ከሰሞኑ ውዝግብ ውስጥ ገብተው የነበሩት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር ወደ ስምምነት መጥተዋል።
የወልቂጤ ከተማው አምበል ጌታነህ ከበደ ላይ የሊግ ካምፓኒው ባስተላለፈው የሦስት ጨዋታ ቅጣት መነሻነት ባሳለፍነው ሳምንት በክለቡ ፣ በሊጉ እና በፌዴሬሽኑ ዙሪያ ተከታታይ ዜናዎች ሲወጡ ሰንብተዋል።
ከሁሉም ከፍ ያለ ትኩረት ያገኘው ደግሞ የተጨዋቹን ይግባኝ ተከትሎ ቅጣቱ ይነሳለት በማለት ፍርድ የሰጠው የእርግኳስ ፌዴሬሽኑ የዲስፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ በሊግ ካምፓኒው ውድቅ የመደረጉ ጉዳይ ነበር። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህንን ተከትሎ ‘ለአክሲዮን ማህበሩ የሰጠሁት የዲስፕሊን ጉዳዮችን የመመልከት ኃላፊነትን አንስቻለው’ ማለቱም አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ጉዳዩን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ከጠራ በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ ማረዘሙም የነገሩ ቀጣይ መቋጫ ምን ሊሆን እንደሚችል ሲያስጠብቅ የነበረ ጉዳይ ነው። በእርግጥ አክሲዮን ማህበሩ የተወዳዳሪ ቡድን መሪዎችን እሁድ ዕለት ሰብስቦ አቋሙን የገለፀ ሲሆን ከሁለቱ አካላት የሚወሰድ ቀጣይ እርምጃም ሆነ የሚሰጥ አዲስ አተያየት ሲጠበቅ ነበር። ማምሻውን ያገኘነው መረጃ ግን በሁለቱ የእግርኳስ አካላት መካከል የተፈጠረው ክፍተት ፈር መያዙን ያመላክታል።
የሁለቱ ተቋማት አመራሮች ጉዳዩን አስመልክተው ያደረጉት ውይይት ጥሩ ውጤት ማስገኘቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሊግ ካምፓኒው ከቢጫ እና ቀይ ካርድ ውሳኔዎች በቀር ያሉ የዲስፕሊን ጉዳዮችን እንዳይመለከት ያዘዘበትን ውሳኔ በመቀየር በቀደመ ኃላፊነቱ የሊጉን ጨዋታዎች የተመለከቱ የዲስፕሊን ጉዳዮችን የመመልከት ኃላፊነቱን ይዞ እንዲቀጥል ከውሳኔ ላይ መድረሱን ለማወቅ ችለናል።