ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

ቀጣዩ ትኩረታችን ደግሞ በጨዋታ ሳምንቱ ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች ላይ ያሚነሱ ሀሳቦች የተዳሰሱበት ነው።

👉 በወሳኝ ሰዓት የተገኘው ሙጂብ ቃሲም

ወደ ኢትዮጵያ ዳግም ከተመለሰ ወዲህ በቀደመው ደረጃ ፋሲልን እየረዳ አይገኝም በሚል ወቀሳ ሲቀርብበት የነበረው ሙጂብ ቃሲም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ቡድኑን ታድጓል።

በውድድር ዘመኑ የአዳማውን ጨዋታ ሳይጨምር በስድስት ጨዋታዎች በድምሩ ለ480 ያህል ደቂቃዎች ተሰልፎ መጫወት የቻለው ሙጂብ ከአጥቂነት ባለፈ በተለያዩ ሚናዎች ማለትም በመሀል ተከላካይነትም ሆነ በአማካይነት ግልጋሎት ሲሰጥ ያስተዋልን ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ቡድኑ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለመቀጠል እጅግ አስፈላጊ የነበረውን ጨዋታ በድል እንዲወጣ ያስቻሉ ወሳኝ ሁለት ግቦችን አስገኝቷል።

በጨዋታው በግሉ ብዙ ሲጥር የነበረው ሙጂብ በሁለተኛው አጋማሽ 56ኛው ደቂቃ ላይ ከሱራፌል ዳኛቸው የደረሰውን ኳስ እንዳገኛት በአስገራሚ አጨራረስ ያስቆጠረ ሲሆን በተመሳሳይ በ78ኛው ደቂቃም እንዲሁ ከቅጣት ምት የተሻማለትን ኳስ በግንነባሩ በመግጨት ድንቅ ኳስ አስቆጥሯል። በዚህም ፋሲል ከነማዎች በሙጂብ ሁለት ግቦች ታግዘው አዳማን 2-0 በመርታት ከመሪው ያላቸውን የ3 ነጥብ ልዩነት አስጠብቀው መቀጠል ችለዋል።

ግብ ሳያስቆጥር የቆየው ሙጂብ በተለይ አዳማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ጠንካራ የመከላከል እንቅስቃሴ ማሳየታቸውን ተከትሎ ውጥረት ውስጥ የነበረው ቡድን ወሳኝ ነጥብ እንዲያገኝ በማስቻል በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ሁለት ግቦችን በፋሲል መለያ ማስቆጠር ችሏል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ግንቦት 9 በ24ኛ የጨዋታ ሳምንት ፋሲል ከነማ በድሬዳዋ ከተማ ያልተጠበቀ የ3-1 ሽንፈት ሲያስተናግድ በ26ኛው ደቂቃ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገችውን ግብ ያስቆጠረው ሙጂብ በዚህ ሳምንት ያስቆጠራቸው ጎሎች በፋሲል ከነማ መለያ ከአንድ ዓመት ከሚልቅ ጊዜ በኋላ ያስመዘገባቸው የመጀመሪያ ግቦች ሆነዋል።

👉 ወሳኝ ግቦችን ማምረቱን የቀጠለው ከነዓን ማርክነህ

አጥቂዎቻቸውን በተደጋጋሚ ጉዳት እያጡ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ግብ ማግኘት በመቻላቸው ፈታኙን ጊዜ እየተወጡት ይገኛል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ወልቂጤ ከተማን ሲረታ ሁለቱም የማሸነፍያ ግቦች የተቆጠሩት ከአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ የአማካዩ ከነዓን ማርክነህ አበርክቶ እጅግ የላቀ ነበር።

በሊጉ በ18 ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ ማድረግን የቻለው ከነዓን ማርክነህ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ወልቂጤ ከተማ ላይ ያስቆጠራትን ግብ ጨምሮ በስድስት ግቦች ከእስማኤል ኦሮ-አጎሮ ቀጥሉ የቡድኑ ሁለተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ለመሆን በቅቷል። በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ባህር ዳር ከተማ እና ወልቂጤ ላይ ግቦችን ያስቆጠረው ከነዓን እነዚህን ጨዋታዎችን ጨምሮ አዳማ ከተማን 1-0 ሲረቱ ወሳኟን የማሸነፊያ ግብ እንዲሁም ሀዋሳን 3-0 ሲረቱ ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ ጨምሮ ለቡድኑ በወሳኝ ሰዓት መፍትሄ እየሰጠ ይገኛል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ሁለት ብቻ ግቦችን ያስቆጠረው ከነዓን በብዙ መመዘኛዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ ምርጡን ጊዜ እያሳለፈ የሚገኝ ሲሆን ከሚታወቅበት ለአጥቂዎች ቀርቦ ከሚያደገው እንቅስቃሴ እና በግሉ በአንድ ለአንድ ግንኙነት ተጫዋቾችን በመቀነስ ረገድ ካለው ጥሩ ብቃት ባለፈ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ደግሞ በአየር ላይ ኳሶች አጠቃቀም እና በግብ ማግባቱ ረገድ ፍፁም ተሻሽሎ ቀርቧል።

👉 በተለየ ገፅታ ብቅ ያለው መክብብ ደገፉ

በ23ኛ የጨዋታ ሳምንት ሲዳማ ቡና በመከላከያ ያልተጠበቀ የ5-3 ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታ የመጀመሪያ ተመራጭ ግብ ጠባቂ የነበረው ተክለማርያም ሻንቆ የሰራቸውን ስህተቶች ተከትሎ ወደ ተጠባባቂ ወንበር በመውረዱ መክብብ ደገፉ በምትኩ ተሰልፎ እየተጫወተ ይገኛል።

አራተኛ ጨዋታውን በዚህኛው ሳምንት ያደረገው መክብብ ደገፉ በተለየ ገፅታ ብቅ ብሏል ፤ ለወትሮው በሚታወቅበት የፀጉር እና የፂም አቆራረጥ የቀጠለው ተጫዋቹ ፂሙን እና በታችኛው የጭንቅላት ክፍሉ ላይ ያለውን ፀጉሩን ቡኒ ቀለም ተቀብቶ ባልተለመደ ገፅታ ተመልክተነዋል።

በአዲስ ገፅታ ብቅ ባለበት ጨዋታ መክብብ ቡድኑን ለድል ያበቁ ወሳኝ ኳሶችን በማዳን አስደናቂ የጨዋታ ዕለትን እንዲሁ ማሳለፍ ችሏል።

👉 የሰዒድ ሀብታሙ የጊዜ አጠባበቅ ስህተቶች

በዘንድሮው የውድድር ዘመን የሲልቪያን ግቦሁን በአበረታች ቅመሞች ሳቢያ መታገዱን ተከትሎ ወደ መጀመሪያ ተመራጭነት የመጣው ሰዒድ ሀብታሙ በወልቂጤ መለያ 16 ጨዋታዎች አድርጓል።

በዚህ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 ሲረቱ የመጀመሪያዋ ግብ ስትቆጠር ሰዒድ በቅድሚያ የተሻማውን የማዕዘን ምት ኳስ ለማቋረጥ በተሳሳተ የጊዜ አጠባበቅ ግቡን ለቆ የወጣ ሲሆን በዚህም ኳሷን ማግኘት ሳይችል ቀርቶ ኳሷ በአማኑኤል ተገጭታ የግቡን አግዳሚ ለትማ ስትመለስ እንዲሁ ከቡድን አጋሩ ዮናስ በርታ ጋር ባለመናበብ መቆጣጠር ያልቻለው ኳስ ወደ ግብነት ተቀይሯል።

ከዚህ አጋጣሚ በተጨማሪ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ግብ ጠባቂው በተሳሳተ የጊዜ አጠባበቅ ግቡን ለቆ ከወጣ በኋላ በሚወስናቸው የተሳሳቱ ውሳኔዎች ቡድኑ ዋጋ ሊከፍልባቸው የተቃረበባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ታድያ ይህ ሂደት በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ብቻ የተከሰተ ሳይሆን በሌሎችም ጨዋታዎች ላይ ቁጥራቸው ይለያይ እንጂ ተመሳሳይ ስህተቶችን ሲፈፅም እያስተዋልን እንገኛለን። ምናልባት ከእንቅስቃሴ ርቆ ወደ ጨዋታ እንደመመለሱ በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት እነዚህ ስህተቶች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ቢጠበቅም በተከታታይ ጨዋታዎች የመሰለፍ ዕድሎችን እያገኘ በሚገኝበት በዚህ ወቅት መሰል አጋጣሚዎች መደጋገማቸው በግብ ጠባቂው ላይ ጥያቄ እንዲነሳ የሚያስገድድ ነው።

👉 እየተሻሻለ የሚገኘው እንዳልካቸው መስፍን

በዘንድሮው የውድድር ዘመን በአርባምንጭ ከተማ መለያ በ26 ጨዋታዎች በድምሩ 2189 ደቂቃዎችን ተሰልፎ በመጫወት ቀዳሚው ተጫዋች የሆነው ወጣቱ አማካይ እንዳልካቸው መስፍን በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች አዲሱ ሚናው ይበልጥ የተመቸው ይመስላል።

በቀደሙት ጊዜያት በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በመሀል አማካይነት ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው እንዳልካቸው ከቅርብ ጨዋታዎች ወዲህ ግን በፊት አጥቂነት ጨዋታውን ለሚጀምረው አህመድ ሁሴን ይበልጥ ቀርቦ እንዲጫወት እየተደረገ ይገኛል በዚህም ከኳስ ጋር እና ከኳስ ውጭ ለቡድኑ የሚሰጠው አበርክቶ እያደገ ይገኛል።

ከኳስ ውጭ ከአህመድ ሁሴን ጋር በመሆን የቡድኑን የመጀመሪያ የጫና መስመር በመምራት እና በአንዳንድ አጋጣሚዎች ደግሞ ወደ ኋላ በጥልቀት እየተሳበ በቀደመው ሚናው የቡድን አጋሮቹን ከማገዝ ባለፈ ቡድኑ ኳስ በሚይዝበት ወቅት ደግሞ ለአጥቂዎች የተመጠኑ ኳሶችን በማድረስ ለግቦች መቆጠር ምክንያት እየሆነ ይገኛል። በዚህም ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ሲዳማን ሲረታ ኤሪክ ካፖይቶ ላስቆጠራት ግብ ግሩም ተንጠልጣይ ኳስ አመቻችቶ ያቀበለ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ አህመድ ሁሴን ድሬዳዋ ከተማ ላይ ላስቆጠራት የመጀመሪያ ኳስ ከቆመ ኳስ በግሩም ሁኔታ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

ብዙዎች እንደ ወንድው ጥሩ የተከላካይ አማካይ አድርገው ቢያስቡትም እንዳልካቸው ግን ወደ ፊት በተጠጋው አዲሱ ሚናው የተሻለ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

👉 ማማዱ ሲዲቤ ምን ነካው ?

ምናልባት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ወደ ሀገራችን ከመጡ ስፍር ቁጥር ከሌላቸው የውጭ ሀገር ዜግነት ካላቸው ተጫዋቾች መካከል የተሻለ ነገር ማበርከት ከቻሉት አንዱ የነበረው ማማዱ ሲዲቤ ዘንድሮ ግን ፍፁም ደካማ ጊዜያትን በድሬዳዋ ከተማ እያሳለፈ ይገኛል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን በአጠቃላይ በ18 ጨዋታዎች በድምሩ ለ1371 ያህል ደቂቃዎች ተሰልፎ መጫወት የቻለው ማሊያዊው አጥቂ በአጠቃላይ እስካሁን አራት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረ ሲሆን እነዚህም በሁለት ጨዋታዎች ማለትም 3ኛ ሳምንት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ አንድ እንዲሁም በ4ኛ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር ላይ ሐት-ትሪክ ከሰራበት ወዲህ እጅግ የተቀዛቀዘ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል።

ምናልባት ከተጫዋቾች የአቋም መውረድ ጋር ተያይዞ ስለ መጫወቻ ቦታ እና ስለ ቡድኑ የአጨዋወት መንገድ ያለመመቸት እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች የሚነሱ ቢሆንም በማማዱ ሲዲቤ ላይ ከእነዚህ ሁሉ ጉዳዮች የሚልቀው እና መሰረታዊ የሆነው የፍላጎት ማጣትን እየተመለከትንበት እንገኛለን።

እርግጥ በጅማ እና በባህር ዳር የተሳኩ ጊዜያትን ያሳለፈው ይህ ማሊያዊ አምና በሲዳማ ቡና ቤት እንዲሁ ቀዝቀዛ አጀማመር ቢያደርግም በተለይ በሁለተኛው ዙር ከኦኪኪ አፎላቢ መምጣት በኋላ በንፅፅር የተሻሉ ጊዜያትን አሳልፎ የውድድር ዘመኑ ሲጠናቀቅ ስድስት ግቦችን ማስቆጠር ቢችልም በተመሳሳይ ዘንድሮም ወደ ድሬዳዋ ከመጣ ወዲህ በወጥነት ቡድኑን ማገልግል እየቻለ አይገኝም።

የዘንድሮው የውድድር ሲጀመር በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት ጥሩ መንቀሳቀስ እና ግቦችን ማስቆጠር ችሎ የነበረው ተጫዋቹ በሂደት የመጀመሪያ ተሰላፊነቱን ለሄኖክ አየለ አስረክቦ ወደ ተጠባባቂ ወንበር ለመውረድ የተገደደ ሲሆን ወደ ሜዳ በሚገባባቸው አጋጣሚዎችም እንዲሁ የመጫወት ፍላጎቱ እንደሌለው የሚያሳብቁ ሂደቶችን እየተመለከትን እንገኛለን።

ምናልባት ይህ ተጫዋች እንደ አብዛኛዎቹ ወደ ሀገራችን እንደሚመጡ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ጥሩ ነገር አበርክተው በቀጣይ ዓመታት ግን ስማቸውን እና የቀደመ አበርክቷቸውን ብቻ ተጠቅመው ረብጣ ዶላሮችን ወደ ካዝናቸው እንደሚያስገቡት ተጫዋቾች ተቀይሮ ይሆን የሚለው ጉዳይ ትኩረት የሚስብ ነው።

👉 አቡበከር ናስር የመጨረሻ ቀናት እየቀረቡ ነው

በእግርኳሳችን ውስጥ በትውልዶች መካከል ከሚገኙ ድንቅ ባለተሰጥኦ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው አቡበከር ናስር በፕሪሚየር ሊጉ ለመጨረሻ ጊዜ የሚታይባቸው ጨዋታዎች ላይ ይገኛል።

ቡድኑ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየበት ጨዋታ በኋላ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚያደርገውን ዝውውር የተመለከቱ የጉዞ ጉዳዮችን ለመከወን ወደ አዲስ አበባ ያቀናው አቡበከር በቀጣዩቹ ቀናት የዝውውር ሂደቱን የሚቋጭ ይሆናል። ተጫዋቹ ሙሉ ለሙሉ ከቡናማዎቹ ጋር ከመለያየቱ በፊት ለ28ኛ ሳምንት ጨዋታ ወደ ባህር ዳር የሚመለስ እና ክለቡን የሚያገለግል ሲሆን በ29ኛ ሳምንት የመገኘቱ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል። ሙሉ ለሙሉ የደቡብ አፍሪካው ክለብ ንብረት የሚሆነው ከሰኔ 24 ጀምሮ በመሆኑ ግን 30ኛው ሳምንት ላይ በቡና መለያ እንደማንመለከተው ታውቋል።

በ14 ግቦች ከይገዙ ቦጋለ ጋር በመሆን በጣምራ የሊጉን ከፍተኛ አስቆጣሪነት እየመራ የሚገኘው አቡበከር በቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ተጨማሪ ግቦችን አክሎ ለተከታታይ ዓመታት ኮከብ ግብ አግቢ የመሆኑ ጉዳይ ከጨዋታ ቁጥር መቀነስ ጋር በተያያዘ ይበልጥ ፈታኝ እንደሚሆንበት ይታሰባል።

👉 የመኳንንት ካሳ አጀማመር

ሲዳማ ቡና ዋነኛ የመሀል ተከላካዮቹ ጊት ጋትኩት እና ያኩቡ መሐመድን በቅጣት ምክንያት ባጣበት በዚህ የጨዋታ ሳምንት የተፈጠረበትን ክፍተት ለመሙላት ወጣቱን መኳንንት ካሳን ለመጀመሪያ ጊዜ የቀዳሚ ተሰላፊነት ሚና በመስጠት ጨዋታውን አስጀምሮት ነበር።

ከሲዳማ የ20 ዓመት በታች ቡድን የተገኘው ወጣቱ ተከላካይ በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ እንደሚያደርግ ተጫዋች ሳይሆን ከጎኑ ከተሰለፈው ባለብዙ ልምዱ ተስፋዬ በቀለ ጋር በመሆን በጨዋታው ጥሩ መንቀሳቀስ ችሎ ነበር። በተለይም ዓይናፋርነት ሳያጠቃው በጥሩ የራስ መተማመን መንፈስ ከኋላ የቡድኑን የኳስ ፍሰት ለማስጀመር ያደርግ የነበረው ጥረት ትኩረት ውስጥ ከትቶት ነበር።

ይህን መሳዩ የተጨዋቹ አጀማመር ግን መጨረሻው ያማረ አልነበረም። 65ኛው ደቂቃ ላይ ተጨዋቹ በጅማው አጥቂ መሐመድኑር ናስር ላይ በሰራው ጥፋት ምክንያት ሁለተኛ ቢጫ ካርድ ተመልክቶ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለመጨረስ ሳይታደል ቀርቷል። በመሆኑም ነገ ብሩህ ጊዜ ከፊቱ እንደሚጠብቁት ያሳየባቸውን ደቂቃዎች እንዲሁም ከሜዳ በሁለተኛ ቢጫ የወጣበት አጋጣሚ በወጣቱ አጀማመር ውስጥ ሁለት ዓይነት ስሜት የሚጭሩ ሆነው አልፈዋል።