የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህርዳር ከተማ 1-1 ሰበታ ከተማ

የዕለቱ ሦስተኛ ጨዋታ በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱም ክለብ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ – ባህርዳር ከተማ

ስለ ሁለቱ አርባ አምስት ደቂቃዎች እንቅስቃሴ…?

“ሁለቱንም አርባ አምስት ደቂቃዎች ብዙ ብልጫ ነበረን ማለት እችላለሁ። ነገር ግን አንድ ሦስተኛው የተጋጣሚ የመከላከል ክፍል ውስጥ ስንደርስ ከጉጉት የተነሳ ብዙ ኳሶችን ስተናል። አለመረጋጋታችን ለውጤት መጓጓታችን ትንሽ ዋጋ አስከፍሎናል እንጂ የመጀመሪያው አርባ አምስትም ሆነ ሁለተኛው አርባ አምስት ሙሉ ሜዳውን ተቆጣጥረን ተጫውተናል ብዬ አስባለሁ፡፡

ከተደረጉ ሙከራዎች አንፃር የሰበታን መከላከል ሰብሮ ስላለመግባታቸው…?

“ትክክል ነው፡፡ ብዙ የጎል ሙከራዎችን አድርገናል፡፡ ነገር ግን ያንን ወደ ጎል ለመቀየር ፊት ላይ ስንደርስ አለመረጋጋታችን እና ለጎል መጓጓታችን አጨራረስ ላይ ዋጋ እንድንከፍል አድርጎናል፡፡ በተረፈ እንደዚህ አይነት ጨዋታዎች በጣም አስጨናቂ እንደሆኑ ቀድመንም እናውቅ ነበር፡፡ የሰበታ ተጫዋቾች አልወረዱም ፤ ቡድኑ ነው የወረደው። የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ እርግጠኛ ነበርን፡፡ ዞሮ ዞሮ ነጥቡንም ይዘን ወጥተናል፡፡ የመጨረሻውን የቡናን ጨዋታ በአሸናፊነትነት ለመዝጋት ጠንካራ ስራ ሰርተን እንመጣለን፡፡

ሜዳ ላይ ስለነበረው የሰለሞን ወዴሳ እና ፉዐድ ፈረጃ ያለ መግባባት…?

“ለክለቡ ሲባል ነው እንጂ በውስጣቸው ምንም የለም። ለክለቡ ነው፡፡ ሰለሞን ኳሱን ቶሎ ልቀቅ ነው የሚለው ፉአድ ደግሞ ውጤቱን ለመቀየር ካለው ፍላጎት የተነሳ ነው ሌላ ነገር አይደለም፡፡

ስለ መጨረሻው ዘጠና ደቂቃ…?

“እስከ መጨረሻው ድረስ እኛ ውጤት አምጥተን ለመጨረስ ብርቱ ትግል እናደርጋለን፡፡ እኔ ዛሬ በነበረው ፐርፎርማንስ ተጫዋቾቼ የሚችሉትን አድርገዋል፡፡ ፊት ላይ ከመጓጓት እና ይህን ሁሉ ደጋፊ ለማስደሰት ከነበራቸው ጉጉት ከተሳቱት በስተቀር ይሄን አርመን እንመጣለን፡፡

አሰልጣኝ ብርሀን ደበሌ – ሰበታ ከተማ

የሚፈለገውን ውጤት አግኝታችዋል …?

“በፍፁም አላገኘውም፡፡ ብናሸንፍ የበለጠ አስራ ስምንት የሚባለውን ነገር ልናሟላ እንችላለን። ሀሳቡ እርግጠኛ ባይሆንም።

በ2015 አስራ ስምንት ክለቦች ይሳተፋሉ የሚል ነገር አለ ማለት ነው..?

“በጭምጭምታ የሚሰማው ነው እንጂ የእኛ ነገር ያለቀለት ነው። ወርዷል ቡድናችን፡፡ ግን ጥሩ ጨዋታ ተጫውቶ መርሃግብሩን ማሟላት ፕሪምየር ሊጉን ጥሩ ድባብ መስጠት በራሱ ለእግር ኳሱ የሚያስፈልግ በመሆኑ ያለንን ለማድረግ ሞክረናል ፤ ተሳክቷልም ጥሩ ነው፡፡

“መረጃው የለንም። ጭምጭምታ ነው፡፡ በሁሉም ዘንድ የሚነገር ነገር ስለሆነ በዕርግጠኝነት በይፋ የወጣ ስላልሆነ እንደገናም ደረጃን አስራ አምስተኛ ለማድረግም ከዛ ከዛ አኳያ እንደገና ደግሞ ጥሩ ጨዋታ ተጫውተን ሊጉን መሰናበት በራሱ አንዱ እግር ኳስ የሚፈለገው ነው፡፡

አንድ ወር ልምምድ ያልሰራ ቡድን ሜዳ ላይ ጥሩ ሆኖ ስለመታየቱ…?

“ሚስጥሩ በአዕምሮ ላይ በመነጋገር ፣ በመግባባት ነው፡፡ ትነጋገርና ከእዛ በተግባር ትንንሽ በመሰሉ መሀል በገባ አይነት ነገሮችን ፣ በማሟሟቆች በስራው ላይ ተጨማሪ በንግግር ስለ ተጋጣሚ ታክቲክ የገንዘብ እና ሌላ ጉዳይን ረስቶ በመግባት የለበስከውን መለያ በማስታወስ ስራ መስራት ትንሽ ሊያሳዩም ችለዋል፡፡

ትንሽ ዕገዛ ቢደረግ ክለቡ ለውጥ ላይ ይገኝ ነበር …?

“በዕርግጠኝነት ዕገዛ ቢደረግልኝ ዋናዎቹ ተርታ ውስጥ የመግባት አቅም አለን፡፡ ስራው በእኛ ነው ፤ ነገር ግን ድጋፍ ከሌለህ ደግሞ ምንም ነገር ልታደርግ አትችልም፡፡ በተለይ ተጫዋች። በተጨማሪ ደግሞ ያንን ሊሰራ የሚችል ስታፍ ያስፈልጋል። በባዶ ብቻህን አይሆንም። አንድ እንጨት አይነድም። የዚህ ችግር ሰለባ የሆነው ድጋፍ ከማጣት የተነሳ ነው፡፡