ሪፖርት | ወልቂጤ የሊጉ ቆይታውን ለማረጋገጥ ተቃርቧል

በ29ኛ የጨዋታ ሳምንት የመክፈቻ በነበረው መርሐ-ግብር አምበሉ ጌታነህ ከበደን መልሰው ያገኙት ወልቂጤ ከተማዎች ጅማ አባ ጅፋርን በመርታት ደረጃቸውን አሻሽለዋል።

ወልቂጤ ከተማዎች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሲዳማ ቡና ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ሁለት ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ቤዛ መድህን እና ዮናታን ፍሰሃን አስወጥተው በምትካቸው ዮናስ በርታ እና ከሦስት ጨዋታዎች ቅጣት የተመለሰውን አምበላቸውን ጌታነህ ከበደ ወደ መጀመሪያ ተመራጭነት የተመለሱ ሲሆን በአንፃሩ መውረዳቸውን ባረጋገጡት ጅማ አባ ጅፋሮች በኩል በወላይታ ድቻ ከተረታው ስብስብ አራት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም የዓብስራ ተስፋዬ ፣ መስዑድ መሀመድ ፣ አድናን ረሻድ እና ቦና ዓሊን አስወጥተው በምትካቸው አካሉ አትሞ ፣ ሙሴ ካበላ ፣ ዱላ ሙላቱ እና ሮባ ወርቁን በመጀመሪያ ተመራጭነት ተጠቅመዋል።

በእንቅስቃሴ ረገድ ተመጣጣኝ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ኳሱን የመቆጣጠር ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም ወልቂጤ ከተማዎች ግን በተሻለ ወደፊት በመድረስ እድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት ነበር።

ጌታነህ ከበደን ከሦስት ጨዋታዎች መልስ ያገኙት ወልቂጤ ከተማዎች ባለፉት ጨዋታዎች ቡድኑ ምን ያክል አጥተውት እንደነበር በዚህ ጨዋታ በሚገባ ተመልከተናል ፤ በጨዋታው የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ቡድኑ ያደረጋቸው ሙከራዎች በሙሉ ከእሱ የተገኙ ነበሩ ፤ በ5ኛ ደቂቃ ላይ ረመዳን የሱፍ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታካ በወጣችበት ኳስ ሙከራ ማድረግ የጀመረው ጌታነህ በ8ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከግቡ ትይዩ ከተገኘ የቅጣት ምት አጋጣሚ በቀጥታ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችበት እንዲሁም በ21ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር አቡበከር ሳኒ ያደረሰውን ኳስ ከሳጥን ጠርዝ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ልኳት በአላዛር ማርቆስ የመከነችበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።


ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ወልቂጤ ከተማዎች በ32ኛው ደቂቃ ወሳኝ ግብ ማስቆጠር ችለዋል ፤ ሀብታሙ ሸዋለም ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም ያሻማውን የቅጣት ምት ኳስ ኳስ በሩቁ ቋሚ የነበረው ወሀቡ አዳምስ በሁለት የጅማ ተጫዋቾች መሀል ሆኖ በመዝለል በግሩም ሁኔታ ገጭቶ ማስቆጠር ችሏል።

በአንድ ደቂቃ ልዮነት ወልቂጤ ከተማዎች መሪነታቸውን ለማሳደግ ቀርበው ነበር ፤ ከቆመ ኳስ መነሻውን ባደረገ ሂደት በግራ የሳጥኑ ክፍል የደረሰው ጌታነህ ከበደ ኳሷን በግራ እግሩ አክርሮ ወደ ግብ ቢልክም አላዛር ማርቆስ እንደምንም አድኖበታል።


በጨዋታው ምንም እንኳን በተወሰኑ አጋጣሚዎች አደጋ የሚፈጥሩ ይመስሉ የነበሩት ጅማዎች በ35ኛው ደቂቃ ላይ መሀመድ ኑር ናስር ከሳጥን ውጭ በግራ እግሩ በቀጥታ ወደ ግብ የላካት እና ሮበርት ኦዶንካራ በቀላሉ ያዳነበት አጋጣሚ በአጋማሹ ያደረጉት ተጠቃሽ ብቸኛ ጠንካራ ሙከራ ነበር።

በመስመሮች ሆነ መሀል ለመሀል በሚደረጉ ጥቃቶች የተሻለ ነገር ለመፍጠር ሲታትሩ በነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች በኩል በ43ኛው ደቂቃ ላይ ከግቡ ትይዩ ዳግም የቅጣት ምት አጋጣሚ ያገኘው ጌታነህ ከበደ በቀጥታ ወደ ግብ የላከው ሀይልን የቀላቀለ ኳስ በግቡ አግዳሚ ሲመለስ በቅርብ ርቀት የነበረው በሀይሉ ተሻገር በቀላሉ ደገፍ አድርጎ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት አሳድጎ አጋማሹን መፈፀም ችለዋል።


በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ወልቂጤ ከተማዎች እንደ መጀመሪያው ሁሉ ወደ ጅማ ሳጥን ቀርበው ባደረጓቸው ተከታታይ ሙከራዎች ቢጀምርም በ51ኛው ደቂቃ ላይ ጅማ አባ ጅፋሮች ወደ ጨዋታ ሊመልሳቸው የሚችለውን እድል በሀይሉ ተሻገር ሱራፌል ዓወል ላይ በሰራው ጥፋት በተገኘ የፍፁም ቅጣት ቢያገኙም ሱራፌል ዓወልን ሙከራ ሮበርት ኦዶንካራ አድኖበታል።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከፍ ያለ ጥረት ማድረጋቸውን የቀጠሉት ጅማ አባ ጅፋሮች በ55ኛው ደቂቃ ሮባ ወርቁ ሳጥን ውስጥ በግሩም ሁኔታ ያደረሰውን ኳስ ዱላ ሙላቱ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ኳሷን በማይታመኑ መልኩ ያመከናት እንዲሁም በ60ኛው ደቂቃ ቤካም አብደላ ከቀኝ መስመር በቀጥታ ወደ ግብ የላካት እና ሮበርት ኦዶንካራ አቋቋሙን በፍጥነት አስተካክሎ ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ አደገኛ ሙከራዎች ነበሩ።

በተፈጠረባቸው ጫና ስጋት የገባው የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ይበልጥ ጨዋታውን በጥንቃቄ ለመጫወት የሚረዱ ለውጦችን በማድረግ መከላከላቸውን ይበልጥ ጠጣር ለማድረግ ጥረት ያደረጉ ሲሆን እነዚህ ለውጦች በተቃራኒው የቡድኑን ማጥቃት ግን በጉልህ እንደቀነሱት አስተውለናል።

በመጠኑም ቢሆን ተቀዛቅዞ በቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በጅማዎች በኩል በ85ኛው ደቂቃ መሀመድኑር ናስር ከርቀት ከቆመ ኳስ በቀጥታ ያደረገው ግሩም ሙከራ በሮበርት ኦዶንካራ ከዳነበት ኳስ ውጥ የጠሩ እድሎችን ለመመልከት ሳንችል ቀርተናል።


በ86ኛው ደቂቃ ላይ ግን ወልቂጤዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሂደት ሦስተኛ ግባቸውን አግኝተዋል ፤ አክሊሉ ዋለልኝ ከግራ የሳጥን ጠርዝ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ጫላ ተሺታ በቀላሉ አስቆጥሮ የቡድኑን አሸናፊነት አረጋግጧል።

ውጤቱን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 35 በማሳደግ ለጊዜውም ቢሆንም ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ብለው የተቀመጡ ሲሆን በአንፃሩ መውረዳቸውን ያረጋገጡት ጅማ አባ ጅፋሮች በ23 ነጥብ አሁንም በ15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።