የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 3-0 ጅማ አባ ጅፋር

ከረፋዱ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው

“መውረዱን ያረጋገጠ ቡድን እንደመሆኑ በነፃነት እንደሚመጡ ጠብቀን ነበር ፤ በነፃነት የሚጫወት ቡድንን መግጠም ደግሞ በጣም አስቸጋሪ ነው። በመሆኑም ከዚህ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ይዞ መጨረስ በጣም ጥሩ ነው።”

ሱራፌል ዓወል ስላመከናት የፍ/ቅ/ም አጋጣሚ

“ከዚህ ቀደም በነበሩ ጨዋታዎች በጨዋታ አስተዳደር በኩል ችግሮች ነበሩብን። ከዚህ አንፃር ተቆጣራ ቢሆን ኖሮ ጥሩ መነሻ ይሆናቸው ነበር። ነገር ግን ኳሱ መሳቱ ጨዋታውን አሸንፈን እንድንወጣ ረድቶናል።”

ሲቀጠር የተሰጠውን ኃላፊነት ስለመወጣቱ

“የተሰጠኝን ቡድኑን በሊጉ የማቆየት ኃላፊነት አሳክቻለሁ። ሌላው ወልቂጤ የራሱ የሆነ የጨዋታ ሞዴል እንዲኖረው ለማድረግ ጥረት አድርጊያለሁ። ምናልባት በቀጣይ ደግሞ ጥሩ የሚጫወት እና ውጤታማ የሆነ ቡድን ለመስራት እጥራለሁ።”

ስለመጨረሻው የሊግ ጨዋታቸው

“የሰው ልጅ ፍላጎት የተገደበ አይደለም። አሁን ላይ በሊጉ የመቆየታችን ነገር እርግጥ ሆኗል። ስለዚህ በሊጉ የተሻለ ደረጃ ይዘን ለማጠናቀቅ እንጥራለን።”

የሱፍ ዓሊ – ጅማ አባ ጅፋር

ስለጨዋታው

“ውጤቱን እነሱ ይበልጥ ይፈልጉት ነበር። በአንፃሩ የእኛ ልጆች ደግሞ ነፃ ሆነው ነበር የተጫወቱት። ነገር ግን አብዛኞቹ ተጫዋቾች በፈለኳቸው ደረጃ አላገኘኋቸውም በጣም ወርደው ነበር። በተለይ መሀል ሜዳ ላይ የነበሩ ተጫዋቾች ጥሩ አለመሆን ይህን ደረጃ ይዘን እንድንጨርስ አድርጎናል።”

ቡድኑን ለመውረድ ስለዳረገው ምክንያት

“የተጫዋቾች ጥራት ችግር ነበረብን። በተመሳሳይ አጨዋወት እንጠቅምባቸው የነበሩ ተጫዋቾች ተመሳሳይ ናቸው። ይህም ድካም እና ጫና ይፈጥራል። በዚህም ጉዳቶች ይፈጠራሉ። በዚህ ሂደት ተክትን የምናስገባቸው ልጆች ክፍተት ይፈጠራል ይህም ችግር ፈጥሯል። እንደ የያዝነው ስብስብ ከሆነ ገና ከመጀመሪያው ጨዋታ ጀምሮ ስትመለከት የምንሸነፍባቸው ጨዋታዎች አንዳንዴ እንደ አሰልጣኝ ቡድን የእኛም ስህተቶች ነበሩ። ሌላው የተጫዋቾቹን ጥራት ለማሳደግ አለመስራታችን ችግር ፈጥሯል
፤ ለዚህም ኃላፊነት እንወስዳለን።”