የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ውድድሮችን በተመለከተ መረጃዎች ወጥተዋል

የአህጉራችን ታላላቆቹ የክለቦች ውድድሮችን በተመለከተ የውድድሩ የበላይ አካል የክለቦች እና የተጫዋቾች ምዝገባ እንዲሁም የውድድሮቹን ቀናት መረጃዎች ይፋ አድርጓል።

የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ በየአመቱ የሀገራት የሊግ አሸናፊዎች እና ሁለተኛ የወጡ እንዲሁም የጥሎ ማለፍ ባለድሎችን እንደየሀገሮቹ የውስጥ ሊግ ህጎች እያሳተፈ እንደሚገኝ ይታወቃል። ሀገራችን ኢትዮጵያም በየትኛው ውድድድ የትኛው ክለብ እንደሚሳተፍ ባታውቅም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ በውድድሮቹ እንደሚወክሏል መረጋገጡ ይታወቃል። የውድድሩ የበላይ አካል ካፍ የ2022/23 አህጉራዊውን ፍልሚያ በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎችን ከሰዓታት በፊት ይፋ አድርጓል።

በወጣው መረጃ ላይ በቅድሚያ የተቀመጠው በሁለቱም ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ክለቦችን ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የሚያስታውቁበት ቀን ወደ ሐምሌ 24 (ጁላይ 31) መገፋቱ ነው። በመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ዙር የሚካፈሉ ክለቦች የሚጠቀሙባቸውን ተጫዋቾች የሚያስገቡበት ቀን ደግሞ ከሐምሌ 25-ነሐሴ 9 ድረስ መሆኑ ተጠቁሟል።

በካፍ የክለቦች ውድድር ደረጃ የመጀመሪያ 12 ቦታዎችን የያዙት አልጄሪያ፣ አንጎላ፣ ዲ አር ኮንጎ፣ ግብፅ፣ ጊኒ፣ ሊቢያ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ እና ቱኒዚያ በሁለቱም ውድድሮች ሁለት ሁለት ተሳታፊ ክለቦችን እንደሚወክሉ ይታወቃል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎቹ ሀገራት ግን እንደየደረጃቸው ከመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጀምሮ ጨዋታዎችን እያደረጉ ለዋናው ውድድር የሚበቁ ይሆናል።

የመጀመሪያው ቅድመ ማጣሪያ የሜዳ/ከሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ከጿጉሜ 4-መስከረም 1/ መስከረም 6-8 ሲደረጉ ሁለተኛው የቅድመ ማጣሪያ የሜዳ/ከሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ደግሞ መስከረም 27-29/ ጥቅምት 4-6 ድረስ እንደሚከናወን የወጣው መርሐ-ግብር ያስታውቃል። ከቻምፒየንስ ሊግ ሁለተኛው ቅድመ ማጣርያ የወደቁ ክለቦች ደግሞ በኮንፌዴሬሽን ካፕ ከጥቅምት 23-30 ተጨማሪ የማጣሪያ ጨዋታዎችን የሚያደርጉ ይሆናል። የተጠቀሱትን ዙሮች ያለፉ ክለቦች ከታህሣስ 23-ጥር 23 ድረስ ተጨማሪ የተጫዋቾች ምዝገባ አከናውነው የካቲት 3-5 የመጀመሪያ ጨዋታ ማድረግ ወደሚጀምረው ዋናው ውድድሩ እንደሚያመሩ ተመላክቷል።

ክለቦች በውድድሩ የሚጠቀሙባቸውን 40 ተጫዋቾች ማስመዝገብ ሲችሉ በተጠባባቂ ወንበር ላይ 9 ተጫዋቾችን አድርገው በጨዋታ 5 ተጫዋቾችን የመቀየር መብት እንዳላቸው ተጠቁሟል።