የአሠልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 1-0 ድሬዳዋ ከተማ

በወራጅ ቀጠናው ትልቅ ትርጉም ያለው ፍልሚያ በጣናው ሞገዶቹ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የአሸናፊ ቡድን አሠልጣኝ አስተያየት ሲሰጡ የተሸናፊው ግን ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

አብርሃም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ


ጨዋታው እንዴት ነበር…?

ጨዋታው ውጥረት የበዛበት እና አስቸጋሪ ጨዋታ ነበር። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ሁለታችንም የታችኛው ደረጃ ላይ በመሆናችንና ወደ ላይኛው ቀጠና ለመውጣት ባደረግነው ብርቱ ፉክክር ነው። ድሬዳዋ ቀላል ሆኖ እንደማይመጣ አውቀን ነበር። ያም ሆኖ ግን የሚያስቆጩ የሳትናቸው ኳሶች ወደ ግብነት ቢቀየሩ ኖሮ ከዚህ በተሻለ አሸንፈን መውጣት እንችል ነበር። ከሁሉም በላይ ግን ሦስት ነጥቡ ለእኛ አስፈላጊ ስለነበር እግዚአብሔር ይመስገን ተሳክቶልናል።

በሁለተኛው አጋማሽ ስለተከተሉት አጨዋወት…?

በሁለተኛው አጋማሽ በአንድ በኩል ያገባነውን ኳስ እንዳይገባብን መጠበቅ በሌላ በኩል ደግሞ እነርሱ ነቅለው ሲመጡ ጀርባቸውን ለመጠቀም ነበር። ይሄንን አግኝተን ዓሊ፣ ፍፁም እና ማውሊ የሳቷቸው ኳሶች የሚያስቆጩ ናቸው።

ስለቀጣይ ጨዋታዎች እና ያለመውረድ ትንቅንቁ…?

እኔ እስከ መጨረሻው ድረስ ላለመውረድም ሆነ ለሻምፒዮናነት የሚደረገው ውድድር በጣም ትንቅንቅ አለው ብዬ ነው የማስበው። ለዚህም ነው ውድድሩ እጅግ በጣም አጓጊ የሆነው። ስለዚህ ቀጣይ ተጋጣሚያችን ሰበታም በስሌት መውረዱን አላረጋገጠምና ፈታኝ ጨዋታ ሊያደርግ ይችላል ብዬ አስባለው።

ስለቡድኑ ደጋፊዎች…?

የዛሬው ውጤት እጅግ በጣም ወሳኝ ነበር። እውነት ለመናገር የባህር ዳር ደጋፊዎች በእስካሁኑ ጉዞዋችን በትዕግስት ነው ሲደግፉን የነበሩት። ስንሸነፍም መቃወማቸው ትክክል ነው ፤ ምክንያቱም ከውጤት መፈለግ የተነሳ ነው። ስለዚህ ሁሉንም ደጋፊዎች እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለው።