የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ ቀን ሦስት መርሐ-ግብሮች ላይ የሚያጠነጥነው ዳሰሳችን እንደሚከተለው ተሰናድቷል።
አርባምንጭ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አንዱንም ያልተረቱት አርባምንጮች በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛሉ። በተለይ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በድምሩ አምስት ግቦችን አስቆጥረው ያሸነፉበት ጨዋታ ምን ያህል ጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ያመላክታል። ከወትሮ በተለየ የኳስ ቁጥጥር ላይ በመጠኑ ፍላጎት እና ቀጥተኛ የማጥቃት አጨዋወቱ ላይ ፍጥነት የጨመረው ስብስቡ የተጋጣሚን ክፍተቶች እንዲሁም ስህተቶች የማይምር ሆኗል። በሁለቱ ጨዋታዎች ሦስት የፍፁም ቅጣት ምት ጎሎችን ቢያስቆጥርም በመልሶ ማጥቃቶች እና በተሻጋሪ ኳሶች የሚገኙ ዕድሎችን ወደ ግብነት የቀየረበት አፈፃፀም እጅግ ተሻሽሏል። የነገው ተጋጣሚ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ለቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት የተመቸ የመከላከል ቅርፅ ሁኔታን ስለሚፈጥር ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በዋናነት ደግሞ ምርጥ ብቃቱን ያገኘ የሚመስለው ኤሪክ ካፓይቶ የቡና ተከላካዮች ወደ መሐል ሜዳ ገፋ ብለው ሲጫወቱ የሚገኙ ቦታዎችን ይጠቀማል ተብሎ ይታሰባል። በመጀመሪያው ዙር እንደታየውም በጥሩ መታተር የቡናን የኳስ ምስረታ እያጨናገፉ ወደ ግብነት ለመቀየር እንደሚጥሩ ቀድሞ መናገር ይቻላል።
በመጨረሻዎቹ ስድስት የሊጉ ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 18 ነጥቦች 13ቱን አሳክቶ በደረጃ ሰንጠረዡ ሽቅብ እየወጣ አስተማማኝ ቦታን ያገኘው ኢትዮጵያ ቡና ሦስተኛ ደረጃን ለማግኘት የሚያደርገውን ጥረት ነገም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ይታሰባል። ባሳለፍነው ሳምንት ላለመውረድ ከሚፋለመው አዲስ አበባ ከተማ ጋር ተጫውቶ አቻ የተለያየው ስብስቡ ከበድ ያለ ፈተና ገጥሞት ነበር። ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚደረግ የዘገየ ሽግግር እና በኳስ ምስረታ ወቅት በሚፈጠሩ ስህተቶች የተጋጣሚ ቡድኑ ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራዎች ሲሰነዘሩበት ነበር። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በርከት ያሉ ለግብ የቀረቡ ኳሶች ተሰንዝረውበት ነበር። ይህ ፈተና ነገም በአርባምንጮች በኩል ተጠናክሮ ሊመጣ ስለሚችል ጥንቃቄ ይሻል። በነገው ጨዋታ የሁሉ ነገር የትኩረት መሐከል የሚሆነው አቡበከር ናስር ነው። ለኢትዮጵያ ቡና የመጨረሻ ጨዋታውን የሚያደርገው ምትዐተኛው በመጨረሻ ጨዋታው ጥሩ ትዝታ እንዲኖረው የሚያደርገው እንቅስቃሴ እና ለከፍተኛ ግብ አስቆጣሪበት የሚያደርገው ጥረት ለአዞዎቹ የሜዳ ላይ ፈተናን እንደሚያበዛ ይገመታል።
አርባምንጭ ከተማ አምበሉ ወርቅይታደስ አበበ እና ግብ ጠባቂው ሳምሶን አሰፋን በጉዳት ምክንያት ሲያጣ ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና ግን ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና እንደሌለበት ተመላክቷል።
የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው ፣ ረዳቶች ተመስገን ሳሙኤል እና ሸዋንግዛው ከበደ ፣ አራተኛ ዳኛ አባይነህ ሙላት
ተጨማሪ ዳኞች – ለዓለም ዋሲሁን እና ሸዋንግዛው ተባበል
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ቡናማዎቹ እና አዞዎቹ ከዚህ ቀደም 15 ጊዜ ተገናኝተዋል። በግንኙነቶቹም 5 ጊዜ ኢትዮጵያ ቡና ሲያሸንፍ 6 ጊዜ አርባምንጭ ረቶ አራቱን አቻ ተለያይተዋል። በግብ ረገድ ግን እኩል 15 ጎሎችን እርስ በርስ አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)
ይስሀቅ ተገኝ
ሙና በቀለ – አሸናፊ ፊዳ – በርናንድ ኦቼንግ – መላኩ ኤሊያስ
ሀቢብ ከማል – አቡበከር ሸሚል – እንዳልካቸው መስፍን – ሱራፌል ዳንኤል
አህመድ ሁሴን – ኤሪክ ካፓይቶ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
በረከት አማረ
ያብቃል ፈረጃ – አበበ ጥላሁን – ወንድሜነህ ደረጄ – አስራት ቱንጆ
አማኑኤል ዮሐንስ – አብነት ደምሴ – ታፈሠ ሰለሞን
አቤል እንዳለ – አቡበከር ናስር – አላዛር ሽመልስ
ፋሲል ከነማ ከ ሀዋሳ ከተማ
በዋንጫ ፉክክሩ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ ሊያመጣ የሚችለው የዕለቱ ጨዋታ ከወዲሁ የብዙዎችን ቀልብ ይዟል። በተለይ ዛሬ ከሰዓት የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ሰለጣለ ይህ ጨዋታ ተጠባቂ ሆኗል። የጊዮርጊስን ውጤት ተከትሎ ፋሲል ነገ የሚያሸንፍ ከሆነ በሁለቱ ክለቦች መካከል የሚኖረው የነጥብ ልዩነት አንድ ስለሚሆን የጨዋታው ትርጉም ከፍ ያለ ነው። ይህንን ጨዋታ ፋሲል ብቻ ሳይሆን ሀዋሳ ከተማም ይፈልገዋል። ዘለግ ላሉ ሳምንታት ሦስተኛ ደረጃ ላይ የነበረው ቡድኑ ትናንት ሲዳማ ቡና ሁለት ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ደረጃውን ለመረከብ ስለሚሻ ቀላል ፉክክር ያደርጋል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው።
ያለፉትን አስር የሊጉ ጨዋታዎች ያልተረታው እና በወቅታዊ ብቃት የሊጉ ምርጥ ቡድን የሆነው ፋሲል ከነማ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች እና በሁሉም የጨዋታ ምዕራፎች ብልጫ ለመውሰድ የሚያደርገው እንቅስቃሴ የሚደነቅ ነው። ባሳለፍነው ሳምንት ላለመውረድ ከሚፋለመው እና ዘለግ ያለውን ደቂቃ በህብረት ለመከላከል ከጣረው አዳማ ከተማ ጋር ተጫውቶ ጠንከር ያለ ፈተና ቢገጥመውም በትዕግስት የጨዋታውን ውጤት ወደ ራሱ አምጥቷል። የነገ ተጋጣሚው ሀዋሳ ከተማም በአምስት የኋላ የተጫዋች አደራደር ቅርፅ ወደ ሜዳ ገብቶ በቅድሚያ ለመከላከል ትኩረት የሚሰጥ ስለሆነ ፈተናው ከአዳማ የቀጠለ ክፍል 2 ሊሆን ይችላል። ይህንን ጠበቅ ሊል የሚችል የመከላከል አጨዋወት ደግሞ የሜዳውን የጎንዮሽ ስፋት መጠቀም በሚያዘወትሩ የመስመር አማካዮች እና ተከላካዮች ሩጫ መዘርዘር እንዲሁም በመስመሮች መካከል መግባት በሚደጋግሙ አማካዮች ጨዋታው መወሰን እንደሚሞክር ይታሰባል።
ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቀው ተከታታይ ሦስት ነጥብ ያስመዘገቡት ሀዋሳ ከተማዎች ከድቷቸው የነበረውን ጠንካራ ብቃት ዳግም ያገኙ ይመስላል። በተለይ ደግሞ በቀዳሚ አሰላለፍ ውስጥ ከሚያስገቧቸው 11 ተጫዋቾች ከግማሽ በላዩ በጉዳት ከሜዳ ርቀው ሲቸገሩ ከርመው በወሳኙ የሊጉ ምዕራፍ ማግኘታቸው ትልቅ ጠቀሜታ ይሰጣቸዋል። ባሳለፍነውም ሳምንት በሜዳው እና በደጋፊዎቹ ፊት የተጫወተው ባህር ዳር ከተማን ገጥመው በኳስ ቁጥጥር እና የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ብልጫ ቢወሰድባቸውም ጫናዎችን ዋጥ አድርገው ጨዋታውን በመቆጣጠር ድል ያደረጉበት መንገድ ለነገው ጨዋታ ትልቅ የሥነ-ልቦና ብርታት የሚለግሳቸው ይመስላል። ከምንም በላይ ግን ወቅታዊው የሀዋሳ የልብ ምቶች አጥቂዎቹ ብሩክ በየነ እና ኤፍሬም አሻሞ እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው። በተከታታይ ጨዋታዎች ለቡድናቸው ወሳኝ ግቦችን ያስቆጠሩት ሁለቱ ተጫዋቾች የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው ወደ መሐል ሜዳው ከፍ ብለው የሚከላከሉት የፋሲል የመጨረሻ (ተከላካዮች) ተጫዋቾች ጀርባ የሚገኘውን ቦታ እንደሚያነፈንፉ እና ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረገውን ሽግግር በማፋጠን የግብ ምንጭ ለማድረግ ሊያስቡ ይችላሉ።
ሀዋሳ ከተማ የውድድር ዓመቱን በጉዳት ከወዲሁ ካጠናቀቁት ፀጋሰው ድማሙ እና ወንድማገኝ ማዕረግ ውጪ በነገው ጨዋታ የሚያጣው ተጫዋች የለም።
የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገሁ ፣ ረዳቶች ዳንኤል ጥበቡ እና ወጋየሁ አየለ ፣ አራተኛ ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ
ተጨማሪ ዳኞች – ዘሪሁን ኪዳኔ እና ሙሉነህ በዳዳ
እርስ በርስ ግንኙነት
– ከ2009 በኋላ በ9 ጨዋታዎች ላይ ተገናኝተው ሀዋሳ ሦስት ጊዜ ሲያሸንፍ ፋሲል ሁለት ጊዜ አሸንፏል። በቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሀዋሳ ከተማ 14 ጎሎችን በማስቆጠር ቀዳሚ ሲሆን ፋሲል ከነማ ደግሞ 12 ኳሶችን ከመረብ ጋር አዋህዷል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)
ሚኬል ሳማኪ
ሰዒድ ሀሰን – አስቻለው ጥላሁን – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን
ይሁን እንዳሻው
ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – ሱራፌል ዳኛቸው- በረከት ደስታ
ሙጂብ ቃሲም
ሀዋሳ ከተማ (3-5-2)
መሀመድ ሙንታሪ
ካሎንጂ ሞንዲያ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ
ዳንኤል ደርቤ – አብዱልባስጥ ከማል – ወንድምአገኝ ኃይሉ – በቃሉ ገነነ – መድሃኔ ብርሃኔ
ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ
መከላከያ ከ አዳማ ከተማ
የመውረድ ስጋት አሁንም ያልተላቀቃቸው መከላከያ እና አዳማ ከተማ ነገ በየትኛውም መንገድ ሦስት ነጥብ አሳክቶ በሊጉ ለከርሞ ለመተረረፍ የሚያደርጉት የእርስ በርስ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግበት ይገመታል። ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻሉት መከላከያዎች በወላይታ ድቻው ጨዋታ ጥሩ ቢንቀሳቀሱም ሦስት ነጥብ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። በዋናነት ደግሞ ነጥብ በተጋሩበት የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች በድምሩ 46 ሙከራዎችን አድርገው አንድም ግብ አለማስቆጠራቸው ፊት ላይ የስልነት ችግር እንዳለ ይጠቁማል። ይህ የአጨራረስ ክፍተት ነገ ተቀርፎ ካልመጣ ግን እንደ ሦስቱ ጨዋታዎች በርከት ያሉ የግብ እድሎችን የማይሰጠው አዳማ ስለሚገጥሙ ሊቸገሩ ይችላሉ። በተለይ ግን ቢኒያም በላይ በሚሰለፍበት የግራ መስመር የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት እንደሚያጋድል ይታሰባል። በመከላከሉ ረገድ እምብዛም እንከን የሌለበት ቡድኑ የፈጣኖቹን የአዳማ አጥቂዎች ሽግግር መቆጣጠር በጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት ይጠቅመዋል።
ከመከላከያ የባሰ የመውረድ ስጋት ያለበት አዳማ ከተማ በበኩሉ ከቀሪ ሦስት ጨዋታዎቹ ሁለቱን ከቀጥተኛ ተፎካካሪዎቹ ጋር ማድረጉ ዕድሉን የመወሰን አጋጣሚውን ያሰፋለታል። በእንቅስቃሴ ረገድ ያን ያህል ክፉ ደረጃ ላይ የማይገኘው አዳማ ዋነኛ ችግሩ ግብ ማስቆጠር ነው። በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ከሚገኘው ሰበታ ከተማ በመቀጠል ያነሱ ግቦችን ያስቆጠረው ቡድኑ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ችግር ባይኖርበትም የመጨረስ ግን የበዛ ውስንነት ይታይበታል። አሠልጣኙ ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች በኋላ በሰጡት የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ይህ ችግር የመጣው ከጉጉት እንደሆነ ቢጠቁሙም በወሳኙ ውድድሩ ምዕራፍ በስክነት እና ስልነት የሚገኙ ዕድሎችን መጠቀም ያስፈልጋል። ተጋጣሚው መከላከያም መከላከልን ጠንቅቆ የሚያውቅ ስለሆነ ደግሞ በተደጋጋሚ የግቡ ጫፍ እንዳይደርሱ ሊያደርግ ይችላል። ከጨዋታው ውጤት ለመያዝ ደግሞ በመስመሮች መካከል እና ከተከላካይ ጀርባ ፍጥነታቸውን ተጠቅመው አዘውትረው የሚገኙት አጥቂዎች ብቃት ወሳኝ ይመስላል።
መከላከያ ብሩክ ሰሙን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ የማይጠቀም ሲሆን በአምስት ቢጫ ካርድ ምክንያት ያሳለፍነው ሳምንት ጨዋታ አልፎት የነበረው ኢማኑኤል ላርዬ ግን ዝግጁ መሆኑ ታውቋል። አዳማ ከተማ ደግሞ ሚሊዮን ሰለሞንን ከቅጣት መልስ ሲያገኝ ዳዋ ሁቴሳ ቅጣቱን ባለመጨረሱ ከጨዋታው ውጪ ነው።
የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ አዳነ ወርቁ ፣ ረዳቶች ትግል ግዛው እና አበራ አብርደው ፣ አራተኛ ዳኛ በላይ ታደሰ
ተጨማሪ ዳኞች – ትንሳኤ ፈለቀ እና ሀብተወልድ ካሳ
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በአጠቃላይ በሊጉ 28 ጊዜ ሲገናኙ እኩል 8 ጊዜ ተሸናንፈው ቀሪዎቹን 12 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡ በእነዚህ ግንኙነቶች መከላከያ 20 ግቦች ሲያስቆጥር አዳማ 22 አስመዝግቧል።
ግምታዊ አሰላለፍ
መከላከያ (4-2-3-1)
ክሌመንት ቦዬ
ገናናው ረጋሳ – አሌክስ ተሰማ – አሚን ነስሩ – ዳዊት ማሞ
ኢማኑኤል ላርዬ – ምንተስኖት አዳነ
ተሾመ በላቸው – አዲሱ አቱላ – ቢኒያም በላይ
እስራኤል እሸቱ
አዳማ ከተማ (4-3-3)
ሴኩምባ ካማራ
ጀሚል ያዕቆብ – ሚሊዮን ሰለሞን – አዲስ ተስፋዬ – ደስታ ዮሐንስ
አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ታደለ መንገሻ
አቡበከር ወንድሙ – አብዲሳ ጀማል – አሜ መሐመድ