28ኛው ሳምንት ደካማ ፉክክር በታየበት እና 0-0 በተጠናቀቀው የመከላከያ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ ተቃጭቷል።
መከላከያ ከወላይታ ድቻ ያለግብ ከጨረሰበት ጨዋታ ከአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት የተመለሰው ኢማኑኤል ላሪያን በኢብራሂም ሁሴን ምትክ በመጀመሪያ አሰላለፉ ውስጥ አካቷል። አዳማ ከተማዎች ደግሞ ከፋሲሉ ሽንፈት ባደረጓቸው ለውጦች ከቅጣት የተመለሰው ሚሊዮን ሰለሞንን በእዮብ ማቲያስ ፣ ፀጋአብ ዮሐንስን በዮናስ ገረመው እና ወሰኑ ዓሊን በአቡበከር ወንድሙ ቦታ አሰልፈዋል።
በመከላከያ የተሻለ የማጥቃት የበላይነት የጀመረው ጨዋታ የተቀዛቀዘ አጋማሽ አሳይቶናል። ጦሩ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመያዝ እና የተነጠቁ ኳሶችን በመጠቀም ወደ አዳማ የግብ ክልል የቀረበባቸው አጋጣሚዎች የነበሩ ቢሆንም ሳኩባ ካማራን የፈተነ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻለም። በቢኒያም በላይ ፣ እስራኤል እሸቱ እና ምንተስኖት አዳነ ቡድኑ ከሳጥኑ ዙሪያ ያደረጋቸው ሙከራዎች ኢላማቸውን ያልጠበቁ ወይም በአዳማ ተከላካዮች የተደረቡ ሆነው አልፈዋል። አዳማ ከተማዎችም ከቆሙ ኳሶች እና ከቀጥተኛ ጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም አደጋ በሚፈጥር ኳስ ሳጥን ውስጥ የተገኙት 26ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። በዚህም አማኑኤል ጎበና ለአሜ መሐመድ ባሳለፈው ኳስ ለግብ ቢቀርቡም አሚን ነስሩ አሜ የግብ ዕድል ለመፍጠር ያደረገውን ጥረት በሸርተቴ አክሽፏል።
ከውሃ ዕረፍቱ በኋላ ጨዋታው የበለጠ ዝግ ያለ እንቅስቃሴ ተስተውሎበታል። አዳማ የተሻለ ለማጥቃት ሲሞክር ቢታይም ጨዋታው በአመዛኙ በሁለቱ ሳጥኖች መሀል ተገድቦ ቆይቷል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ግን በሁለቱ የግብ አቅጣጫዎች የተሻሉ ሙከራዎች ተደርገዋል። 44ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዮሐንስ ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ በክሌመንት ቦዬ ሲድንበት ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ እስራኤል እሸቱ ከግማሽ ጨረቃው ላይ ወደ ቀኝ ያሳለፈለትን ኳስ ተሾመ በላቸው ነፃ ሆኖ አክርሮ ወደ ግብ ቢልከውም በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል።
ሁለተኛው አጋማሽ መከላከያ በእስራኤል እሸቱ ከሳጥን ውጪ አዳማ ደግሞ በፀጋአብ ዮሐንስ ከሳጥን ውስጥ ባደረጓቸው ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች የተነቃቃ አጀማመር ቢያደርግም ተመልሶ ወደ መቀዛቀዙ ሄዷል።
አንዳቸው የሌላኛቸውን የማጥቃት ሂደቶች በማቋረጥ በቀጠለው ጨዋታ በቀጣይነት ያየነው የግብ ሙከራ 74ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተላከ እና አሜ መሐመድ የጨረፈውን ኳስ አብዲሳ ጀማል ሳጥን ውስጥ አሌክስ ተሰማን አልፎ ወደ ግብ ሲሞክር እና በአሚን ነስሩ ሸርተቴ ሲድን ነበር። በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች መከላከያዎች በጥልቀት መከላከልን ሲመርጡ አዳማ ከተማዎች የተሻለ የማጥቃት ጫናን ቢፈጥሩም ጨዋታው ግብም ሆነ ሌላ አደገኛ ሙከራን ሳያስመለክተን ያለግብ ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ መከላከያ 34 አዳማ ከተማ ደግሞ 31 ነጥብ ላይ ሲገኙ አዳማ ከተማ በሊጉ መቆየቱን ለማረጋገጥ በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ እንዲመረኮዝ ሆኗል።