ፋሲል ከነማዎች ወሳኝ ድል ካስመዘገቡበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ – ፋሲል ከነማ
ስለድሉ አስፈላጊነት
“በጣም ጠንካራ ከነበረው ጨዋታ አስፈላጊ ሦስት ነጥብ አግኝተናል ፤ የተፈጠሩ ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም አለመቻላችን በኋላ ላይ ጫና ውስጥ ከቶን የነበረ ቢሆንም ነጥቡን ማሳካታችን ደስተኛ አድርጎኛል።
ስለሱራፌል እና ሙጂብ ጥምረት
“ሙጂብ በጣም ሁለገብ ተጫዋች ነው ምናልባት ቀጣይ ግብ ጠባቂ ልንጠቀመው እንችላለን።
ስለቀጣይ ሁለት ጨዋታዎች
“ሁሉም ጨዋታዎች ወሳኝ ናቸው ፤ ከፈጣሪ ጋር የሚሆነውን እናያለን።”
ስለዕቅዱ ትግበራ
“በፈለግነው መንገድ እየሄደልን ነው። ከዚህ በላይ ይሄዳል ብዬ አስባለሁ ነገር ግን ለጊዜው ያለው ነገር በቂ ነው።”
አሰልጣኝ ዘርዓይ መሉ – ሀዋሳ ከተማ
ስለጨዋታው
” ሳይጠበቅ ግብ አስናግደናል ፤ ጨዋታውን በሦስት ተከላካይ ነበር የጀመርነው በዚህም ወጣቱ ተከላካይ ከልምድ ማነስ በሰራው የአቋቋም ስህተት ግብ አስተናግደናል። ከዚያም የአደራደር ለውጥ አድርገን በመስመር በኩል የነበረውን የነሱን ማጥቃት በተሻለ ለመከላከል ጥረት አድርገናል አጋማሹን ጨርሰናል። ከዕረፍት በኋላ ግን ይበልጥ አጥቅተን ለመጫወት ጥረት አድርገናል። የተሻሉ ዕድሎችን
ፈጥረን መጠቀም አልቻልንም። በአንፃሩ እነሱ ግን ያገኙትን አጋጣሚ መጠቀማቸው ባለድል አድርጓቸዋል።”
ስለካሎጂ ሞንዴያ ፈጣን ቅያሬ
“ባልተሰበ ሰዓት በተቆጠረ ግብ የመጀመሪያ ዕቅዳችን ፈርሶብናል ፤ ስለዚህ ይበልጥ አጥቅተን ለመጫወትም ሆነ ግራ እና ቀኝ የነበረውን የእነሱን ማጥቃት ለመቆጣጠር የአደራደር ለውጥ አድርገናል ታክቲካል ቅያሬ እንጂ ልጁ ስህተት ሰርቶ አይደለም።”