የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 1-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ተጠባቂው ጨዋታ በአቻ ውጤት ከተጠነቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዲያ ሆሳዕና

ስለጨዋታው

“ጨዋታው ከሞላ ጎደል እንደሚከብድ መጀመሪያም ገልጬ ነበር። እንደጠበቅነው ነው ፤ እኛ ግን የምንፈልገው አንድ ነጥብ ነበር። ከባድ ሁኔታ ላይ ስለነበርን ውጤት አሳክተናል። እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥንካሬ መሪም ስለሆነ አንድ ነጥብ ከእነሱ ማግኘት ለእኛ ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው።

በመጀመሪያው አጋማሽ ከሙከራ ስለመራቃቸው

“ተጋጣሚያችን ካለው ጥንካሬ አንፃር መርጠን የገባነው ነው። ከዕረፍት በኋላ ግን ምንም አማርጭ ስለሌለን ያሉንን ተጫዋቾች ተጠቅመን አግብተን ዕኩል ለመውጣት ከተቻለ ለማሸነፍ ነበር። ካሰብነው በአንዱ ተሳክቶልናል።

ስለኤፍሬም ዘካርያስ ጎል

“በሰዓቱ ጎሉ የሚያምር ነው። ከጎሉ ይልቅ ግን እኔ ስፈልግ የነበረው የቡድኑን ዕኩል ለዕኩል እና ማሸነፍ ስለነበር ስለጎሉ ከዚህ በኋላ ነው ልገልፅ የምችለው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለቀ ሰዓትም ዕድሎች አግኝቷል እና ምንም ደስታ አልነበረኝም ፤ ከዚህ በኋላ ነው ምናልባት ላጣጥመው የምችለው።

ስለመሳይ አያኖ ብቃት

“መሳይ ቡድንችንን ሲቀላቀል ጥሩ የሚንቀሳቀስ በመሆኑም ነው። እሱም ብቻ ሳይሆን ሌሎች ግብ ጠባቂዎችም ሆኑ ተጫዋቾች ሁሉም ገብተው መጫወት የሚችሉ ናቸው። የመሳይ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ደስ የሚል ብቃት ነው የሚያሳየው ፤ ይሄ ለራሱም አንድ ጥንካሬ ነው ፤ ለቡድናችንም ጠንካራ ጎን ነው። ወደ ፊት ለራሱ የሚወስደው የቤት ሥራ ነው የሚበልጠው። እሱ ጥሩ ከሆነ እኛም ጥሩ እንሆናልን።”

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለጨዋታው

“ውጤት እንፈልግ ነበር። ውጤት ለማግኘትም ብዙ እንቅስቃሴ አድርገናል። ብዙ ነገሮች ሞክረናል ግን በመጨረሻ ደቂቃ ባልጠበቅንበት ሰዓት ገብቶ ዕኩል ለዕኩል ወጥተናን። በአግባቡ ተጫውተን ጎሎች ለማግኘት እየሄድን ነበር። በዛ መሀል ባለቀ ደቂቃ ላይ ጎል ገብቶብናል።

ስለቡድኑ አጨዋወት

“ብዙም አመርቂ ባይሆንም የተሻለ ነገር ለማድረግ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተው ነበር። ግን እንደፈለኩት እና በይበልጥ ወደ ጎሉ ቶሎ ቶሎ ለመኬድ ስለፈለጉ ያንን ነገር አድርገናል። ውጤቱ ግን ያው ዕኩል ለዕኩል ሆነናል።

ስለቀጣይ ጨዋታዎች ጫና

“ምንም ጫና ውስጥ የሚከተን ነገር የለም። ሁሉም ነገር በራሳችን እና እኛ እየተጫወትን ያለነው ለራሳችን ነው። ሠላሳውንም ጨዋታ እንደዋንጫ ጨዋታ ነው የምናየው እና እዛ ላይ ትኩረት እያደረግን መጫወት ነው የምንፈልገው።

ፍሬዘር ካሳ ከመስመር ላይ ስላወጣው ኳስ (በምስል ከተመለከቱት በኋላ)

“ይሄ ጎል አይደለም። መስመሩን ስላለቀቀ ይሄን አይቼ መፍረድ ስለፈለኩ ነው። ይሄ ትክክለኛ ጎል አይደለም ፤ እውነት ነው። ግን በጨዋታው ላይ የተሻለ ነገር ለማድረግ ሞክረናል። በእግርኳስ የሚያጋጥም ነው።”