ቅድመ ዳሰሳ | የ29ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ሦስት ጨዋታዎች ቅድመ ምልከታ

የ29ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሦስት ጨዋታዎችን እንደሚከተለው ቃኝተናቸዋል።

በዘንድሮ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዋንጫ ፉክክሩ እና ላለመውረድ ትንቅንቁ ቀጠሎ እስካለንበህ የ29ኛ ሳምንት ደረስ ደርሷል። እርግጥ ባሳለፍነው ሳምንት ከነገ ተጋጣሚዎች መካከል ሰበታ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ወደ ታችኛው የሀገሪቱ የሊግ እርከን መውረዳቸውን ቢያረጋግጡም አንደኛውን ቦታ ግን በሂሳባዊ ስሌት እስከ ደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ ድረስ የሚገኙ ሰባት ክለቦች ይዞሩታል። ነገ ከሚደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ውስጥ የዋንጫው ፉክክር ላይ ተፅዕኖ የሚያመጣ መርሐ-ግብር የሌለ ቢሆንም በታችኛው ቦታ ላይ የሚኖሩ መበላለጦችን በመንተራስ ዳሰሳውን አሰናድተናል።

ከላይ እንደገለፅነው የነገ የባህር ዳር ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ተጋጣሚዎች ሰበታ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ለከርሞ በሊጉ አለመኖራቸውን ባሳለፍነው ሳምንት አረጋግጠዋል። በእንቅስቃሴ ደረጃ ለክፉ የሚዳርጋቸው ነገር ባያሳዩም ወሳኙን ሦስት ነጥብ ለማሳካት በተደጋጋሚ ማፈራቸው እዚህ ደረጃ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል። ነገም በእነርሱ በኩል ከመርሐ-ግብር ማሟያ ውጪ ምናልባት ለክብር የሚደረግ ጨዋታቸውን ያለምንም ተፅዕኖ አድርገው ከሜዳ ይወጣሉ። በነፃነት የሚጫወት ቡድን ደግሞ ብዙ ጊዜ ከበድ ስለሚል ጠዋት ወልቂጤን የሚፋለው ጅማም ሆነ አመሻሽ ከባህር ዳር ጋር የሚጫወተው ሰበታ አንዳች ነገር ከሜዳ ይዘው ሊወጡ ይችላሉ። ምክንያቱም ከክብር ውጪ የሚያጡት ነገር ስለሌለ ያለምንም ገፊ ሀይል ስለሚንቀሳቀሱ የሚኖራቸው ነፃነት ብርታት ይሰጣቸዋል።

ወልቂጤ እና ባህር ዳር ከተማ ግን የነገውን ጨዋታ እጅግ አጥብቀው ይፈልጉታል። በተለይ ያለፉትን ሰባት ጨዋታዎች ያላሸነፉት ሠራተኞቹ የሌሎች ክለቦችን ውጤት ሳይጠብቁ በሊጉ ለመቆየት አራት ነጥቦችን ይሻሉ። ይህንን ለማሳካት ደግሞ ነገ ትልቁን እርምጃ ወደ ፊት መራመድ ይገባቸዋል። ባሳለፍነው ሳምንት ለሦስተኝነት ከሚፎካከረው ሲዳማ ቡና ጋር ተጫውተው ነጥብ የተጋሩት ወልቂጤዎች በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ የማጥቃት አጨዋወት ተከትለው ጨዋታውን ለመወሰን ጥረት አድርገዋል። ነገርግን ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች በቅጣት ምክንያት ለቡድኑ ግልጋሎት ያልሰጠው ጌታነህ ከበደ ትቶት የሄደውን ቦታ ማንም መድፈን ሳይችል ጎል ፊት ዶልዶም ብለው ነበር። ነገ ግን አይምሬው አጥቂ ወደ ሜዳ ስለሚመለስ ያጡትን ስልነት አግኝተው በሊጉ ሁለተኛ ብዙ ግብ ያስተናገዱትን ጅማዎች እንደሚፈትኑ ይጠበቃል።

ከ22ኛ ሳምንት ጀምሮ በመቀመጫ ከተማው እየተጫወተ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ገጥሞ አንድ ለምንም አሸንፎ እጅግ አስፈላጊውን ሦስት ነጥብ አሳክቷል። ከቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ከሚገኙት 6 ነጥቦች ግማሹን ካሳካ የማንንም ውጤት ሳይጠብቅ አለመውረዱንም ያረጋግጣል። የቀሩት ተጋጣሚዎች ደግሞ በአንገብጋቢ ሁኔታ ድሎችን የሚሹ ስላልሆኑ ፈተናው ቀለል እንደሚልለት ይታሰባል። በድሬዳዋው ጨዋታ በተሻለ ልዕልና ማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወት በመከተል ሦስት ነጥብ ለማግኘት ጥሮ የነበረው ቡድኑ ካልተጠበቀ ምንጭ ግብ ከማግኘቱ በተጨማሪም ሌሎች እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ሲሰነዝር ነበር። የድሬው የግብ ዘብ ፍሬው ጌታሁን ብቃት የተለየ ባይሆን ኖሮ ከሦስት በላይ ጎሎችን አስቆጥሮ አስተማማኝ ድል ያገኝ ነበር። በተለይ በተለይ ደግሞ የተጋጣሚን የላላ የመከላከል አደረጃጀት ለመጠቀም የጣረበት መንገድ አስገራሚ ነበር። የነገው ተጋጣሚ ሰበታም በመከላከል አደረጃጀት የሚታማ ስለሆነ ብዙ ላይቸገር ይችላል።

ቀትር ላይ በሀዲያ ሆሳዕና እና ወላይታ ድቻ መካከል የሚደረገው ፍልሚያ ደረጃን እና ነጥብን ከማሻሻል ያለፈ እምብዛም ጠቀሜታ የለውም ብሎ መናገር ይቻላል። እርግጥ በሂሳባዊ ስሌቶች በደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ ቦታ ላይ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና አሁንም የመውረድ እጣ ሊደርስበት ይችላል ብሎ መናገር ቢደፈርም ቀመሩ ግን የሌሎች 6 ክለቦችን ነጥብ የሚያካትት አልፎም የጎል ልዩነቶችም ስላሉበት ከመሆን ያለመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው። ባሳለፍነው ሳምንት የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ያስጣለው የአሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ስብስብ ነገ ቢያሸንፍ ደረጃውን ባያሻሽልም ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ለመገናኘት ይጠቅመዋል። በተቃራኒው ከአስራ አንድ ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ የናፈቀውን ሦስት ነጥብ ባሳለፍነው ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር ላይ ያገኘው ወላይታ ድቻ በበኩሉ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የመጨረስ ዕድሉን አሟጦ ለመጠቀም ነገም ይጥራል ተብሎ ይጠበቃል። ያለፉትን ጨዋታዎች ድል ብቻ ሳይሆን ግብ ማግኘትም ተስኖት የነበረው ቡድኑ ከ655 ደቂቃዎች በኋላ በተጋጣሚ ሳጥን የነበረው የጎል ግርዶሽ ተቀርፎለታል። ቡድኑ በላይኛው ሳጥን ክፍተቶች ቢኖሩትም በራሱ ሳጥን ግን ጠንካራ ነው።

ወልቂጤ ከተማ አበባው ቡጣቆ ከጉዳት ጌታነህ ከበደ ደግሞ ከቅጣት ሲመለሱለት ተስፋዬ ነጋሽ ግን አሁንም ባለማገገሙ ከጨዋታው ውጪ ነው። ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ ኢዮብ ዓለማየሁን በቅጣት አምበሉ መስዑድ መሐመድን በጉዳት ምክንያት አያገኝም።

የወልቂጤ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር እርስ በእርስ ግንኙነት

– የተሰረዘውን የውድድር ዓመት ሳይጨምር ሁለት ቡድኖች ሦስት ጊዜ በሊጉ የተገናኙ ሲሆን ሁለት ወልቂጤ አሸንፎ አንዱን ደግሞ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። ድሎቹ በተገኙበት ጨዋታዎች ወልቂጤ 5 ጅማ 3 ግቦችን አስቆጥረዋል።

የጨዋታው ዳኞች (04:00) – ዮናስ ካሣሁን፣ አማን ሞላ፣ ማህደር ማረኝ፣ ምስጋና መላኩ

ተጨማሪ ዳኞች – ይበቃል ደሣለኝ እና ዳዊት ገብሬ

ግምታዊ አሰላለፍ


ወልቂጤ ከተማ (4-3-1-2)

ሮበርት ኦዶንካራ

ዮናታን ፍሰሀ – ዳግም ንጉሴ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ

በኃይሉ ተሻገር – ኢሞሞ ንጎዬ – ሀብታሙ ሸዋለም

አብዱልከሪም ወርቁ

ጫላ ተሺታ – ጌታነህ ከበደ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)

አላዛር ማርቆስ

ወንድማገኝ ማርቆስ – ኢያሱ ለገሠ – የአብስራ ተስፋዬ – ተስፋዬ መላኩ

ሙሴ ከበላ – አስጨናቂ ፀጋዬ – ዳዊት እስቲፋኖስ

አድናን ረሻድ – መሐመድኑር ናስር – ሱራፌል ዐወል

ሀዲያ ሆሳዕና ሁሉም ተጫዋቾቹ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆኑለት ባሳለፍነው ሳምንት በጉዳት ተቀይሮ የወጣው ተስፋዬ አለባቸው ለነገው ፍልሚያ እንደሚደርስ ታውቋል። ወላይታ ድቻም በተመሳሳይ በጉዳት እና ቅጣት የሚያጣው ተጫዋች ባይኖርም መጠነኛ ህመም ያጋጠመውን አጥቂው ስንታየሁ መንግስቱን የመጠቀሙ ጉዳይ ነገ እንደሚለይ ተጠቁሟል።

የሀዲያ ሆሳዕና እና ወላይታ ድቻ እርስ በእርስ ግንኙነት

– በሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት ወላይታ ድቻ ሦስት ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ሁለት ጊዜ ድል አድርጓል። በጎል ረገድ ግን እኩል ሰባት ሰባት ጎሎችን አስቆጥረዋል።

የጨዋታው ዳኞች (7:00) – እያሱ ፈንቴ፣ ሲራጅ ኑርበገን፣ ተስፋዬ ንጉሴ፣ ተስፋዬ ግርሙ

ተጨማሪ ዳኞች – ኤሊያስ አበበ እና ደረጄ አመራ

ግምታዊ አሰላለፍ


ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)

መሳይ አያኖ

ግርማ በቀለ – ፍሬዘር ካሳ – ቃለአብ ውብሸት

ብርሃኑ በቀለ – ሳምሶን ጥላሁን – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – እያሱ ታምሩ

ሀብታሙ ታደሠ – ባዬ ገዛኸኝ

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

ቢኒያም ገነቱ

በረከት ወልደዮሐንስ – መልካሙ ቦጋለ – ደጉ ደበበ – አናጋው ባደግ

ሀብታሙ ንጉሴ – ንጋቱ ገብረስላሴ – እንድሪስ ሰዒድ

ምንይሉ ወንድሙ – ስንታየሁ መንግሥቱ – ቃልኪዳን ዘላለም

ሰበታ ከተማ ኃይለሚካኤል አደፍርስ፣ ለዓለም ብርሃኑ እና ገዛኸኝ ባልጉዳን በጉዳት ምክንያት ነገ አያገኝም። ባህር ዳር ከተማ ደግሞ ፈቱዲን ጀማል ከህመም ሲመለስለት በድሬዳዋ ጨዋታ ግብ ያስቆጠረው መናፍ ዐወል ግን ግዳት ስለገጠመው አይሰለፍም።

የሰበታ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ እርስ በእርስ ግንኙነት

– በ2012 ያደረጉት ጨዋታ በኮቪድ ምክንያት በመሰረዙ የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት በሦስት ጨዋታዎች የተገደበ ነው። በመጀመርያው ግንኙነት ባህር ዳር 4-1 ሲያሸንፍ በሁለተኛው ደግሞ ሰበታ ከተማ 2-1 አሸንፏል። ዘንድሮ የተከናወነው ፍልሚያ ደግሞ አንድ ለአንድ ተጠናቋል።

የጨዋታው ዳኞች (10:00) – ባህሩ ተካ፣ ትግል ግዛው፣ ፍቅሬ ወጋየሁ፣ ዓለማየሁ ለገሰ

ተጨማሪ ዳኞች – ፋሲካ የኋላሸት እና መሐመድ ሁሴን

ግምታዊ አሰላለፍ


ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)

ሰለሞን ደምሴ

ጌቱ ኃይለማሪያም – ወልደአማኑኤል ጌቱ – አንተነህ ተስፋዬ – አለማየሁ ሙለታ

በኃይሉ ግርማ – ጋብርኤል አህመድ

ሳሙኤል ሳሊሶ – አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ – ዱሬሳ ሹቢሳ

ፍፁም ገብረማርያም

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ፋሲል ገብረሚካኤል

አህመድ ረሺድ – ፈቱዲን ጀማል – ሰለሞን ወዴሳ – ግርማ ዲሳሳ

ፍፁም ዓለሙ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ፎዐድ ፈረጃ

አደም አባስ – ኦሴይ ማዉሊ – ዓሊ ሱሌይማን