ሪፖርት | በሁለቱ አጋማሾች የተቆጠሩት ድንቅ ጎሎች ባህር ዳር እና ሰበታን ነጥብ አጋርተዋል

በዕለቱ ሦስተኛ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ እና ሰበታ ከተማ በውብ ግቦቻቸው አንድ እኩል ወጥተዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን አንድ ለምንም ያሸነፉት ባህር ዳር ከተማዎች በጨዋታው ግብ አስቆጥሮላቸው የነበረውን መናፍ ዐወል በጉዳት ምክንያት በፈቱዲን ጀማል ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በአዲስ አበባ ከተማ የ4ለ3 ሽንፈት ያስተናገዱት ሰበታ ከተማዎች በኩላቸው ኃይለሚካኤል አደፍርስ፣ አንተነህ ተስፋዬ፣ ቢስማርክ አፒያ እና ቢያድግልኝ ኤሊያስን በታፈሰ ሰርካ፣ በረከት ሳሙኤል፣ ሳሙኤል ሳሊሶ እና በኃይሉ ግርማ ተክተው ጨዋታውን ቀርበዋል።

ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ የጀመሩት ባህር ዳሮች ገና ሁለት ደቂቃ ሳይሆን ቀዳሚ ሊሆኑ ነበር። በዚህም የሰበታን የኳስ ቅብብል ያቋረጠው አጥቂው ኦሴ ማውሊ ከሳጥን ውጪ በግራ እግሩ ጠበቅ ያለ ኳስ ልኮ ግብ ጠባቂው ሰለሞን ደምሴ አምክኖበታል። ገና በጊዜ አስደንጋጭ ጥቃት የተሰነዘረባቸው ሰበታዎች ከደቂቃዎች በኋላ በኃይሉ ግርማ አማካኝነት አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ሞክረው ተመልሰዋል።

የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው ያደረጉት ባለሜዳዎቹ በ5ኛው ደቂቃ ሌላ ጥቃት ሰንዝረዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ፍፁም ዓለሙ ከመዓዘን ምት መነሻን ያደረገ ኳስ በጠባቡ ቋሚ ወደ ግብ ቢልክም ለጥቂት ዒላማውን ስቶ ወጥቶበታል። ይሁ የአጥቂ አማካይ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ከሳጥኑ ጫፍ በግራ እግሩ ሞክሮ ሰለሞንን ፈትኗል። በጨዋታው ብልጫ የተወሰደባቸው ሰበታዎች በ16ኛው ደቂቃ የባህር ዳርን የግብ ክልል ለሁለተኛ ጊዜ ጎብኝተው ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም ከተከላካዮች ዕይታ ውጪ ሆኖ ራሱን ነፃ አድርጎ የነበረው ሳሙኤል ሳሊሶ ከዱሬሳ ሹቢሳ የደረሰውን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ሰለሞን ወዴሳን በሰውነቱ አታሎ በግራ እግሩ ከመረብ ጋር አዋህዶታል።

በመጀመሪያዎቹ አስር እና አስራ አምስት ደቂቃዎች ከፍተኛ ብልጫ የነበራቸው የጣና ሞገዶቹ ጥሩ በነበሩበት ጊዜ ግብ ሳያስቆጥሩ ዋጋ ቢከፍሉም ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። በ28ኛው ደቂቃም ማውሊ ከርቀት ሞክሮ ወጥቶበታል። ከደቂቃ በኋላ ለመጀመሪያው ግብ መገኘት ምክንያት የሆነው ዱሬሳ ከጌቱ የተሻማለትን ኳስ ሁለተኛ ጎል ለማድረግ በግንባሩ ቢሞክረውም የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። በ37ኛው ደቂቃ ደግሞ ሳሙኤል ከተሰለፈበት የቀኝ መስመር በእንቅስቃሴ ወደ ግራ በመሄድ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል ሊያስቆጥር ተቃርቦ ነበር። አጋማሹም ሌላ ሙከራ ሳይስተናገድበት በሰበታ ከተማ መሪነት ተጠናቋል።

የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ለውጠው ያስገቡት አሠልጣኝ አብርሃም በቶሎ አቻ ለመሆን መንቀሳቀስ ይዘዋል። ይህንን ቢያስቡም ግን በኃይሉ በ49ኛው ደቂቃ የዘገየ ሩጫን ወደ ሳጥኑ አድርጎ በሞከረው ኳስ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። በ53ኛው ደቂቃ ግን እጅግ ማራኪ ጎል አስቆጥረው ውጥናቸው ሰምሯል። በዚህም አደም አባስ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ኦሴ ማውሊ አክሮባቲክ በሆነ መልኩ እግጅ ግሩም ጎል አስቆጥሯል።


ጨዋታው 65ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የሰበታው የመሐል ተከላካይ በረከት ሳሙኤል አህመድ ረሺድ ላይ ጥፋት ሰርተካል ብለው የዕለቱ አልቢትር ባህሩ ተካ በቀይ ካርድ አሰናብተውታል። ይህንን ተከትሎ የቁጥር ብልጫ ያገኙት ባህር ዳሮች በሙሉ ሀይማቸው በማጥቃት ወደ መሪነት ለመሸጋገር ሞክረዋል። በተለይ በደቂቃዎች ልዩነት አለልኝ አዘነ ከቆመ ኳስ እና በእንቅስቃሴ የሞከራቸው ኳሶች ጥሩ ነበሩ። በተጨማሪም በ76ኛው ደቂቃ አህመድ ረሺድ ፈጣን የመስመር ላይ ሩጫ በማድረግ ስል ኳሶ ልኮ መክኖበታል።

ተጫዋች ከጎደለባቸው በኋላ ሙሉ ለሙሉ መከላከሉ ላይ ተጠምደው ያመሹት ሰበታዎች አንዷን ነጥብ ይዞ ለመውጣት ሲጣጣሩ ነበር። ነገርግን በ81ኛው ደቂቃ ፍቅረሚካኤል እንዲሁም በ84ኛው ደቂቃ አለልኝ በሰነዘሯቸው ኳሶች እጅ ሊሰጡ ነበር። ከሁለቱ ሙከራዎች ውጪም በ87ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው አስቻው የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ማውሊ በቀጥታ ወደ ግብ ልኮት ለጥቂት ወጥቶበታል። ጨዋታውም ያለ ተጨማሪ ጎል አንድ አቻ ተፈፅሟል።

በውጤቱ መሠረት ባህር ዳር ከተማ በ34 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ባሳለፍነው ሳምንት መውረዱን ያረጋገጠው ሰበታ ከተማ ደግሞ በ22 ነጥቦች የነበረበት ግርጌው ላይ ፀንቶ ተቀምጧል።