ሪፖርት | ወላይታ ድቻ እና ሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ተጋርተዋል

ጥሩ ፉክክር ያስተናገደው የምሳ ሰዓቱ የወላይታ ድቻ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ባደረጋቸው ስድስት ለውጦች ሶሆሆ ሜንሳህ ፣ ኤልያስ አታሮ ፣ ፀጋዬ ብርሀኑ ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ ፣ ራምኬል ሎክ እና ዑመድ ዑኩሪ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ መጥተዋል። በወላይታ ድቻ በኩል በተደረገ ብቸኛ ለውጥ ከጅማ አባ ጅፋሩ ድል መልስ ጉዳት የገጠመው ስንታየሁ መንግሥቱ በቢኒያም ፍቅሬ ተተክቷል።

ጨዋታው በሀዲያ ሆሳዕናዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የጀመረ ነበር። በወላይታ ድቻ የሜዳ ክልል ላይ ባመዘነው እንቅስቃሴ ሆሳዕናዎች ወደ ሳጥን ለማድረስ የሚያደርጉት ጥረት በወላይታ ድቻ በመጠኑ ወደ ቀኝ ባመዘነ ቀጥተኛ ጥቃት ምላሽ እየተሰጠው ታይቷል። የመጀመሪያው ሙከራም 7ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳዊት ከመሀል ሜዳ ያሻገረውን የቅጣት ምት ኳስ ቢኒያም ፍቅሬ በግንባሩ ጨርፎ ለጥቂት ሲወጣበት የታየ ነበር።

ብርሀኑ በቀለ 11ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውስጥ አክርሮ መትቶ ወደ ውጪ በወጣበት ኳስ ሙከራ ማድረግ የጀመሩት ሆሳዕናዎች የድቻን ቀጥተኛ ኳሶች በማርገብ በቅብብል መውጣት በቀጠሉበት አጋጣሚ ግብ አግኝተዋል። አበባየሁ ዮሐንስ በፈጣን ሽግግር የሰነጠቀውን ኳስ ዑመድ ዑኩሪ ባልተለመደ ሁኔታ ከወላይታ ድቻ የተከላካይ መስመር ጀርባ የተገኘውን ሰፊ ክፍተት ተጠቅሞ ሳጥን ድረስ በመግባት 16ኛው ደቂቃ ላይ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል።

ዑመድ ከአንድ ደቂቃ በኋላም በተመሳሳይ ሁኔታ ከተከላካይ ጀርባ አምልጦ ከጠባብ አንግል ያደረገው ሙከራም ለግብ ይቀረበ ነበር።

ከኋላ ክፍተት ቢፈጥሩም ከሜዳቸው መውጣት የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች የጨዋታውን እንቅስቃሴ ሚዛናዊ እንዲሆን አድርገውታል። በዚህም በጥሩ የማጥቃት ምልልስ የቀጠለው ጨዋታ ቆየት ብሎም ቢሆን ተከታታይ ሙከራዎችን አስተናግዷል። 32ኛው ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ ሶሆሆ ሜንሳህ ሳይቸገር ሲያድንበት እና እንቅስቃሴው ሲቀጥል በሌላኛው ጫፍ ራምኬል ሎክ ከኤልያስ አታሮ ከግራ ያቀበለውን ኳስ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ዞሮ ያደረገው የተሻለ ጠንካራ ሙከራ በቢኒያም ገነቱ ተመልሷል።

በጥሩ ሁኔታ የተጋጋለው ጨዋታ እምብዛም ሳይቆይ ድንቅ ግብ አስተናግዷል። በዚህም 36ኛው ደቂቃ ላይ አናጋው ባደግ በረጅሙ የተላከ እና ቃልኪዳን ዘላለም ያበረደውን ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ድቻን አቻ አድርጓል። 

ቀሪው የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች በንፅፅር ፉልሚያው ጋብ ያለባቸው ሆነው ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጋምሷል።

እንድሪስ ሰዒድን ቀይረው ሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች በተሻለ የማጥቃት ጫና ወደ ሜዳ ተመልሰዋል። የቡድኑ ጥቃት ሙከራ ያስገኘው ግን 55ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ቃልኪዳን ዘላለም ከግርማ በቀለ ቅብብል ያቋረጠውን ኳስ ከርቀት ሞክሮ ሜንሳህ ሳይቸገር ይዞበታል። በመቀጠል የቡድኑ ቅብብሎች 58ኛው ደቂቃ ላይ እንድሪስ ሰዒድ ከግራ ወደ ቀኝ ያሻገረውን ኳስ ቢኒያም ሳይደርስበት ቀረ እንጂ ወደ ግብነት ሊቀየሩ ደርሰው ነበር።

እንደመጀመሪያው አጋማሽ ከሜዳቸው መውጣት ያልሆነላቸው ሀዲያ ሆሳዕናዎች 60ኛው ደቂቃ ላይ በዑመድ ዑኩሪ ቅጣት ምት ሙከራ ካደረጉ በኋላ ወዲያው ግብ አስቆጥረዋል። ቢኒያም ገነቱ ኳስ በረጅሙ ሊያስጀምር ሲል መንሸራተቱን ተክትሎ ያጠረውን ኳስ ድቻዎች በድጋሚ ለማራቅ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ፀጋዬ አበራ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ዑመድ 61ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል።

ከግቡ በፊት ወጣቶቹ መሳይ ኒኮል ፣ ዮናታን ኤልያስ እና ዘላለም አባቴን ቀይረው ያስገኑት ወላይታ ድቻዎች አጋማሹን በጀመሩበት መልክ ባይሆንም ምላሽ ለመስጠት ባደረጉት ጥረት 71ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም አባቴ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ በግራ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ከፍ አድርጎ የሞከረው ኳስ ወደ ላይ ወጥቶበታል። ወጣቱ አጥቂ 76ኛው ደቂቃ ላይም ቢኒያም ፍቅሬ ወደ ውስጥ ያጠፈለትን ኳስ ከቅርብ ርቀት ሲያመክን ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ ከግራ ራሱ ያሻማውን በተራው ቢኒያም በግንባሩ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች መሪ ከሆኑ በኋላ ያሳዩት መቀዛቀዝ በአንድ አጋጣሚ አበባየሁ የሐንስ ቡድኑ በቅብብል ሳጥን ውስጥ ከገባበት ቅፅበት ውጪ ካደረገው ሙከራ ውጪ ራሱን ለጥቃት እንዲጋብዝ ምክንያት ሆኗል። በድቻ ተደጋጋሚ የግራ መስመር ጫናም ሁለተኛ ግብ ማስተናገዱ አልቀረም። በዚህም 80ኛ ደቂቃ ላይ ዘላለም በድጋሚ ከግራ ያሻገረውን ኳስ ፍሬዘር ካሳ ለማውጣት ሲሞክር በራሱ መረብ ላይ አሳርፎታል። 

ነብሮቹ ወዲያውኑ ወደ ማጥቃት መንፈሳቸው ተመልሰው በፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄ የተደመደሙ ጥቃቶችን ማድረግ ችለው ነበር።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችም የወላይታ ድቻ ወጣቶች የበላይነት የተስተዋለበት ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕናዎች 88ኛው ደቂቃ ላይ በባዬ ገዛኸኝ ያደረጉት የቅጣት ምት መከራ ብቻ የተሻለ የግብ ዕድል ሆኖ ታይቷል። ማራኪ ፉክክር ያስታናገደው ጨዋታም ተጨማሪ ጎሎችን ሳያስመለክተን 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ ወደ 42 ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ወደ 36 ነጥብ ከፍ ብለዋል።

ያጋሩ