን ይበልጥ ማጥቃት ይገባን ነበር።”

ስለቀጣይ ጨዋታዎች

“ተጋጣሚዎችን እኛ አካባቢ ያሉ እንደመሆናችን ተጠንቅቀን ለመጫወት እንሞክራለን ፤ ከአጥቂዎችን ጋር በተለይ ከጉጉት የመጣ የሚባክኑ ኳሶች ስላሉ ትንሽ ተረጋግተው እንዲያስቡ መነጋገር ይኖርብናል።”

አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ – ፋሲል ከነማ

ስለጨዋታው

“ወደ ኋላ ሸሽተው እንደሚጫወቱ ገምተን ነበር ፤ ግን ይህን እንዴት ማስከፈት እንደሚገባን ተነጋግረን ነበር በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ነበርን ብዬ አስባለሁ።”

በመጀመሪያው አጋማሽ ስለነበራቸው የማጥቃት አፈፃፀም ድክመት

“ጭንቀት አልፈጠረብንም ፤ ጊዜው ቢገፋም ማስቆጠር እንደምንችል እርግጠኛ ነበርን አደጋ የነበረው እኛ ላይ ግብ እንዳይቆጠርብንም መጠበቅ ነበረብን።”

ስለሙጂብ ቃሲም የዕለቱ ብቃት

“ሲመጣ የጨዋታ ዝግጁነቱ ጥሩ አልነበረም ፤ ነገርግን ወደ ባህር ዳር ከመጣን ወዲህ ግን እንቅስቃሴው ጥሩ ነው በቀጣይም ከዚህ በላይ ይሻሻላል ብዬ እጠብቃለሁ።”

ስለቡድኑ እድገት

“ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በምፈልገው መልኩ እያደግን ነው ብዬ አስባለሁ።”