ሪፖርት | ዐፄዎቹ ከመሪው ያላቸው የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ቀንሰዋል

እጅግ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን የፋሲል ከነማ እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ፋሲሎች በመጂብ ቃሲም ብቸኛ ግብ በድል መወጣታቸውን ተከትሎ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ በመቀነስ የመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ይበልጥ እንዲጠበቁ አድርገዋል።

ፋሲል ከነማዎች አዳማ ከተማን ከረታው ስብስብ ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች ያሬድ ባየህ እና ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስን በከድር ኩሊባሊ እና በዛብህ መለዮ የተኩ ሲሆን በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ ከባህር ዳር ከተማን የረታውን ስብስብ ሳይለውጡ በዛሬው ጨዋታ ተጠቅመዋል።

ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ በጀመረው ጨዋታ ፋሲል ከነማዎች ገና በ3ኛው ደቂቃ በረከት ደስታ ከተከላካይ ጀርባ የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ባደረጋት እና ለጥቂት ወደ ውጪ በወጣችበት ሙከራ የሀዋሳን ግብ ክልል መጎብኘት የጀመሩ ሲሆን በ5ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ ከተከላካይ ጀርባ የደረሰውን ኳስን ተጠቅሞ ሙጂብ ቃሲም ከሀዋሳ ተከላካዮች አምልጦ በመሄድ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በመሀመድ ሙንታሪ መክኖበታል። 9ኛው ደቂቃ ላይ ግን የፋሲሎች ጥረት ፍሬ አፍርቷል። ሱራፌል ዳኛቸው ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት ዐፄዎቹን ገና በማለዳ ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ በኋላ በተሻለ ፍላጎት ጫና ፈጥረው መጫወት የቀጠሉት ፋሲሎች በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ብልጫ በመውሰድ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። በዚህም በተለይ በ16ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ ከቀኝ የሳጥን ጠርዝ ያሻማውን ኳስ በሀዋሳ ተከላካዮች አለመናበብ የተፈጠረውን ዕድል ተጠቅሞ በረከት ደስታ ያደረገው ሙከራ በመሀመድ ሙንታሪ ቅልጥፍና ድኖበታል።

በጨዋታው በተወሰነ መልኩ በመልሶ ማጥቃት የመጫወት ፍላጎት ይዘው የገቡት ሀዋሳ ከተማዎች የመጀመሪያ ሙከራቸውን በ18ኛው ደቂቃ አስመዝግበዋል። በዚህ ሂደት ብሩክ በየነ በፋሲል ሳጥን ውስጥ ከቡድን አጋሩ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ቢሞክርም ሚክኤል ሳማኪ አድኖበታል።

በ21ኛው ደቂቃ ላይ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ተከላካዩን ካሎንጂ ሞንዲያን አስወጥተው በምትኩ አጥቂውን መስፍን ታፈሰ በማስገባት ጨዋታውን ከጀመሩበት የኋላ ሦስት ተከላካዮች ወደ አራት ተከላካይ በመመለስ በፊት መስመራቸው ላይ ተቀይሮ የገባውን መስፍን ታፈሰን ከብሩክ በየነ እና ኤፍሬም አሻሞ ጋር በማጣመር ለመጫወት ሞክረዋል። በዚህም ከለውጡ በኋላ ሀዋሳ ከተማዎች በተሻለ መልኩ በጨዋታው ኳሶችን በማንሸራሸር ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመጠጋት ጥረት ቢያደርጉም ይህን ሂደት ግን ማስቀጠል ሳይችሉ ቀርተዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ፋሲሎች ፍፁም የሆነ የበላይነት የነበራቸው ቢሆንም የመሀመድ ሙንታሪ ድንቅ ብቃት ሀዋሳዎች በጨዋታው እንዲቆዩ አስችሏቸዋል። በ34ኛው ደቂቃ በረጅሙ የተላከን ኳስ ፀጋአብ ዮሴፍ መቆጣጠር አለመቻሉን ተከትሎ በረከት ደስታ የተፈጠረለትን ዕድል ተጠቅሞ በአስደናቂ ሁኔታ በማፈትልክ ሀዋሳ ሳጥን ውስጥ ከደረሰ በኋላ በግራ አግሩ ያደረገው ድንቅ ሙከራ እንዲሁም በተመሳሳይ ከደቂቃዎች በኋላ በረከት ደስታ ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ከድር ኩሊባሊ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ የላከውንም ኳስ በተመሳሳይ መሀመድ ሙንታሪ በድንቅ ብቃት አድኖበታል። በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ በተመሳሳይ ከቀኝ መስመር ከተሻማ ኳስ በረከት ደስታ ያቀበለውን ያለቀለት ኳስ ሙጂብ አስቆጥረ ተብሎ ሲጠበቅ ባመከናት ኳስ ነበር ፍፃሜውን ያገኘው።

በፋሲል ከነማዎች በኩል በተፈጠሩ አስደንጋጭ አጋጣሚዎች የጀመረው ሁለተኛ አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ፋሲሎች ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩበት ነበር። በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በተለይ ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄዱ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ለመያዝ ቢሞክሩም እንደ ፋሲል ሁሉ በሙከራዎች ረገድ ግን ቀዝቃዛ አጋማሽ አሳልፈዋል። በሂደት እየተዳከመ የመጣውን የቡድኑን ማጥቃት ለማነቃቃት አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ዓለምብርሃን ግዛው ፣ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ እና ተክተው በማስገባት የተሻለ ጥረት ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም በ70ኛው ደቂቃ ኦኪኪ አፎላቢ ከሽመክቱ ጉግሳ የደረውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ተቀብሎ ከዞሮ በኋላ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በመሀመድ ሙንታሪ በቀላሉ ከተያዘበት አጋጣሚ ውጪ ሙከራ ለማድረግ የተቸገሩበት ነበር።

በጨዋታው በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ይበልጥ ጫና ፈጥረው የአቻነቷን ግብ ማሰስ የጀመሩት ሀዋሳ ከተማዎች በ73ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በየነ በግሩም ሁኔታ በርከት ባሉ የፋሲል ተጫዋቾች መካከል ያሳለፈለትን ኳስ መስፍን ታፈሰ በአስገራሚ መልኩ ዞሮ በግራ እክርሮ መሬት ለመሬት ጠንካራ ሙከራ አድርጎ ኳስ የግቡን ቋሚ ታካ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥታለች። በተለይ በመጨረሻዎች 10 ደቂቃዎች ይበልጥ ጫና ለመፍጠር ሙከራ ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎች በተደጋጋሚ ኳሶችን ወደ ፋሲል ሳጥን በማድረስ ግብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ የቀረ ሲሆን በአንፃሩ ፋሲሎች በግሩም የመከላከል ትጋት ከጨዋታው ወሳኙን ነጥብ ይዘው ለመውጣት በቅተዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ 58 ያደረሱት ፋሲል ከነማዎች ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ሲያጠቡ በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በ42 ነጥብ በነበሩበት የ4ኛ ደረጃ ቀጥለዋል።