የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ተጠባቂው ጨዋታ ነጥብ በመጋራት ተጠናቋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት ስድስት ጨዋታዎች ዛሬ በሁለት ስታዲየሞች ሲደረጉ ተጠባቂው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ 1-1 ሲጠናቀቅ ሀዋሳ ፣ መከላከያ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ አዲስ አበባ እና ጌዲኦ ዲላ ተጋጣሚዎቻቸውን ረተዋል፡፡

ሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በረፋዱ ጨዋታ ድል አድርገዋል

3፡00 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሜዳ ላይ ሊጉን ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ እና ላለመውረድ እየዳከረ የሚገኘውን አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን በግብ አንበሽብሾ አሸናፊ አድርጓል፡፡ ተመጣጣኝ ፉክክርን ከጅምሩ ያስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሂደት የሀዋሳ ከተማ የተሻለ የማጥቃት ንቃትን አስተውለንበታል፡፡ 23ኛው ደቂቃ ላይ ኪፊያ አብዱራህማን በአግባቡ ያቀበለቻትን ረድኤት አስረሳኸኝ መረብ ላይ አሳርፋ ሀዋሳን መሪ አድርጋለች፡፡

በእንቅስቃሴ ጥሩ ቢሆኑም የሀዋሳን የማጥቃት ሽግግር መቋቋም የተሳናቸው አቃቂዎች 40ኛው ደቂቃ ላይ በነፃነት መና ድንቅ የማቀበል አቅም ረድኤት በድጋሚ ጎል አስቆጥራ የሀዋሳን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ስታደርግ ትዕግስት ሽኩር አቃቂን ወደ ጨዋታ የምትመልስ ግብ ከመረብ ብታሳርፍም ኪፊያ አብዱራህማን በአጋማሹ ጭማሪ ላይ አክላ 3-1 ሀዋሳን አሸጋግራ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ወደ መልበሻ ክፍል ሲያመሩ በስታዲየሙ አንድም የፀጥታ አካላት አለመኖራቸው የዕለቱ ዳኞች ከአቃቂ ቃሊቲ የቡድን አባላት ጋር የፈጠሩት እሰጥ አገባን ሊቆጣጠር የነበረ አካል አለመኖሩ አስገራሚ ሆኗል፡፡ ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ነፃነት መና እንዲሁም አንጋፋዋ ተጫዋች ብዙሀን እንዳለ ተጨማሪ ጎሎችን አክለው ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በተመሳሳይ 3፡00 ሰዓት ሲል ቅዱስ ጊዮርጊስን ከባህርዳር ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በእንስት ፈረሰኞቹ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ በተደጋጋሚ በሚደረጉ ጨዋታዎች እየመሩ በሊጉ ለመሸነፍ ሲበቁ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከዕረፍት በፊት አማካዩዋ ቤተልሄም መንተሎ 45ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረችው ብቸኛ ግብ የአሰልጣኝ ረውዳ ዓሊው ክለብ 1-0 ድል አድርጓል፡፡

አዲስ አበባ እና ጌዲኦ ዲላ የ8፡00 ሰዓቱን ጨዋታ በድል ተወጥተዋል

ጨዋታው ከሰዓት 8፡00 ቀጥሎ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዲስ አበባ ከተማን እና ድሬዳዋ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር አስተናግዶ በመጨረሻም የመዲናይቱን ክለብ ሦስት ነጥብ አሸምቶ ተደምድሟል፡፡ 56ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ግብ ጠባቂ አበባየው ጣሰው በአጥቂዋ ቤተልሄም ሰማን ላይ በሳጥን ውስጥ የሰራችሁን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አሪያት ኦዶንግ ከመረብ አሳርፋ ቡድኗን 1-0 አሸናፊ አድርጋለች፡፡

በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሜዳ ላይ ለወራት ከክፍያ ጋር በተያያዘ ልምምድ ሳይሰሩ የከረሙት ጌዲኦ ዲላዎች ቦሌ ክፍለከተማን የገጠሙበትን ጨዋታ በድል ተወጥተዋል፡፡ ይታገሱ ተገኝወርቅ እና አምበሏ ቀለሟ ሙሉጌታ የጌዲኦ ዲላን የድል ግቦች ሲያስቆጥሩ ልማደኛዋ አጥቂ ንግስት በቀለ ቦሌን ከሽንፈት ያልታደገች ግብ አስቆጥራ ጨዋታው 2-1 በጌዲኦ ዲላ የበላይነት ተገባዷል፡፡

መሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ተከታዩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ሲጋሩ መከላከያ አሸንፏል

ተጠባቂ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ለተመልካች አዝናኝ በነበረው እና በሙሉ የጨዋታው ደቂቃ ጠንካራ የሜዳ ላይ ትንቅንቅ በርትቶ መታየት በቻለበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ለረጅም ደቂቃዎች ግብ ሳይቆጠርበት ዘልቆ ልክ 60ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚዋን ግብ ተመልክተናል፡፡ ከማዕዘን ምት እፀገነት ብዙነህ ስታሻማ ሀሳቤ ሙሶ በግንባር በመግጨት ባንክ ወደ መሪነት አሸጋግራለች፡፡ ከአስራ ዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን ኤሌክትሪክ ሲረታ ተቀይራ በመግባት ልዩነት ስትፈጥር የታየችው ትንቢት ሳሙኤል እጅግ ግሩም ጎል ከመረብ አገናኝታ ኤሌክትሪክን 1-1 አድርጋለች፡፡ 85ኛው ደቂቃ ላይ ሀሳቤ ሙሶ ጥፋት ሰርተሻል በሚል በኢንተርናሽናል ዳኛ ምስጋና ጥላሁን በሁለት ቢጫ በንግድ ባንክ በኩል በቀይ ከሜዳ ተወግዳለች፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች በተሻለ ኃይል ጥቃት ለመሰንዘር ሁለቱም ቡድኖች ጥረት ቢያደርጉም ተጨማሪ ጎል ሳንመለከት 1-1 ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

በሌላኛው ጨዋታ መከላከያ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሜዳ ላይ አዳማን ገጥሞ 3-1 አሸናፊ ሆኗል፡፡ ረሂማ ዘርጋው ከዕረፍት በፊት እና በኋላ ለመከላከያ ሁለት ግብ ስታስቆጥር ሴናፍ ዋቁማ በበኩሏ አንድ ጎሎ አክላለች፡፡ ሄለን እሸቱ ለአዳማ ሁለት ጎሎችን ብታስቆጥርም መከላከያ ጨዋታውን 3-2 በማሸነፍ ነጥቡን አሳድጓል፡፡