የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 2-2 ወላይታ ድቻ

ከጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር በኋላ ሁለት አቻ ከተጠናቀቀው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዲያ ሆሳዕና

ስለጨዋታው

“ቆንጆ እና ተመጣጣኝ ጨዋታ ነበር። ቀዝቀዝ ያለ አጀማመር ቢኖረንም በሂደት የተሻልን ሆነናል። በሁለተኛው አጋማሽ በሁለታችንም በኩል ጥሩ ፉክክር ነበር እንደአጠቃላይ ጥሩ ጨዋታ ነበር።

ወደ መጀመሪያ ተመራጭነት ስላመጣቸው ተጫዋቾች ሚና

“የዓመቱ መጨረሻ ላይ እንደመገኘታችን እና ጨዋታዎች በየሁለት ቀኑ እንደመደረጋቸው ተጫዋቾች ላይ ጉዳት እንዳይከሰት ማፈራረቅ የግድ ይለናል። ዛሬ ያስገባናቸው ተጫዋቾች ከዚህ በፊትም ቢሆን ቀይረን እያስገባን እንጠምባቸው የነበሩ ስለነበር የሰጠናቸውን ኃላፊነት በሚገባ ተወጥተዋል በዚህም ደስተኛ ነኝ።

ስለቀጣይ የሲዳማ ጨዋታ

“ሜዳ ውስጥ ሁሌም ስንገባ ለማሸነፍ ነው። በቀጣይ በሚኖረንም ጨዋታ ከልጆቼ ጋር ተነጋግረን በቀሪ ቀናት ጠንካራ ስራ ሰርተን ጠንካራ ፉክክር ይኖረናል ብዬ አስባለሁ። ዓመቱን ስንጀምር እንደነበረን ዕቅድ አሸንፈን ለመጨረስ እንጫወታለን።”

ስለደጉ ደበበ አሁን ድረስ መጫወት

“እኔ መግለፅ ይከብደኛል ፤ ማንም ሰው የማያደርገውን ነው የሚያደርገው። እሱ ካለ ሁሌም የትኛውም ቡድን ይቸገራል። ከመጫወቱ ባለፈ ቆሞ ቡድኑን ሲመራ በጣም የሚገርም ነው። ድቻዎች እንዳያችሁት ወጣት ልጆች ናቸው የእሱ ከኋላ መቆም ትልቅ እገዛ ያደርግላቸዋል። በአጠቃላይ ለቡድኑ ብቻ ሳይሆን በሊጉ ላሉ ወጣት ተጫዋቾች በመሉ ትምህርት የሚሆን ነው። ከዚያ በላይ ደግሞ ጓደኛዬ ስለሆነ ደስ ይለኛል።”

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ

ስለጨዋታው

“90 ደቂቃው እንደተመለከታችሁት ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች የተገነባ ቡድን እንደመግጠማችን ከሰሞኑ ለማድረግ እንደሞከረነው የተወሰኑ 20 ደቂቃዎች ብልጫ ቢወሰድብንም ቀሪውን 70 ደቂቃ ተቆጣጥረን ለመጫወት ሞክረናል። ከዓላማ አንፃር የፈለግነው ነገር ማሳካት ችለናል ፤ በጨዋታው አጥቅተን ተጫውተናል። ከዚህ ባለፈ ግን በጨዋታው ትልቁ ስኬት ብዬ የምወስደው ለወጣት ተጫዋቾች የመጫወት ዕድል መስጠታችን ለአጠቃላይ ለቡድኑ ሞራልም ሆነ ለተጫዋቾቹ ትልቅ ስኬት ነው ብዬ አስባለሁ።

ስለዘላለም እና ዮናታን እንቅስቃሴ

“በጣም ምርጥ ተጫዋቾች ናቸው። እኛ መጀመሪያም ያሰብነው ግብ ጠባቂው ቢኒያም ፣ አማካዩ አበባየሁ እና አጥቂው ቢኒያምን እንዳያችሁት ነው። እነዚህ ተጫዋቾች ከእኛ ጋር አብረው ሲዘጋጁ ነበር የቆዩት። ግን ከልምድ አንፃር ሙሉ ኃላፊነት ሰጥተን ለማጫወት አልፈለግንም ነበር። አሁን ግን ከሞላ ጎደል የተሻለ ቦታ ላይ ስለምንገኝ በቀሪ ጨዋታም ወጣት ተጫዋቾችን ከመጠቀም የሚከለክለን ነገር የለም። ሌሎች ያልጠቀምንባቸው ልጆችን ጨምሮ በቀጣይ ከክለብ ባለፈ ለሀገርም መጥቀም የሚችሉ ጥሩ ልጆች ናቸው።

ስለ ደጉ ደበበ

“ዛሬ ስለወጣት ተጫዋቾች አያወራን ነበር የምንገኘው። ደጉ በእኔ ዕምነት ከእነሱ አንዱ ነው። በዚህ ደረጃ ታክሎችን እየወረደ የሚጫወት ተጫዋች ምናልባት ወጣት ካልሆነ በስተቀር ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው። ምናልባት አሁን ላይ እሱን ለብሔራዊ ቡድን መምረጥ ከባድ ቢመስልም አሁን ላይ ያለው ብቃት ግን በሊጉ ከሚገኝ የትኛውም ተጫዋች የሚያንስ አይደለም። የትኛውም ተጫዋች በየትኛውም ዕድሜ እርከን ቢገኝም ከደጉ መማር ይኖርባቸዋል። እኔ በግሌ ረጅም ዓመት በተቃራኒ ነበር የምገጥመው አሁን ላይ ግን እሱን የማሰልጠን ዕድል በማግኘቴ በጣም ዕድለኛ ነኝ።”

ያጋሩ