ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | 27ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተደረጉ የ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን መሰረት በማድረግ የሳምንቱን ምርጥ ቡድን እንዲህ አሰናድተናል።

አሰላለፍ 4-3-2-1

ግብ ጠባቂ

መክብብ ደገፉ – ሲዳማ ቡና

በተለየ የፀጉር ቀለም ወደ ጅማ አባ ጅፋሩ ጨዋታ የመጣው መክብብ ከአዲሱ ገፅታው ባለፈ ጥሩ የጨዋታ ቀንን አሳልፏል። ጅማዎች 6 ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን ቢያደርጉም በጊዜ አጠባበቅ እና ሙከራዎችን በማዳን ጠንቃቃ የነበረው መክብብ አደጋዎችን በመቀነስ ጨዋታውን ፈፅሟል።

ተከላካዮች

ሄኖክ አዱኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በሁለቱም መስመሮች ተሰልፎ መጫወት የሚችለው ሄኖክን የቀኝ መስመራችን ላይ አካተነዋል። በወልቂጤው ጨዋታ ከወትሮው ታታሪነቱ በተጨማሪ በእንቅስቃሴ እና በቆሙ ኳሶች የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችል ለከነዓን ማርክነህ ጎልም መነሻ ሆኗል።

አሸናፊ ፊዳ – አርባምንጭ ከተማ

በድሬዳዋው ጨዋታ የኳስ ቁጥጥሩን ለተጋጣሚው በተወው የአዞዎቹ ቡድን ውስጥ አሸናፊ የተከላካይ መስመሩን በጥሩ ሁኔታ መርቷል። አደጋ የሚጋብዙ ኳሶችን በማጥራት እና በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ፈጥኖ እርምጃ በመውሰድ ለቡድኑ ድል የሚጠበቅበትን አድርጓል።

አሚን ነስሩ – መከላከያ

ጦሩ ከወላይታ ድቻ ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ መረቡን እንዳያስደፍር ባስፈላጊ ሰዓቶች ላይ በአግባቡ ተከላክሏል። የተጋጣሚውን ዋነኛ አጥቂ ስንታየሁ መንግሥቱን እንቅስቃሴ ተከታትሎ በማምከኑ በኩል ደግሞ አሚን ቁልፍ ሚና ነበረው።

አምሳሉ ጥላሁን – ፋሲል ከነማ

ወደ ኋላ ያፈገፈገው ተጋጣሚውን ለማስከፈት ብዙ በለፋው ፋሲል ከነማ ውስጥ ወደ ፊት ተጠግቶ የቅብብል አማራጭ ይፈጥር የነበረው አምሳሉ ከቆሙ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ሲያመቻች የነበረ ሲሆን ሁለተኛው የሙጂብ ጎል እንዲቆጠርም ምክንያት ሆኗል።

አማካዮች

ጋቶች ፓኖም – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ግዙፉ አማካይ በድንቅ አቃሙ ገፍቶበታል። በወልቂጤው ጨዋታም የቡድኑን ድል ያረጋገጠች ግብ በፍፁም ቅጣት ምት ከማስቆጠር ባለፈ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ፣ ጥቃቶችን በቅብብል በማስጀመር እና የተጋጣሚ ቅብብሎች ወደ አደጋ ዞን እንዳይሻገሩ በማድረግ ኃላፊነቱን ተወጥቷል።

እንዳልካቸው መስፍን – አርባምንጭ ከተማ

በድሬዳዋው ጨዋታ ከወትሮው ወደ ኋላ የተጠጋ የመሀል አማካይነት ሚና ወደ ፊት ከፍ ብሎ በታታሪነት የቡድኑን ሚዛን ከመጠበቅ ባለፈ ማጥቃቱን በአግባቡ እያገዘ የታየው እንዳልካቸው እጅግ ወሳኝ የነበረው የአህመድ ሁሴን ጎል እንዲቆጠር መነሻ የሆነ የተመጠነ የቆመ ኳስ ማድረስም ችሏል።

ሱራፌል ዳኛቸው – ፋሲል ከነማ

የዐፄዎቹ አማካይ ከቆይታ በኋላ ወደ ሜዳ ተመልሶ መሀል ሜዳውን በሚያስመሰግን መልኩ መርቷል። ወደ ኋላ የታሳቡት አዳማዎችን ለማስከፈት ቅብብሎችን ከማድረግ ባለፈ ቁልፍ ኳሶችን ጥሩ አድርጎ ሲያደርስ የሙጂብን እጅግ ወሳኝ ቀዳሚ ጎል ድንቅ በሆነ አኳኋን ማመቻቸትም ችሏል።

ከነዓን ማርክነህ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከነዓን የሳምንቱ ምርጥ ተጫዋች የሚያስብለውን የጨዋታ ቀን አሳልፏል። ለቡድኑ ውጤት ማማር አብዝታ ስትጠበቅ የነበረችውን ቀዳሚ ጎል ከማስቆጠሩ ባለፈ በስድስት የጊዮርጊስ ጥቃቶች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ መሆን ችሏል።

ኤፍሬም አሻሞ – ሀዋሳ ከተማ

ለተከታታይ ሳምንት በቡድናችን የተካተተው ኤፍሬም በባህር ዳሩ ጨዋታም በቁልፍ ቦታዎች ላይ እየተገኘ ያለድካም ቡድኑን አገልግሏል። በራሱ ጥረት ከመረብ ያገናኛት የሀዋሳ ቀዳሚ ጎል 2-1 በተጠናቀቀው ጨዋታ ለሀዋሳ ድል የነበራት ዋጋም እጅግ ከፍተኛ ነበር።

አጥቂ

ሙጂብ ቃሲም – ፋሲል ከነማ

ከግብ አግቢዎች ዝርዝር ውስጥ ከጠፋ ረጅም ጊዜ ያሳለፈው ሙጂብ ፋሲልን ወሳኝ ድል ያስጨበጡ ሁለት ግቦች አስቆጥሯል። ግቦቹን በአዳማ ላይ ያስቆጠረባቸው የአጨራረስ መንገዶቹ ደግሞ ለዐፄዎቹ ቀጣይ ጨዋታዎች ጭምር ተስፋን የሰጡ ነበሩ።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ

የተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማን አጨዋወት ፍሬ አልባ ያደረገው የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የጨዋታ ዕቅድ ሰምሮ አዞዎቹ ሳምንቱን በ3-0 ድል ደምድመዋል። በዚህም አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቡድናቸውን ከመውረድ ስጋት አርቀው እስከ አምስተኛ ደረጃ ይዞ ስለመጨረስ ማለም እንዲጀምር አድርገዋል።

ተጠባባቂዎች

መሐመድ ሙንታሪ – ሀዋሳ ከተማ
አስቻለው ታመነ – ፋሲል ከነማ
ደጉ ደበበ – ወላይታ ድቻ
ሮቤል ግርማ – አዲስ አበባ ከተማ
ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ሀዲያ ሆሳዕና
ፍሬው ሰለሞን – ሲዳማ ቡና
ብሩክ በየነ – ሀዋሳ ከተማ
ኤሪክ ካፓይቶ – አርባምንጭ ከተማ