የመጨረሻው የትኩረታችን ክፍል ደግሞ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኩራል።
👉 የመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች እና ዳኝነት
ባህር ዳር ከተማ እና ድሬዳማ ከተማ ያደረጉት የ28ኛ የጨዋታ ሳምንት መርሃግብር እጅግ አወዛጋቢ የነበረ የዳኝነት ውሳኔን የተመለከትንበት ጨዋታ ነበር።
በጨዋታው በ89ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች ያገኙትን የማዕዘን ምት አብዱለጢፍ መሀመድ ያሻማውን ኳስ አቡበከር ኑራ መቆጣጠር አለመቻሉን ተከትሎ ከሩቁ ቋሚ ማማዱ ሲዲቤ ወደ ውስጥ ዳግም በግንባሩ ያሻማውን ኳስ ሱራፌል ጌታቸው በግንባሩ በመግጨት ቢያስቆጥርም ጨዋታውን የመሩት አልቢትር ግቧን ሳያፀድቋት ቀርተዋል።
ለድሬዳዋ ከተማዎች እጅግ አስደንጋጭ የነበረው የዳኛው ውሳኔ ቡድኑን ላለመውረድ በሚያደርገው ፉክክር ካሳጣቸው ወሳኝ ነጥብ ባለፈ የጨዋታው ዳኞች ግቡን ለመሻር የሚያበቃ አንዳች በቂ ምክንያት በሌለበት ይህን ውሳኔ መወሰናቸው በጨዋታ ዳኞቹ ላይ ጥያቄ እንድናነሳ የሚያስገድድ አጋጣሚ ነው።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በውሳኔው ፍፁም ደስተኛ ያልነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ለሊጉ አክሲዮን ማህበር ባቀረቡት አቤቱታ ውስጥ በዋነኝነት “በ28ኛ ሳምንት ከባህርዳር ከተማ ጋር ከመጫወታችን በፊት በደረሰን መረጃ የዳኝነት ስጋት እንዳለብን በደብዳቤ ገልፀን ነበር። በመሆኑም በጨዋታው 89ኛው ደቂቃ ግልፅ ጎል አስቆጥረን እጅግ ውድ ነጥብ ልናገኝ በተቃረብንበት ሰዓት ፌደራል ዳኛ ተፈሪ አለባቸው ምንነቱ ባልታወቀ ምክንያት ጎሉን ሽሮ ቡድናችን ላይ ትልቅ ጉዳት አድርሷል።” የሚል ይገኝበታል።
ሁሉም ነገር በአጉሊ መነፅር በሚታዩበት በዚህ ወሳኝ የሊጉ ምዕራፍ ላይ እንደመገኘታችን በቀጣይ የሊጉን አሸናፊም ሆነ ሌላኛውን ሦስተኛ ወራጅ ቡድንን በመለየት ሂደት በቀጣይ የሚደረጉ ጨዋታዎች ትልቅ ትርጉም ያላቸው ከመሆኑ አንፃር አሁንም ቢሆን በተለይ የዳኝነቱ ነገር ሊታሰብበት ይገባል ስንል እናሳስባለን።
በተለይ ከዳኞች አመዳደብ ጋር በተያያዘ የጨዋታዎችን ክብደት እና ሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት የዳኞች ልምድ እና የጨዋታ አመራር ብቃት እየታየ ዳኞች መመደብ እጅግ አስፈላጊ ይሆናል።
👉 ለሜዳው የተለየ ድባብ የሚያላብሱት የመከላከያ ደጋፊዎች
የመከላከያ ጨዋታዎችን የሚታደም አካል ከሜዳ ላይ የእግር ኳስ ትርዒት ባለፈ ከመዚቃ መሳሪያዎች የሚወጣው ጥዑመ ዜማም እንዲሁ አብሮ ዘና ይላል።
በሀገራችን እግርኳስ ባልተለመደ መልኩ ለአንዳንድ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ደጋፊዎች የአደጋገፍ ስልት በቀረበ መልኩ የመከላከያ ማርሽ ባንድ አባላት ቡድናቸውን እየተከተሉ ማበረታታት ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል።
ታድያ ይህ የድጋፍ ስርዓትም እግርኳሱን ለሚታደሙ አካላት ከሜዳው ባሻገር በተመሳሳይ ወቅት ከደጋፊዎች መካከል በሚሰሙት የተለያዩ ሀገራዊ ስሜት ባላቸው ዜማዎች እንዲሁ ራሱን ዘና የሚያደርግበትን አማራጭ መፍጠር ችለዋል።
👉 ግሩም ግቦች መቆጠራቸውን ቀጥለዋል
ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በዓመቱ መጨረሻ ለውድድር ዘመኑ ምርጥ ግብ መፎካከር የሚችሉ ሁለት ግቦችን ተመልክተን የነበረን ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ሁለት ተጨማሪ ግቦችን ተመልክተናል።
በጨዋታ ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር በወላይታ ድቻ 2-1 በተሸነፈበት ጨዋታ ጅማዎችን ቀዳሚ ያደረገችውን ግብ መስዑድ መሀመድ ከአድናን ረሻድ የተቀበለውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ከርቀት በመምታት ያስቆጠራት ግብ እጅግ አስደናቂ ነበረች።
በተመሳሳይ ሀዲያ ሆሳዕና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ 80ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ዘካርያስ ከማዕዘን የተሻማለትን ኳስ ወደ ቅርቡ ቋሚ በመማምራት በግሩም ሁኔታ በመምታት ያስቆጠረበት መንገድም እንዲሁ ቀልብን የሚስብ ነበር። ከውጤት ባለፈ በሊጉ መሰል ለዓይን ማራኪ የሆኑ ግቦችን ለመመልከት መቻል በየሳምንቱ ሊደጋገም የሚገባው ሁነት ነው።