በደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ አስጥሎ የዋንጫውን ፉክክር አጓጊ አድርጓል።
ባሳለፍነው ሳምንት ከሰበታ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ዛሬ ሁለት ተጫዋቾችን ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም ፍሬዘር ካሣን በቃለአብ ውብሸት እንዲሁም አበባየሁ ዩሐንስን በሚካኤል ጆርጅ ተክተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው ወልቂጤ ከተማን ከረታው ስብስባቸው በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ የሆነው አቤል እንዳለን ብቻ በዳግማዊ አርአያ ለውጠው ጨዋታውን ቀርበዋል።
ከሁለቱ ተጋጣሚዎች ውጪ የበርካታ ክለብ ደጋፊዎች በትኩረት የሚመለከቱት ጨዋታ ውጥረት ነግሶበት ጥፉ ፉክክር ማሳየት ጀምሯል። በአንፃራዊነት የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ከመዓዘን ምት መነሻን ካደረጉ ኳሶች መሪ ለመሆን ሲጥሩ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ የጊዮርጊስን የኳስ ቅብብል እያጨናገፉ ፈጣን ሽግግሮችን በማድረግ ቀዳሚ ለመሆን ተንቀሳቅሰዋል። ጨዋታው እስከ 30ኛው ደቂቃ መዳረሻ ድረስ ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል ባይስተናገድበትም ሁለቱም ጥሩ ያለመሸነፍ ስሜት አሳይተው ታታሪነት የተሞላበት አጨዋወት ተከትለው ተንቀሳቅሰዋል።
29ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ የቀረበው የመጀመሪያ ሙከራ ከመደረጉ ከ9 ደቂቃዎች በፊት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል ግማሽ የግብ ማግባት አጋጣሚ ፈጥረው ተመልሰዋል። በጠቀስነው ደቂቃ ግን በረከት ወልዴ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ የተከላካዩ ፍሬዘር ካሣን ግንባር እንዲሁም የግብ ዘቡን መሳይ አያኖን ጣቶች ነክቶ አግዳሚውን በመግጨት ወደ ውጪ ወጥቷል። ይህ ሙከራ የበለጠ ያነቃቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ36ኛው ግብ አግኝተዋል። በዚህም ሱሌይማን ሀሚድ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ራሱን ነፃ አድሮጎ በተከላካዮች መሐል ቆሞ የነበረው አማኑኤል ገብረሚካኤል በግንባሩ መረብ ላይ አሳርፎታል።
ከግቡ በኋላም ጥቃት መሰንዘራቸውን የቀጠሉት ፈረሰኞቹ ሁለት ያለቀላቸው አጋጣሚዎችን ፈጥረው ነበር። በቅድሚያ በ42ኛው ደቂቃ የግራ መስመር ተከላካዩ ሔኖክ አዱኛ ፈጣን የመስመር ላይ ሩጫ በማድረግ ሙከራ አድርጓል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ይሁ ተጫዋች ያሻማውን የመዓዘን ምት ቸርነት ጉግሳ የተከላካዩ ፍሬዘርን ትከሻ አስነክቶ ወደ ግብ የላከውን ኳስ መሳይ አያኖ በጥሩ ቅልጥፍና አድኖታል። በአጋማሹ ደቂቃዎች እየተቆጠሩ በሄዱ ቁጥር እየወረዱ የመጡት ሀዲያ ሆሳዕናዎች አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛውን አጋማሽም በተሻለ ተነሳሽነት የጀመሩት የአሠልጣኝ ዘሪሁን ተጫዋቾች ገና በጊዜ በግብ አስቆጣሪው አማኑኤል አማካኝነት ሁለት አጋጣሚዎችን ፈጥረው ተመልሰዋል። ሀዲያዎች በበኩላቸው የማጥቃት አጨዋወታቸውን በተጫዋች እና በቅርፅ በመለወጥ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረዋል። በተለይ በ57ኛው ደቂቃ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ከቀኝ መስመር ኳስ እየገፋ ተጫዋቾችን በማለፍ ከግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ጋር ተገናኝቶ ቋሚው የመለሰበት አጋጣሚ ቡድኑን አቻ ለማድረግ ከጫፍ የደረሰ ነበር። ይህ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ ከተደረገ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ባዬ በግንባሩ ሌላ ሙከራ አድርጎ ነበር።
ጨዋታው 66ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን ወደ ሁለት ከፍ ሊያደርግ ነበር። በዚህም በግቡ ላይ የተቀናጁት ሱሌይማን እና አማኑኤል ዳግም ተጣምረው የተገኘውን አጋጣሚ አጥቂው በጥሩ እርጋታ ተከላካዮችን አልፎ በግብ ጠባቂው እግሮች ስር ቢልከውም ፍሬዘር ኳስ የግቡን መስመር እንዳታልፍ አድርጓል።
በዚህኛው አጋማሽ የተሻሉት ሀዲያዎች በ80ኛው ደቂቃ አቻ ሆነዋል። በዚህም 70ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ አለባቸውን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ኤፍሬም ዘካሪያስ ከመዓዘን ምት የተሻማውን ኳስ በቅርቡ ቋሚ ሆኖ በቀጥታ ወደ ግብነት ቀይሮታል። በቀሪ ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሙሉ ሀይላቸው ለማጥቃት ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ቡድኖቹ ደረጃቸው ላይ ለውጥ ባያስመዘግቡም ሀዲያ ሆሳዕና 35 ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ 59 ነጥቦችን በመያዝ በቅደም ተከተል የደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ እና መሪ ቦታ ላይ ተቀምጠዋል።