ሪፖርት | በአቡበከር የመጨረሻ ጨዋታ አዞዎቹ ቡናማዎቹን ረተዋል

አርባምንጭ ከተማዎች በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ያሸነፉበትን ውጤት ኢትዮጵያ ቡና ላይ አስመዝግበዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎል የወሰዱት አርባምንጭ ከተማዎች ተካልኝ ደጀኔን በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ የሆነው ወርቅይታደስ አበበ ተክቶ እንዲገባ ሲያደርጉ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ለዛሬው ጨዋታ የተዘጋጁት ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው አራት ተጫዋቾችን ለውጠዋል። በዚህም በወንድሜነህ ደረጄ፣ ያብቃል ፈረጃ፣ ታፈሰ ሰለሞን እና አቤል እንዳለ ምትክ ገዛኸኝ ደሳለኝ፣ ኃይሌ ገብረትንሣኤ፣ ሮቤል ተክለሚካኤል እና ዊሊያም ቀዳሚ ምርጫ ውስጥ ገብተዋል።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በኢትዮጵያ እግር ኳስ እምብዛም ያልተለመደ ትዕይንት ተከናውኗል። በዚህም ጥር ወር ላይ የደቡብ አፍሪካውን ሀያል ክለብ ማሜሎ ዲሰንዳውን የተቀላቀለው አቡበከር ናስር የመጨረሻ ጨዋታውን ለቡናማዎቹ ለማድረግ ወደ ሜዳ ሲገባ በቡድን አጋሮቹ እና የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች የክብር አሸኛኘት ተደርጎለታል። የክለቡ አመራሮችም ተጫዋቹ በኢትዮጵያ ቡና ቆይታው የሚለብሰው መለያ በፍሬም በስጦታ መልክ አበርክተውለታል።

ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የሁለቱ ቡድኞች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የግብ መከራዎች ሲደረጉበት አልነበረም። በእንቅስቃሴ ደረጃ ኢትዮጵያ ቡና በኳስ ቁጥጥሩ ከፍ ያለ ብልጫ ወስዶ የነበረ ሲሆን አርባምንጭ ከተማ ደግሞ ከኳስ ውጪ በመሆን ስህተቶችን በማነፍነፍ ለመጫወት ሲሞክር ታይቷል። የጨዋታው የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራም በ19ኛው ደቂቃ ተስተናግዷል። በዚህም የጨዋታው የትኩረት መሐከል የሆነው አቡበከር ናስር ከመሀል ሜዳ አብነት የላከለትን ተንጠልጣይ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ተጠቅሞ በግራ እግሩ ግብ ለማስቆጥር ቢሞክርም ዒላማውን ስቶበት ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥርም የግብ ዕድሎች ያልነበሩት ጨዋታው ቀጣዩን ሙከራ ያስተናገደው በ42ኛው ደቂቃ ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም አማኑኤል ዮሐንስ ከሳጥኑ ጫፍ ጠበቅ ያለ ምት ወደ ግብ ልኮ ለጥቂት ወጥቶበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሰከንዶች በሚቀሩት ሰዓት ለመጀመሪያ ጊዜ የቡናማዎቹን ግብ ለመጎብኘት ፍላጎት ያሳዩት አዞዎቹ ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። ቁመታሙ አጥቂ መህመድ ሁሴን ከእንዳልካቸው መስፍን የደረሰውን ኳስ የግብ ጠባቂው በረከት አማረን መውጣት ተከትሎ በብልጠት ከመረብ ጋር አዋህዶታል።

በመጀመሪያ አጋማሽ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ግጥግጥ ብሎ የነበረውን የአርባምንጭ የመከላከል አደረጃጀት ማስከፈት ተስኗቸዋል። እርግጥ የቡድኑ አሠልጣኝ ካሣዬ አራጌ የመከላከል ባህሪ ያለው አማካይ ቀንሰው የአጥቂ አማካይ ቢያስገቡን ውጥናቸው ሊሰምር አልቻለም። ለመጀመሪያ ጊዜም በተሳካ ሁኔታ መስመሩን አልፈው ከግብ ጠባቂው ጋር የተገናኙት በ62ኛው ደቂቃ ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም አቡበከር ከግዙፉ ተከላካይ በርናንድ ኦቺንግ ጋር ታግሎ ሚዛኑን ስቶ የሞከረው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

የተጫዋቾች ለውጦችን በማድረግ ያለ ተፈጥሯዊ የሳጥን ውስጥ አጥቂ መጫወት የቀጠሉት አርባምንጮች በ69፣ 75 እና 76ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ሊያሳድጉ ነበር። በቅድሚያ መላኩ ኤሊያስ ከቀኝ መስመር ጠበቅ ያለ ምት ሲመታ በመቀጠል ደግሞ አቡበከር ሻሚል እና ተቀይሮ የገባው አሸናፊ ኤሊያስ ሌላ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አከታትለው ሰንዝረው በረከት አማረ አድኖባቸዋል።

በቀሪ ደቂቃዎች ከጨዋታው አንዳች ነገር ይዞ ለመውጣት መጣጣራቸውን የቀጠሉት ቡናማዎቹ በ78 እና 79ኛው ደቂቃ በአስራት ቱንጆ እንዲሁም አቡበከር አማካኝነት ሙከራዎችን ሰንዝረው ተመልሰዋል። ከሁለቱ ሙከራዎች በተጨማሪ አስራት በ81ኛው ደቂቃ የመታው ኳስ ለግብነት የተቃረበ ቢሆንም የግብ ዘቡ ይሳቅ ተገኝ አምክኖታል። የብዙዎች ትኩረት የነበረው አቡበከርም በድጋሜ በ84ኛው ደቂቃ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ቡድኑን አቻ ለማድረግ ቢጥርም ሳይሳካለት ቀርቷል። ጨዋታውም በአርባምንጭ አሸናፊነት ፍፃሜውም አግኝቷል።

ውጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ ከተማ ነጥቡን 40 ያደረሰ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በአንድ ነጥብ እና ደረጃ ከፍ ብሎ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።