ሪፖርት | አዲስ አበባ ከተማ ተንፈስ ብሏል

ሰባት ግቦችን ያስተናገደው የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የ4-3 ድል ያሳካው አዲስ አበባ ከተማን ከአደጋ ዞኑ ሲያሸሽ ሰበታ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋርን ከሊጉ አሰናብቷል።

አዲስ አበባ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ነጥብ የተጋራበትን የመጀመሪያ አሰላለፍ ሳይለውጥ የዛሬውን ጨዋታ ጀምሯል። ሰበታ ከታማ ደግሞ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያለግብ ከተለያየው ስብስብ በኃይሉ ግርማ እና ዴሪን ንስባምቢን በዱሬሳ ሸቢሳ እና ቢስማርክ አፒያ ተክቷል።

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች በቻርለስ ሪባኑ እና ኤልያስ አህመድ ከሳጥን ውጪ ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ያደረጉት አዲስ አበባዎች የተሻለ አጀማመር ነበራቸው። ክፍት ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ በእንቅስቃሴ የተሻለ እርጋታ ይታይባቸው የነበሩት ሰበታዎች ቀስ በቀስ ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን የሚደርሱባቸው አጋጣሚዎች መታየት ጀምረዋል። በአንፃሩ አዲስ አበባዎች በመጨረሻው የሜዳው ክፍል ላይ የተሳኩ ቅብብሎችን ማድረግ ተሳናቸው እንጂ አደገኛ የማጥቃት ሂደቶችን አስመልክተዋል።

16ኛው ደቂቃ ላይ ሰበታ ከተማ ሳይታሰብ ግብ አስቆጥሯል። ፍፁም ገብረማሪያም በረጅሙ ወደ ግራው ማዕዘን የተላከውን የአብዱልሀፊስ ቶፊቅን ኳስ በግል ጥረቱ ይዞ ልመንህ ተዳሰን አታሎ በመግባት እና የዳንኤል ተሾመን ግምት በማዛባት ጎል አድርጎታል። ሆኖም የማጥቃት ጫናቸውን ከፍ አድርገው የቀጠሉት አዲስ አበባዎች 21ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ሆነዋል። ሙሉቀን አዲሱ መሀል ላይ ቢያድግልኝ ኤልያስ ያልተቆጣጠረውን ኳስ ሰንጥቆለት አንተነህ ተስፋዬ ለማቋረጥ ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ያገኘው ፍፁም ጥላሁን ሳጥን ድረስ በእርጋታ ይዞ በመግባት አስቆጥሮታል።

በሰበታ ሜዳ ላይ አድሎቶ የቀጠለው ጨዋታ ከውሃ ዕረፍት ሲመለስም የመዲናዋ ክለብ ሌላ ግብ አክሏል። 28ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለ ከበደ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ፍፁም ጥላሁን በግንባሩ በመግጨት ሁለተኛ ጎል አድርጎታል። አዲስ አበባዎች መሪ ከሆኑ በኋላ ከባባድ ሙከራዎች መታየታቸውን ቢቀንሱም ከእንዳለ ከበደ እና ቻርለስ ሪባኑ የሚነሱ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ይቃረቡ ነበር። ሆኖም ሰበታዎች ሌላ ግብ ለማግኘት ከጫፍ ደርሰው ነበር። 42ኛው ደቂቃ ላይ ኃይለሚካኤል አደፍርስ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ዱሬሳ ሸቢሳ በግንበሩ ገጭቶ ለማስቆጠር ቢቃረብም ዳንኤል ተሾመ አድኖበታል።

 በተቃራኒው ጎል ግን አዲስ አበባዎች በተመሳሳይ የግንባር ጎል ምላሽ ሰጥተዋል። 45ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለ ከግራ መስመር ያሻመውን ኳስ ፍፁም ጥላሁን በግንባር ሲሞክር ሰለሞን ደምሴ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ ሪችሞንድ ኦዶንጎ ሦስተኛ ጎል አድርጎታል።

ከዕረፍት መልስ ሰበታዎች የማጥቃት ኃይላቸውን ለማጠናከር ሳሙኤል ሳሊሶ እና በኃይሉ ግርማን ቀይረው አስገብተዋል። ሆኖም ጨዋታው በአዲስ አበባ ከተማ የማጥቃት ጫና የቀጠለ ነበር።

 በዚህም ቡድኑ 53ኛ ደቂቃ ላይ የግንባር ጎል ፌሽታውን ቀጥሏል። ሙሉቀን አዲሱ ከቀኝ መስመር ያሻገረው ኳስ ከነጠረ በኋላ ሪችሞንድ ኦዶንጎ ደርሶ በግንባሩ የሰበታ መረብ ላይ አሳርፎታል።

ከፍተኛ ንፋስ የቀላቀለ ዝናብ ያጀበው ጨዋታ በእንቅስቃሴ ደረጃ ወደ መመጣጠኑ ቢመጣም ቡድኖቹ የመጨረሻ የግብ ዕድል የሚፈጥሩባቸው ቅፅበቶች በቁጥር ቀንሰዋል። ነገር ግን 67ኛው ደቂቃ ላይ ያለቀ ይመስል የነበረውን ጨዋታ ያነቃቃ ጎል ከሰበታ በኩል ተገኝቷል። ፍፁም ገብረማሪያም ራሱ ያስጀመረውን ጥቃት ተከትሎ ጌቱ ኃይለማሪያም ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሳጥን ውስጥ በመገኘት በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ አክርሮ በመምታት ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አድርጎታል።

የዝናቡ መጠን ጨዋታው 70ኛውን ደቂቃ ካለፈ በኋላ ጨምሮ ታይቷል። አዲስ አበባዎች የሰበታን የማጥቃት ጥረት ተከትሎ ከኋላ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለመጠቀም የሚሞክሩበት እንቅስቃሴ ከመታየቱ በቀር የግብ ሙከራዎች ረግበው ቆይተዋል። ጨዋታው ሊፈፀም ሲቃረብ ግን 88ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳሊሶ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት አዲስ አበባን ወደ ሌላ ውጥረት ያሸጋገረች ጎል አስቆጥሯል። በቀሪ ደቂቃዎች የመዲናዋ ክለብ ተጫዋቾች ተጨማሪ ጎል ላለማስተናገድ ኳስን ከግብ ክልላቸው በማራቅ ተጠምደው በ4-3 ድል ለመጨረስ ችለዋል።

ውጤቱን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማ ነጥቡን 32 በማድረስ ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሰበታ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ከሊጉ መሰናበታቸው እርግጥ ሆኗል።