ነጥብ በመጋራት ከተጠናቀቀው ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
አሰልጣኝ ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ
ስለ ጨዋታው
“እጅግ ጠንካራ ፉክክር የታየበት ፣ በሁለታችን በኩል የተሻለ ነገር ያሳየንበት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
በሁለተኛው 45 ስለተቀየረው ነገር
“መልበሻ ክፍል ውስጥ በዕረፍት ሰዓት የተነጋገርነው ‘ምንም አማራጭ የለንም ከማጥቃት ውጪ’ ነው፡፡ ማጥቃት ማለት አጥቂዎችን ማብዛት ሳይሆን የማጥቃት መንገዶችን በትክክል ማወቅ ከዛን ያንን ደግሞ በአግባቡ መጠቀም የሚል ነገር ነው ይዘን የገባነው፡፡ በተወሰነ መልኩ ዕድሎችን ፈጥረናል ተጠቅመንበታል ይሄን ሁለተኛውን አርባ አምስት ላይ፡፡
ተጨማሪ ጎል አለማስቆጠራቸው
“ለረጅም ጊዜያት ፊት ላይ የምንጠቀመው ጌታነህ ከበደን ነው ፤ ጨራሹ አጥቂያችን እሱ ነው፡፡ አጥቂዎቻችንን በዚህ መንገድ ማምጣት አለመቻላችን ዛሬ ጎድቶናል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደ ጌታነህ ዓይነት ተጫዋች በምታጣ ሰዓት እነዚህን ልጆች ስትጠቀም ሻርፕ ካልሆኑ ትጎዳለህ፡፡ ስለዚህ እነርሱን ወደ ሥራ ውስጥ ማስገባት ነበረብን ብዬ አስባለሁ፡፡
ስለ ቀጣይ ተጋጣሚ ጅማ አባ ጅፋር እና ወላይታ ድቻ
“የሌሎች ውጤት ብዙም አያስጨንቀንም፡፡ ወልቂጤ በራሱ ይወስነዋል ውድድሮቹን ብዬ ነው የማስበው፡፡”
አሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ – ሲዳማ ቡና
ስለ ጨዋታው እና ስለተሰጠባቸው ፍፁም ቅጣት
“ጨዋታው ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ማራኪ የሆነ እንቅሰቃሴ ነበረው፡፡ በማይሆን ስህተቶች በዳኝነት የተነሳ ዋጋ ከፍለን ወጥተናል፡፡ እኛም የተከለከልነው በመጀመሪያው አርባ አምስት ላይ ተገቢ አልነበረም፡፡ ሁለተኛው አርባ አምስት ላይ ደግሞ እኛ ላይ የተፈረደበት ፍርድ ለእኔ ግልፅ አልሆነልኝም፡፡ አሁን ሊጉ እያለቀ ነው፡፡ ሊጉ እያለቀ እያለ በሊጉ ላይ የተሻለ ነገር መስራት እየቻሉ ፣ ዳኞች እንዲህ ዓይነት ስህተት ቡድኖችን ዋጋ ያስከፍላል እና ለቀጣይ ቢያስተካክሉ፡፡
ስለተደረጉ ሙከራዎች
“አጥቂዎች አንዳንዴ ጎል የማግባት ፍላጎት ሲበዛ ኳሶች ይሳታሉ፡፡ በቀጣይ ይሄንን እየሰራን እናስተካክላለን፡፡
ስለግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ
“አሁን ላይ እያደረገ ያለው ጥሩ እንቅስቃሴ ነው፡፡ በቀጣይም ይሄንን ነገር ያስቀጥላል የሚል አመኔታ አለኝ። በግሉ ይጥራል ፣ ይጣጣራል ፤ የተሻለ ተጫዋች ለመሆን። በቀጣይ በምናየው ነገር እያየን የምናስተካክለው ይሆናል፡፡”