ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 28ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የመጀመሪያው ፅሁፋችን ትኩረት የሚያደርገው በጨዋታ ሳምንቱ ትኩረት በሳቡ ክለብ ነክ ጉዳዮች ላይ ይሆናል።

👉 ፈረሰኞቹ አሁንም ነጥብ ሲጥሉ ዐፄዎቹ መጠጋታቸውን ቀጥለዋል

ከጥቂት ጨዋታዎች በፊት ለ15ኛ የሊግ ዋንጫ እጅጉን ቀርበው የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አሁን ላይ ግን ከተከታያቸው ፋሲል ከነማ ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩ ወደ አንድ ነጥብ ጠቧል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕናን የገጠሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አንድ አቻ ተለያይተው አሁንም ነጥብ ለመጣል የተገደዱ ሲሆን በአንፃሩ ፋሲል ከነማዎች በተመሳሳይ ከሀዋሳ ከተማ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ጠንካራ ፈተና ቢገጥማቸውም ከጨዋታው ወሳኝ ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል።

በወሳኙ የሊግ ምዕራፍ እርግጥ ሁሉም ተጋጣሚ ለራሱ ህልውና ሲል የአቅሙን ሰጥቶ እንደሚጫወት የሚጠበቅ ቢሆንም ፈረሰኞቹ ከ23ኛው የጨዋታ ሳምንት በኋላ ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ሲያደርጉ በአንዱ ሽንፈት እንዲሁም በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ አስመዝግበዋል። በዚህም ማግኘት ከሚገባቸው አስራ አምስት ነጥብ ውስጥ ማሳካት የቻሉት ስምንት ነጥብ (54%) ብቻ ሲሆን በአንፃሩ ከ23ኛ የጨዋታ ሳምንት በኋላ በስምንት ነጥቦች ርቀው ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲከተሉ የነበሩት ፋሲሎች ደግሞ ከአምስቱ ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ አምስት ነጥብ ሁሉንም (100%) በማሳካት ከመሪው ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ነጥብ ማጥበብ ችለዋል።

አሁንም ቢሆን ፈረሰኞቹ ቀሪ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ ከቻሉ የማንንም ውጤት ሳይጠብቁ የሊጉን ክብር መቀዳጀት የሚችሉ ቢሆንም በቀጣይ ከአርባምንጭ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ጋር በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ነጥብ የሚጥሉ ከሆነ ግን ፋሲል ከነማ አሁን ላይ በገነባው የማሸነፍ ሥነልቦና በቀጣይ ከኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ተመሳሳይ ጉዞን በማድረግ ዋንጫውን ከመንጋጋቸው ለመንጠቅ አድብቶ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።

👉 ሲያጣጥሩ የከረሙት ሰበታ እና ጅማ በመጨረሻም እጅ ሰጥተዋል

ሊጠናቀቅ የ180 ደቂቃዎች ዕድሜ በቀረው ፕሪሚየር ሊጉ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የተመዘገቡ ውጤቶችን ተከትሎ ጅማ አባ ጅፋር እና ሰበታ ከተማ ከወዲሁ ከሊጉ መሰናበታቸውን አረጋግጠዋል።

በ2009 ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉት ጅማ አባ ጅፋሮች በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያቸው በነበረው የ2010 የውድድር ዘመን ከከፍተኛ ሊጉ ባደጉበት ዓመት የሊጉን ክብር በማንሳት የማይረሳ ታሪክን መፃፍ ችለዋል። በዚህም መነሻነት በቀጣዩ የውድድር ዘመን ኢትዮጵያን በመወከል በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግም እንዲሁ የተሳትፎ ታሪክ የነበረው ክለብ ነበር።

ታድያ በ2011 የውድድር ዘመን በተወሰነ መልኩ መታየት የጀመሩት አስተዳደራዊ ህፀፆች በሂደት ክለቡን ለተጫዋቾች ደመወዝ አለመክፈል እና የተጫዋቾች ልምምድ ማቆም ለሚሉ ሀረጎች አቻ ትርጉም እስኪመስል ድረስ ተደጋጋሚ ሂደቶች ሲያስተናግድ ቆይቷል። በዘንድሮም ክረምት በተወሰነ መልኩ የአካሄድ ለውጥ ለማድረግ ያሰቡት የክለቡ አመራሮች ጥቂት ባለልምድ ተጫዋቾችን በርከት ካሉ ወጣት ተጫዋቾች ጋር በማጣመር ለመገንባት ያሰቡት ቡድን በተፈለገው ደረጃ ውጤት ለማምጣት መቸገሩን ተከትሎ ጥቂት የማይባሉ ተጫዋቾችን በውሰት እና በዝውውር በመቀላቀል ለማሻሻል የተደረገው ጥረት መጠነኛ ፍንጮችን ቢሰጥም ቡድኑን ግን ከተፈራው የመውረድ ስጋት ሊታደገው አልቻለም።

በተመሳሳይ በ2011 የውድድር ዘመን ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድባቸው የበላይ ሆነው ለከርሞ የፕሪሚየር ሊግ ተሳትፏቸውን ማረጋገጥ የቻሉት ሰበታ ከተማዎች በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ወጣ ገባ የነበረ የውድድር ዘመን ቢያሳልፉም በመጨረሻዎቹ ጥቂት ጨዋታዎች ባስመዘገቧቸው አዎንታዊ ውጤቶች ሊጉን በአምሰተኛ ደረጃ መፈፀማቸው አይዘነጋም።

ከዚህ ቀደም በአሰልጣኝነት ከመሩት ሦስት አሰልጣኞች በጨዋታ አስተሳሰብም ሆነ የተጫዋቾች ምልመላ ለየት በሚሉት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው እየተመሩ በጀመሩት የውድድር ዘመን በቅድመ ውድድር ጨዋታዎች ላይ የነበረው ውጤታማነት ውድድር ዘመኑን በተስፋ እንዲጀምሩ ቢያስችላቸውም ተስፋቸው ግን በፍጥነት ነበር ወደ እንደ ጉም የተነነው። ረዘም ላሉ ሳምንታት በውጤት ማጣት ጉዞ ውስጥ የሰነበተው ሰበታ በመጨረሻም ወደ ከፍተኛ ሊጉ የሚመለሰውን ደረጃ ይዞ አጠናቋል። እንደ ጅማ አባ ጅፋር ሁሉ የተንከባለለ ያልተከፈለ የተጫዋቾች ደወሞዝ እና ሌሎች አስተዳደራዊ ሁነቶች ጋር እየታገሉ የውድድር ዘመናቸውን ያጠናቀቁት ሰበታ ከተማዎች በተለይ ያለፉትን ጥቂት ጨዋታዎች በቂ ልምምድ ሳይሰሩ ያደረጓቸው ነበሩ።

የሂሳባዊ ስሌት ጉዳይ ሆነ እንጂ ሁለቱ ቡድኖች ላይ የወራጅነት ስጋት ካንዣበባቸው እጅጉን የቆየ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ሁለቱም ቡድኖች መሸነፋቸውን ተከትሎ ከሊጉ የመሰናበታቸው ነገር እርግጥ ሆኗል። ምንም እንኳን በብዙ መመዘኛዎች የክለቡ ዙርያ ያሉ አካላት ሊያስታውሱት የማይፈልጉት ዓይነት የውድድር ዘመን ቢያሳልፉም በቀጣይ ግን ቡድኖቹን ዳግም ወደ ሊጉ ለመመለስ ከተሰሩ ስህተቶች ትምህርት በመውሰድ በከፍተኛ የቁጭት ስሜት ስራዎች ለመጀመር ጊዜው አሁን እንደሆነ ለመጠቆም እንወዳለን።

👉 ባህር ዳር እና አዲስ አበባ ወሳኝ ድል አሳክተዋል

በጨዋታ ሳምንቱ ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ እጅግ ትልቅ ዋጋ በነበራቸው ሁለት መርሃግብሮች ባህር ዳር ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት በሊጉ የመቆየት ተስፋቸው ላይ ብርሃን ፈንጥቀዋል።

በጨዋታ ሳምንቱ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ደጋፊያቸው ፊት በወራጅ ቀጠና ውስጥ የቅርብ ተፎካካሪያቸው የሆኑትን ድሬዳዋ ከተማዎችን የገጠሙት ባህርዳር ከተማዎች በመናፍ ዓወል ብቸኛ ግብ በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው ቀና ያሉበትን ድል ያስመዘገቡ ሲሆን በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማዎች ደግሞ በወራጅ ቀጠናው እየዳከረ ከነበረው ሰበታ ከተማ ጠንካራ ፈተና ቢገጥማቸውም አስቀድመው ባስቆጠሯቸው ግቦች ታግዘው በተመሳሳይ ከወራጅ ቀጠናው ያመለጡበትን ውጤት አስመዝግበዋል።

ባህር ዳር ከተማዎች የስድስት ነጥብ ያህል ዋጋ በነበረው የድሬዳዋ ከተማው ጨዋታ ፍፁም ማጥቃት ላይ መሰረት ያደረገን የተጫዋቾች ምርጫን ይዘው በመቅረብ ተጋጣሚያቸውን ገና ከጅምሩ ጫና ውስጥ በመክተት በ40ኛው ደቂቃ ወደ ግራ ካደላ አቋቋም መነሻ ባደረገ የቆመ ኳስ አጋጣሚ የተፈጠረውን ዕድል የመሀል ተከላካያቸው መናፍ ዓወል በተረጋጋ አጨራረስ በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ የነበረችዋን ግብ ማስቆጠር ችሏል። በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ባህር ዳሮች ከመጀመሪያው በተሻለ በርከት ያሉ ያለቀላቸው የግብ አጋጣሚዎችን ቢያገኙም በተጫዋቾቻቸው ደካማ የውሳኔ አሳጣጥ እና በፍሬው ጌታሁን ድንቅ ብቃት ተጨማሪ ግብ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።
በእርግጥ ድሬዳዋ ከተማዎች በጨዋታው መገባደጃ ላይ ግብ ማስቆጠር ችለው የነበረ ቢሆንም ምክንያቱ በግልፅ በማይታወቅ ሁኔታ መሻሩን ተከትሎ ባህር ዳር እጅግ ወሳኝ የሆነውን ውጤት በእጁ አስገብቷል።

በተመሳሳይ በጨዋታዎች ከተጋጣሚያቸው የተሻለ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ችግር የሌለባቸው አዲስ አበባ ከተማዎች ከወትሮው በተሻለ የማጥቃት አፈፃፀምን ባሳዩበት ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 53 ደቂቃዎች ፍፁም ጥላሁን እና ሪችሞንድ አዶንጎ ባስቆጠሯቸው ሁለት ሁለት ግቦች በድምሩ 4-1 እየመሩ ቢቆዩም ቡድኑ ከትኩረት ማጣት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባስተናገዳቸው ሁለት ግቦች ሦስት ነጥቡን ሊያጣ ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም እንደምንም የነበረውን የአንድ ግብ ልዩነት አስጠብቀው መውጣት ችለዋል። 28ኛ የጨዋታ ሳምንት መጠናቀቁን ተከትሎ ባህር ዳር ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 33 በማሳደግ ወደ 10ኛ ደረጃ መስፈንጠር ሲችሉ በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማዎችም እንዲሁ በ32 ነጥብ ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ ብለው ተቀምጠዋል።

በመጪዎቹ ቀናት ከሰበታ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጋር ቀሪ ሁለት የሊግ መርሃግብር የሚቀራቸው ባህር ዳሮችም ሆኑ ከሲዳማ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ቀሪ ጨዋታ የሚጠብቃቸው አዲስ አበባ ከተማዎች ከሁለት ጨዋታዎች ቢያንስ አንዱን ማሸነፍ በሊጉ ለከርሞ ተካፋይ መሆናቸውን ያረጋግጥላቸዋል።

👉 ወደ ገደል አፋፍ እየተጓዙ የሚገኙት አዳማ እና ወልቂጤ

ሊጠናቀቅ የሁለት የጨዋታ ሳምንታት ዕድሜ በቀረው ፕሪሚየር ሊጉ ሦስተኛው ወራጅ ለመሆን በሚደረገው ያልተፈለገ ፉክክር ውስጥ አዳማ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ በአደገኛ ሰዓት ራሳቸውን አግኝተዋል።

በ31 ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት አዳማ ከተማዎችም ሆኑ በ32 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ ‘በእንቅስቃሴ መጥፎ አይደለንም’ በሚል መፅናኛ ማሳካት የሚገባቸውን ነጥብ በጊዜ መሰብሰብ ባለመቻላቸው በመጨረሻዎቹ ሳምንታት መሰል አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ለመገኘት በቅተዋል።

በውድድሩ በ16 ጨዋታዎች አቻ በመለያየት ወደር የማይገኝለት አዳማ ከተማ ከጅምሩ እስከ 28ኛ ሳምንት ሰባት ጨዋታዎችን ብቻ በመሸነፍ በሊጉ አነስተኛ ሽንፈት ካስተናገዱ አምሰት ቡድኖች ተርታ ቢመደብም አቻዎች ወደ ማሸነፍ መቀየር አለመቻሉ ህልውናውን አጣብቂኝ ውስጥ ከቶበታል። ቡድኑ የአሰልጣኝ ለውጥ ባደረገ ማግስት መጠነኛ የመሻሻል ፍንጭ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ይህን መነቃቃት ማስቀጠል የቻለ አይመስልም።

በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች በ21ኛው የጨዋታ ሳምንት አርባምንጭ ከተማን ከረቱበት ጨዋታ ወዲህ ባደረጓቸው ሰባት የሊግ ጨዋታዎች ውስጥ በአራቱ ነጥብ የተጋሩ ሲሆን በተቀሩት ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ሽንፈትን አስተናግደዋል። በዚህም ማሳካት ከሚገባቸው 21 ነጥቦች ውስጥ ያሳኩት የነጥብ ብዛት አራት ሆኗል። ይህም ከወቅታዊ ብቃት አንፃር ከተመለከትነው በሊጉ ለመቆየት በቂ አይመስልም።

በተመሳሳይ ካሸነፏቸው ጨዋታዎች አንፃር እንኳን ከመዘናቸው ወልቂጤዎች በውድድር ዘመኑ እስካሁን ያሸነፉት የጨዋታ ብዛት ሰባት ሲሆን ይህም እንደ አዳማ ሁሉ ከዝቅተኖቹ ተርታ የሚመደብ ነው። በሊጉ በአንድ ወቅት ወገብ አካባቢ የሚጨርስ ይመስል የነበረውን ቡድን ቀስ በቀስ ወደ ወራጅ ቀጠናው እንዲጠጋ ተገዷል። ሜዳ ላይ በሚያሳዩት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ብዙ ነጋራቸው ተሸፍኖ ሲጓዙ የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች በዚህ ‘የቁርጥ ቀን’ ላይ ግን ባለተጠበቁበት የሊጉ ስፍራ ለመገኘት ተገደዋል።

በመጨረሻ ሁለት የሊጉ መርሃግብሮች ወልቂጤ ከተማ መውረዱን ካረጋገጠው ጅማ አባ ጅፋር እና ወላይታ ድቻ ጋር ጨዋታውን የሚያደርግ ሲሆን አዳማ ከተማዎች ደግሞ የሞት እና የሽረት ያህል ዋጋ ባለው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን ከገጠሙ በኋላ በመጨረሻ ጨዋታቸው ደግሞ ሀዋሳን የሚገጥሙ ይሆናል።

በመሆኑም ሁለቱ ቡድኖች ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በመሆን ሦስተኛው ወራጅ ቡድን ላለመሆን በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ለህልውናቸው ይፋለማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

👉 ወላይታ ድቻ የማሸነፍ ረሀቡን አስታግሷል

ለ990 የጨዋታ ደቂቃዎች ያለድል የዘለቀው የወላይታ ድቻ ጉዞ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከሙሉ ሦስት ነጥብ ጋር ተገናኝቷል።

በ16ኛ የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ስታዲየም ቡድኑ በቃልኪዳን ዘላለም ብቸኛ ግብ ድሬዳዋ ከተማን ከረታ ወዲህ በነበሩት 11 ጨዋታዎች ላይ ሳያሸንፍ ቢቆይም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ጅማ አባ ጅፋርን ከመመራት ተነስቶ በማሸነፍ የድል ረሃቡን አስታግሷል።

በማጥቃቱ ረገድ በሊጉ እጅግ ደካማ አፈፃፀም ካላቸው ቡድኖች አንዱ የሆነው ወላይታ ድቻ ከአዳማ እና ሰበታ ከተማ ቀጥሎ በ21 ግቦች ሦስተኛ ዝቅተኛ ግብ አስቆጣሪው ቡድን ሲሆን በአጠቃላይ ከመጨረሻው የድሬዳዋ ድል መልስ ባደረጋቸው አስራ ሁለት ጨዋታዎች ያስቆጠረው የግብ መጠን አራት መሆኑ የማጥቃት ክፍተቱን በሚገባ የሚያሳይ ቁጥር ነው። ሌላው የወላይታ ድቻ ደካማ የማጥቃት አፈፃፀም ማሳያ የሚሆነው ጅማ አባ ጅፋር ላይ አበባየሁ አጪሶ ያስቆጠራት የመጀመሪያ ግብ ቡድኑ በ21ኛ ሳምንት በፋሲል ከነማ ሲረታ በረከት ወልደዮሐንስ ካስቆጠራት ግብ በኋላ የተገኘች ግብ ስትሆን እንደ አጠቃላይ በጨዋታው ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች በውድድር ዘመኑ በአንድ ነጠላ ጨዋታ ከአንድ በላይ ግብ ያስቆጠረበት አራተኛ አጋጣሚ ሆኖ ማለፉ ነው።

በአንፃሩ ደግሞ ድቻ በመከላከሉ ረገድ ያለው ጥንካሬ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በሊጉ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥሎ በጣምራ ከፋሲል ጋር ሁለተኛው ጠንካራ የመከላከል አወቃቀር ባለቤት የሆነው ወላይታ ድቻ በመከላከሉ ያለውን ጥንካሬ በማጥቃቱ መድገም ችሎ ቢሆን ኖሮ አሁን ላይ ለቻምፒዮንነት ፉክክር ውስጥ ራሱን ማግኘት በቻለ ነበር።