ነገ ቀጥለው በሚደረጉት የሊጉ ሦስት ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
ጅማ አባ ጅፋር ከ ወላይታ ድቻ
የጨዋታ ቀኑ ረፋድ ላይ እየሰመጠ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋርን እና ቀድሞ የሰበሰባቸው ነጥቦችን እየመነዘረ የሚገኘው ወላይታ ድቻን ያገናኛል። ጅማ ከበላዩ ያለው ድሬዳዋ ዛሬ መሸነፉን ተከትሎ የመጨረሻ ዕድሉን ተጠቅሞ የስድስት ነጥብ ልዩነቱን ለማጥበብ በማሰብ ወደ ሜዳ ሲገባ ቀሪ የወራጅ ቀጠና ተፋላሚዎችም ሽንፈት እንዳያገኛቸው ያልማል። 6ኛ ደረጃ ላይ ያለው ወላይታ ድቻ በበኩሉ ከ11 ጨዋታ በኋላ ከድል ጋር መታረቅ ቢያንስ አንድ ደረጃን እንዲያሻሽል ሊረዳው ይችላል።
ከውጤት ፈላጊነት አንፃር ከፍ ባለ ጫና ውስጥ ሆኖ ጨዋታውን የሚያደርገው ጅማ አባ ጅፋር የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመያዝ ግቦችን ለማግኘት በሚችለው መጠን ለማጥቃት እንደሚሞክር ይጠበቃል። ነገር ግን በሲዳማ ቡናው ጨዋታ በቀይ ካርድ ምክንያት የቁጥር ብልጫ ባገኘባቸው ደቂቃዎች እንኳን በሚፈለገው መጠን ተጋጣሚውን ማስከፈት አለመቻሉ ሲታይ የተሻለ የመከላከል አደረጃጀት ካላው የነገ ተጋጣሚው አንፃር ይህ ትዕግስት የሚጠይቀው የጨዋታ ምርጫው ካለበት የውጤት አንገብጋቢነት አንፃር ምን ያህል አዋጭ ይሆንለታል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል። በአንፃሩ በዛው የሲዳማው ጨዋታ አንዳንድ ቅፅበቶች ላይ ያሳየው በመልሶ ማጥቃት በፈጣሪ አማካዮቹ የመጨረሻ ቅብብሎች ዕድሎችን የመፍጠር አዝማሚያ ድቻዎችን ከሜዳቸው ማስወጣት ከቻለ እንደሁለተኛ ዕቅድ ሊያገለግለው ይችላል።
በአንፃሩ ወቅታዊ አቋሙ እምብዛም የሚያኩራራ ያልሆነው ወላይታ ድቻ ቀድሞ ለሰበሰባቸው ነጥቦች ምስጋና ይግባ እና የተሻለ ደረጃን ይዞ የመጨረስ ዓላማን ይዞ ጨዋታውን ያደርጋል። ከዚህ አንፃር ቡድኑ እንደወትሮው በጥልቀት ይከላከላል ተብሎ የማይታሰብ ቢሆንም ከኳስ ውጪ በፍጥነት የመከላከል ቅርፁን ለመያዝ ከመሞከር ወደ ኋላ የሚል አይመስልም። ድቻ ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ሜዳ የተመለሰው አጥቂው ስንታየሁ መንግሥቱ ወደ ሙሉ የጨዋታ ብቁነት ደረጃ ላይ እንዳልደረሰ ባሳየን የመከላከያው ጨዋታ ልዩነት ባይፈጥርለትም ነገ የተሻሻለ ብቃት እንዲያሳይ ይጠብቃል። ለዚህም የቡድኑ ቀጥተኛ ጥቃቶች በመከላከሉ ደካማ በሆነው የጅማ ሳጥን ውስጥ በንፅፅር የሚያላውስ ክፍተት ሊያገኝ ለሚችለው አጥቂ በቂ ዕድሎችን የሚፈጥር የማጥቃት ስትራቴጂ ይዞ መግባት ጨዋታን ለማሸነፍ ዋነኛ የቤት ሥራው ይመስላል።
ጅማ አባ ጅፋር እዮብ ዓለማየሁን በቅጣት የሚያጣ ሲሆን ሽመልስ ተገኝ እና አልሳሪ አልመሀዲም ከስብስቡ ጋር አይገናኙም። ወላይታ ድቻ ግን ያለቅጣት እና ጉዳት ዜና ጨዋታውን ያደርጋል።
የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ሄኖክ አክሊሉ ፣ ረዳቶች ሸዋንግዛው ከበደ እና ትንሳኤ ፈለቀ ፣ አራተኛ ዳኛ ሀብታሙ መንግስቴ
ተጨማሪ ዳኞች – ትግል ግዛው እና ሸዋንግዛው ተባበል
የእርስ በርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ሰባት ጊዜ ተገናኝተዋል። በውጤቶቹ ሁለት ጊዜ ነጥብ የተጋሩ ሲሆን ጅማ አባ ጅፋር ሦስት ወላይታ ድቻ ደግሞ ሁለት ድል አስመዝግበዋል። በጨዋታዎቹ ድቻ 8 ጅማ ደግሞ 7 ግቦች አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወላይታ ድቻ (4-3-3)
ቢኒያም ገነቱ
በረከት ወልደዮሐንስ – አንተነህ ጉግሳ – ደጉ ደበበ – አናጋው ባደግ
ሀብታሙ ንጉሴ – ንጋቱ ገብረስላሴ – እንድሪስ ሰዒድ
ምንይሉ ወንድሙ – ስንታየሁ መንግሥቱ – ቃልኪዳን ዘላለም
ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)
አላዛር ማርቆስ
በላይ አባይነህ – ኢያሱ ለገሠ – የአብስራ ተስፋዬ – ተስፋዬ መላኩ
መስዑድ መሐመድ – አስጨናቂ ፀጋዬ – ዳዊት እስቲፋኖስ
አድናን ረሻድ – መሐመድኑር ናስር – ሱራፌል ዐወል
ሀዲያ ሆሳዕና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በሰንጠረዡ አጋማሽ እና ጫፍ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ተጠባቂ ጨዋታ ነው። ከወራጅ ቀጠናው ራቅ ብሎ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማሳካት ለከርሞው በሊጉ የመቆየቱን ነገር ያረጋግጥለታል። ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ወደ ዋንጫው የሚያደርገው ጉዞ ላይ ሌላ ወሳኝ እርምጃ የሚጨምርለት ወሳኝ ጨዋታ ነው።
ሀዲያ ሆሳዕና ወደዚህ ጨዋታ ይዞ የሚመጣው ጠንካራ ጎን በሊጉ የላይኛው ሰንጠረዥ ከሚገኙ ቡድኖች ጋር ሲገናኝ የሚያሳየውን አቋምን ነው። ለአብነት እስካሁን እስከ አምስተኛ ደረጃ ካሉት ቡድኖች ጋር ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ሁለቱን ብቻ ሲሸነፍ ሦስት ድል እና ሁለት አቻን ማስመዝገቡ ለዚህ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይቻላል። ከአቀራረብ አንፃር ቡድኑ በነገውም ጨዋታ ሁለቱን መስመሮች ለመዝጋት በብዛት ወደራሳቸው የሜዳ ክፍል አመዝነው በሚንቀሳቀሱ የመስመር ተመላላሾች የታጀበ ከኋላ ባለአምስት ተጫዋች መስመር ሰርቶ የሚጫወትባቸው ደቂቃዎች እንደሚበራከቱ ይጠበቃል። ይህም የጊዮርጊስን የኳስ ቁጥጥር እና የማስከፈት ጥረት እንዲሁም የሀዲያ ሆሳዕናን ጥብቅ መከላከል እና መልሶ ማጥቃት ዋናኛ የጨዋታው ገፅታ ሆኖ እንደምንመለከተው የሚያደርግ ይመስላል።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ከዚህ ጨዋታ ከድል ውጪ የሚታሰብ ውጤት ባለመኖሩ ቡድኑ ሁሉንም ነገር ዉደ ፊት በመወርወር ላይ እንደሚያተኩር ይታሰባል። በዚህ ሂደት ውስጥ በኳስ ቁጥጥር ክፍተቶችን ለማግኘት ድንቅ አቋም ላይ በሚገኘው ከነዓን ማርክነህ የሚመራው አማካይ ክፍሉ ነገሮች ቀላል ላይሆኑለት እንደሚችል ቢታሰብም ቡድኑ በእንቅስቃሴም ሆነ በቆሙ ኳሶች በረጅሙ ወደተጋጣሚ የግብ ክልል የሚልካቸው ኳሶች እገዛቸው ቀላል የሚባል አይሆንም። በሁሉም ዲፓርትመንቶች ላይ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋቾችን በመያዙ በብዙው የተጠቀመው ቡድኑ ዋነኛ አግቢው ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ በመጨረሻው ጨዋታ በጥቂት ደቂቃዎች ካሳየው ጥሩ ምልክት አንፃር ነገ ረዘም ያሉ ደቂቃዎች ተሰጥቶት ልዩነት ሊፈጥር እንድሚችል ይታሰባል። ይህም የጊዮርጊስን የኳስ ቁጥጽር እና የማስከፈት ጥረት እንዲሁም የሀዲያ ሆሳዕናን ጥብቅ መከላከል እና መልሶ ማጥቃት ዋናኛ የጨዋታው ገፅታ ሆኖ እንደምንመለከተው የሚያደርግ ይመስላል።
በነገው ጨዋታ የሀዲያ ሆሳዕናው ፍሬዘር ካሳ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ሲጠበቅ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ አቤል ያለው አገግሞ መሰለፍ ግን እርግጥ አልሆነም።
የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ተካልኝ ለማ ፣ ረዳቶች ሙሉነህ በዳዳ እና ለዓለም ዋሲሁን ፣ አራተኛ ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ
ተጨማሪ ዳኞች – ተመስገን ሳሙኤል እና ዳንኤል ጥበቡ
የእርስ በርስ ግንኙነት
– ቡድኖቹ እስካሁን በአምስት ጨዋታዎች የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለቴ ሀዲያ ሆሳዕና አንድ ጊዜ ድል ቀንቷቸው ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በእነዚህ ጨዋታዎች ጊዮርጊስ አምስት ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ሁለት ግቦችን አስመዝግበዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)
መሳይ አያኖ
ግርማ በቀለ – ፍሬዘር ካሳ – ቃለአብ ውብሸት
ብርሃኑ በቀለ – ሳምሶን ጥላሁን – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – እያሱ ታምሩ
ሀብታሙ ታደሠ – ባዬ ገዛኸኝ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)
ቻርለስ ሉኩዋጎ
ሱሌይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሄኖክ አዱኛ
በረከት ወልዴ – ጋቶች ፓኖም
አብስራ ተስፋዬ – ከነዓን ማርክነህ – ቸርነት ጉግሳ
አማኑኤል ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ ከተማ ከ ሰበታ ከተማ
የጨዋታ ዕለቱ በወራጅ ቀጠና ፍልሚያ ይጠናቀቃል። አዲስ አበባ ከተማ ከስሩ ያለው ድሬዳዋ ከተማን በሦስት ነጥብ የመራቅ እንዲሁም ከአዳማ እና ወልቂጤ በላይ የመቀመጥ ዕድልን ይዞ ይገባል። በአንፃሩ ሰበታ ከተማ እስትንፋሱን በድል እስከመጨረሻው ለማስቀጠል ከመሞከር ባለፈ ሽንፈት እና አቻ የዘንድሮው የመጀመሪያ ወራጅ ቡድን ያደርገዋል።
እጅግ ወሳኝ በሆነው የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ ውስጥ እስካሁን የዘዋቸው የመጡት እና በቅርብ ጨዋታዎችም የታዩት ድክመቶቻቸው እንዲቀረፉ ማደርግ የሚፈልጉትን ውጤት ለማግኘት ወሳኝ ይሆናል። በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ጨዋታውን በራሱ ቀጥጥር ውስጥ አድርጎ የግብ ዕድሎችን በተደጋጋሚ በሚፈጥርባቸው ደቂቃዎች የተቻለውን ያህል ግቦች ማስቆጠር መቻል በዚህ ረገድ ይነሳል። የፊት መስመር ተሰላፊዎች ደካማ አጨራረስ እና የቅብብል ወይም የሙከራ የመጨረሻ ውሳኔ ድክመት ጨዋታዎችን መግደል እንዳይችል ሲያደርገው ታይታል። ይህንን ተከትሎ የሚታየው ቀድሞ መርቶ ውጤቱን አሳልፎ የመስጠት አባዜው በነገው ጨዋታም የቡድኑ ትልቁ ፈተናው እንደሆነ ይታመናል።
በሰበታ ከተማ በኩል የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን መያዝ እንዲሁም ቡድኑ ባሉት ጥሩ የመስመር ተከላካዮች የሜዳውን ስፋት በመጥቀም በተለይም ከቀኝ መስመር ጥሩ አጋጣሚዎችን ሲፈጥር መታየቱ የተለመደ ነው። ሆኖም ከፊት የሚታይበት የአጨራረስ ችግሩ እና እጅግ ተለዋዋጭ የሆነ የተጫዋቾች ምርጫው በመሀል ምልክት ሰጥቶ የነበረው የቡድን ውህደት ደረጃው መዳከም ነገም ፈተናው ይሆናል። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የቡድኑ አሰልጣኞች ከልምምድ ርቆ በነበረ እና አሁንም ከሜዳ ውጪ ባሉ ችግሮች በሥነልቦናው ከተጎዳው ስብስባቸው ውስጥ መፍትሄ ፈልገው ማግኘት ቀላል እንደማይሆንላቸው ግን ግልፅ ይመስላል።
አዲስ አበባ ከተማ ወሳኙን ጨዋታ ያለቅጣት እና ጉዳት የሚያከናውን ሲሆን በረከት ሳሙኤል ከቅጣት የሚመለስለት ሰበታ ከተማ ገዛኸኝ ባልጉዳ እና ለዓለም ብርሀኑን በጉዳት ያጣል።
የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ሀብታሙ መንግስቴ ፣ ረዳቶች ዘሪሁን ኪዳኔ እና ሀብተወልድ ካሳ ፣ አራተኛ ዳኛ ተፈሪ አለባቸው
ተጨማሪ ዳኞች – አበራ አብርደው እና ወጋየሁ አየለ
የእርስ በርስ ግንኙነት
– ለቡድኖቹ የመጀመሪያ በነበረው የዘንድሮው ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ 5-1 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
ግምታዊ አሰላለፍ
አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)
ዳንኤል ተሾመ
አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ልመነህ ታደሰ – አዩብ በቀታ – ሮቤል ግርማ
ሙሉቀን አዲሱ – ቻርለስ ሩባኑ – ኤሊያስ አህመድ
እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን
ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)
ሰለሞን ደምሴ
ጌቱ ኃይለማሪያም – በረከት ሳሙኤል – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ
በኃይሉ ግርማ – ጋብርኤል አህመድ
ሳሙኤል ሳሊሶ – አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ – ዱሬሳ ሹቢሳ
ዴሪክ ኒስባምቢ