የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የሊጉ መሪ ንግድ ባንክ እና ተከታዩ ኤሌክትሪክ ሲያሸንፉ ሀዋሳ እና መከላከያ ነጥብ ተጋርተዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በአዳማ ሲከወኑ ሊጉን እየመራ የሚገኘው ንግድ ባንክ በግብ ሲንበሸበሽ ተከታዩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ አዳማ ፣ አቃቂ እና ድሬዳዋ ከተማ ሦስት ነጥብ ሸምተው ተጠባቂ የነበረው የሀዋሳ እና መከላከያ ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል፡፡

3፡00 ሰዓት ላይ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች መሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባህር ዳር ከተማን 5-1 ፣ አዳማ ከተማ ደግሞ ጌዲኦ ዲላን 2-0 አሸንፈዋል

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሜዳ ረፋድ ላይ ሊጉን እየመራ የሚገኘው የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ቡድን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ባህርዳር ከተማ ጋር ጨዋታውን አድርጓል፡፡ አጀማመሩ ተመጣጣኝ የነበረ ቢሆንም በሂደት የባህር ዳርን ደካማ የተከላካይ ክፍልን በአግባቡ ለመጠቀም የጣሩት ንግድ ባንኮች በሎዛ አበራ እና አረጋሽ ካልሳ አስደናቂ ጥምረት ታግዘው ሦስት ነጥብ አሳክተዋል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ 29ኛው ደቂቃ ላይ የባህር ዳር ከተማ ተከላካይ በሳጥን ውስጥ በእጅ ኳስ መንካቷን ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ሎዛ አበራ አስቆጥራው ቡድኗን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ሎዛ አበራ ለአረጋሽ ካልሳ ሰጥታት የመስመር ተጫዋቿ ወደ ጎልነት ለውጣው የጎል መጠኑን ወደ ሁለት ከፍ አድርጋለች፡፡ አጋማሹ ሊገባደድ ስድስት ደቂቃ ያህል ደቂቃዎች እየቀረው በመልሶ ማጥቃት ትዕግስት ወርቄ ግብ አስቆጥራ ባህር ዳርን ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት አድርጋ 2-1 ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከዕረፍት መልስ የሰላ የማጥቃት አማራጮችን በመጠቀሙ ረገድ የተዋጣላቸው ንግድ ባንኮች ተደጋጋሚ ሙከራን አድርገው በርካቶቹ በባህር ዳሯ ግብ ጠባቂ ባንቺአየው ደመላሽ ድንቅ አቅም ሲከሽፉ ብንመለከትም ተከላካዮች ይሰሩት በነበረው ዝንጉነት ሦስት ጎሎችን በዚህኛው አጋማሽ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ ሎዛ አበራ በአግባቡ የሰጠቻትን ሁለት ያለቀላቸውን ኳሶች አረጋሽ ካልሳ ወደ ግብነት በመቀየር የባንክን የግብ መጠን ወደ አራት ስታሳድግ ለራሷ ሀትሪክ ሰርታለች፡፡ ተቀይራ የገባችሁ ታሪኳ ዴቢሶ ከሳጥን ውጪ አስደናቂ ጎል አክላ ጨዋታው 5-1 ተፈፅሟል፡፡

አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ አዳማ ከተማ ጌዲኦ ዲላን የገጠመበትን ጨዋታ 2ለ0 በመርታት ድልን አጣጥሟል፡፡ የቀድሞዋ የደደቢት የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች የሆነችው ትዕግስት ዘውዴ ከዕረፍት በፊት እና በኋላ ያስቆጠረቻቸው ጎሎች አዳማን ባለ ድል አድርገዋል፡፡

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ንግድ ባንክን እግር በእግር መከተሉን ያስቀጠለበትን ውጤት ሲያስመዘግብ አቃቂ ቃሊቲ በዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን አግኝቷል

ኢትዮ ኤሌክትሪክ አርባምንጭ ከተማን በመርታት ወሳኝ ነጥብን አሳክቷል፡፡ ጠንካራ የሜዳ ላይ ፉክክርን ማየት በቻልንበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የአርባምንጭ ከተማን የተደራጀ የአጨዋወት መንገድ የኤሌክትሪክን ጠንካራ የማጥቃት ኃይልን ያየንበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እስከ ሀያ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ ቅርፅ የነበረውን የጨዋታ መንገድ በሁለቱም በኩል ብናይም የኋላ ኋላ አደገኛ ይዘት የተላበሰው የኤሌክትሪክ የአጥቂን ክፍል የሚቀመስ አልሆነም፡፡ 21ኛው ደቂቃ ላይ ከሰሞኑ ልዩነት ፈጣሪ ሆና በኤሌክትሪክ በኩል ብቅ ያለችው ትንቢት ሳሙኤል ከዓይናለም አሳምነው ከመስመር የደረሳትን ኳስ በግንባር በመግጨት ከመረብ አዋህዳ ቡድኗን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡

ወደ ጨዋታ ለመመለስ የአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልዱ አርባምንጭ በብርቱ ትግል ወደ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ መድረስ ቢችልም ደካማ የነበረው የአጨራረስ ብቃታቸው በተቃራኒው ተጨማሪ ጎል እንዲያስተናግዱ ዳርጓቸዋል፡፡ 58ኛው ደቂቃ ላይ ትንቢት ሳሙኤል ለቡድኗ እና ለራሷ ሁለተኛ ጎል ስታስቆጥር አርባምንጭን ከሽንፈት ያልታደገች አንድ ግብ አምበሏ ወርቅነሽ ሜልሜላ አግብታ ጨዋታው በአሰልጣኝ መሠረት ማኔው ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2-1 የበላይነት ተጠናቋል፡፡

10፡00 ሰዓት ላይ የተጠበቀው የመከላከያ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ነጥብ በመጋራት ሲጠናቀቅ ድሬዳዋ ከተማ አሸንፏል

አዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ልዩነትን የሚፈጥረው የመከላከያ እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ተከናውኖ በስተመጨረሻም 1-1 አጠናቀዋል፡፡ የሁለቱ ቡድኖች መርሀግብር የመጀመሪያው አጋማሽ መከላከያ በተወሰነ መልኩ በሀዋሳ ላይ ጫናን ፈጥሮ ለመጫወት ጥረት ያደረገበት ሀዋሳዎች በበኩላቸው ጥንቃቄ አዘል ጨዋታን በመጫወት በተሻጋሪ ኳሶች ጥቃት ለመሰንዘር የጣሩበት ነበር፡፡ መከላከያዎች ጫናቸውን ከጅምሩ አድርገው 5ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አግኝተዋል፡፡ በሀዋሳ የግራ የግብ ክልል አቅጣጫ የተገኘውን የቅጣት ምት መሳይ ተመስገን በቀጥታ ወደ ጎል ስትመታው የግብ ጠባቂዋ መስከረም መንግሥቱ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ተጨምሮበት ጎል ሊሆን ችሏል፡፡

ጨዋታው 16ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ከማዕዘን የሚሻማ ኳስን በመከላከያ የግብ ክልል ውስጥ ለመግጨት የሀዋሳዋ ተከላካይ ቅድስት ዘለቀ በምትዘልበት ወቅት በመስከረም ካንኮ ጥፋት ተሰርቶባት ተጫዋቿም በጉንጯ ላይ የስብራት አደጋን አስተናግዳለች፡፡ ተጫዋቿ በወደቀችበት ወቅት ጉዳቱ ጠንካራ በመሆኑ ከሀዋሳ ከተማው የህክምና ባለሙያ ሽመልስ ባለፈ የንግድ ባንክ ፣ የባህርዳር እና የመከላከያ የህክምና ባለሙያዎች ከቀይ መስቀል ጋር በመተባበር ለተጫዋቿ የመጀመሪያ ህክምና ዕርዳታን ካደረጉላት በኋላ በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋም በአምቡላንስ አምርታለች፡፡ ጨዋታው ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ ቀጥሎ ሀዋሳ በነፃነት መና እና ረድኤት አስረሳኸኝ መከላከያ በሴናፍ ዋቁማ እና ረሂማ ዘርጋው አማካኝነት ሙከራን ቢያደርጉም አጋማሹ 1-0 ተገባዷል፡፡

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ቀጥሎ እጅግ አስደናቂ ፉክክርን ያስመለከተን ቢሆንም በዳኞች የተዛቡ ውሳኔዎች በተደጋጋሚ ሲደበዝዝ ተመልክተናል፡፡ ጨዋታው 85ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የሀዋሳዋ አጥቂ ረድኤት አስረሳኸኝ ግብ አስቆጥራ ሀዋሳን 1-1 አድርጋለች፡፡ ተጫዋቿ ግቡን ካስቆጠረች በኋላ በሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ዓይነት በማናውቀው መልኩ የለበሰችውን የላይኛውን መለያ አውልቃ ደስታዋን የገለፀችበት መንገድ ብዙሀኑን ተመልካች አስገርሟል፡፡ በሌላ በኩል አሰልጣኝ መልካሙ ታፈረ ደስታውን ሲገልፅ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በማምራቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከወጣ በኋላ ጨዋታው 1-1 ፍፃሜን አግኝቷል፡፡

በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሜዳ ድሬዳዋ ከተማ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተፈትኖም ቢሆንም ሦስት ነጥብን ማግኘት ችሏል፡፡ ታደለች አብርሃም በጨዋታ ቤተልሔም ታምሩ በፍፁም ቅጣት ምት ድሬዳዋን 2-0 አሸናፊ ያደረጉ ግቦችን አገናኝተው ጨዋታው ተጠናቋል፡፡

ያጋሩ