ቅድመ ዳሰሳ | የ29ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

የነገውን ተጠባቂ የጨዋታ ቀን የተመለከተው ዳሰሳችን እንዲህ ይነበባል።

ወደ ፍፃሜው እየቀረበ በሚገኘው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ እጅግ አጓጊ የሆነ የጨዋታ ቀን ይጠበቃል። ፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ ቀን በተከታታይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ በመሆኑ ዕለቱ የሊጉን ቻምፒዮን የማመላከት አቅም ሊኖረው የሚችል ስለሆነ ተጠባቂነቱ ከፍ ብሏል። ከዚህ በተጨማሪ በመጀመሪያው ጨዋታ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ በሊጉ የመቆየቱን ነገር ለማረጋገጥ ሲዳማ ቡና ደግሞ የሦስተኝነት ደረጃውን ለማስጠበቅ ይፋለማሉ።

ላለፉት 11 ጨዋታዎች ሽንፈት ያላስተናገደው አዲስ አበባ ከተማ የአቻ ውጤት ማብዛቱ አጣብቂኝ ውስጥ ቢያቆየውም በሰበታ ከተማ ላይ ያሳካው ድል ትልቅ እርምጃ አራምዶታል። በሌላ በኩል ወልቂጤ ከተማ ዛሬ ማሸነፉን ተከትሎ አዲስ አበባ ከስሩ የቀሩት እርስ በርስ የሚጫወቱት አዳማ እና ድሬዳዋ ብቻ ሆነዋል። በመሆኑም ሪችሞንድ ኦዶንጎን ብቻ በቅጣት የሚያጣው ቡድኑ ነገ ሙሉ ነጥብ ማሳካት ለቆይታው ወሳኝ መሆኑን በማገንዘብ ወደ ሜዳ ይገባል። ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ የሆነው ሲዳማ ቡና በበኩሉ ወጥ አቋም እያሳየ ባይገኝም አሁን ላይ ያለበትን የሦስተኝነት ደረጃ ለማስጠበቅ ይጫወታል።

በተጠባቂዎቹ ቀጣይ ጨዋታዎች ፋሲል ከነማ ኢትዮጵያ ቡናን ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ አርባምንጭ ከተማን ይገጥማሉ። ቡና እና አርባምንጭ የሲዳማ ውጤት ላይ ተመስርተው እስከ ሦስተኛ ደረጃ ለመጨረስ ብቻ የሚጫወቱ ከመሆኑ አንፃር የዋንጫ ተፎካካሪዎቹ ጉዳይ ትልቁን ርዕሰ ጉዳይ ይሆናል። በዚህ ሳምንት በሁለቱ ቡድኖች መካከል የሚኖረው ፍጥጫ ልዩነቱ ዝቅ ማለቱን እና የመርሐግብሩ ከወትሮው የተለየ መሆኑን ተከትሎ ሌላ መልክ ሊይዝ እንደሚችል ይታሰባል።

በዚህም ልዩነታቸው 10 ነጥብ ከነበረበት የ22ኛው ሳምንት ጀምሮ ብንመለከት እንኳን እርስ በእርስ ካደረጉት የ25ኛ ሳምንት ጨዋታ ውጪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅድሚያ ፋሲል ከነማ ደግሞ በመቀጠል ጨዋታቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ነገ ደግሞ በተቃራኒው ፋሲል ከነማ ቀድሞ ሲጫወት ቅዱስ ጊዮርጊስ የዕለቱን የመጨረሻ ጨዋታ ያደርጋል። በዚህ ደረጃ ባሉ ፉክክሮች ላይ ሥነ ልቦናዊ ጉዳዮች ካላቸው ዋጋ አንፃር ስንመለከተው ፋሲል ከነማ የተቀናቃኙን ውጤት ሳይሰማ የሚያደርገው ጨዋታ ቀድሞ በሊጉ ሰንጠረዥ ላይ እንዲቀመጥ እንደሚያደርገው እያወቀ ወደ ሜዳ የሚገባበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ፉክክሩ ከጦፈ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀናቃኙን ውጤት ሰምቶ የሚያደርገው ጨዋታ መሆኑ ለየት ያደርገዋል። በዚህም ቡድኖቹ ይህ የጨዋታ ቅደም ተከተል ለውጥ ለሳምንታት ከለመዱት አኳኋን ተለይቶ ሲገጥማቸው እንዴት ያስተናግዱታል የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ይሆናል።

ከአዕምሯዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሌላ ሀሳብ የነገዎቹን ፍልሚያዎች ስናስባቸው ቡድኖቹ ከተጋጣሚዎቻቸው በላይ አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ቀላል አለመሆኑን ለመረዳት የመጨረሻ ጨዋታዎቻቸውን መመልከት በቂ ነው። ባሳለፍነው ሳምንት ሁለቱም በተመሳሳይ ሁኔታ በከፍተኛ የጨዋታ ብልጫ ፣ በግብ እና በተደጋጋሚ ዕድሎች ጨዋታዎቻቸውን ቢጀምሩም የኋላ ኋላ ጭንቀት ውስጥ ገብተው ተመልክተናል። ጭንቀቱን ስናስተውለው ተጋጣሚዎቻቸው ሀዲያ ሆሳዕና እና ሀዋሳ ከተማ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጫና ውስጥ እንዲገቡ ከማድረጋቸው ይልቅ ውጤቱ በሊጉ አናት የሚፈጥረው ለውጥ የፈጠረባቸው ጫና አይሎ እናየዋለን።

በእርግጥ የመጨረሻ ደቂቃ ፈተናው ቅዱስ ጊዮርጊስን ጥሎ ፋሲልን በማሳለፍ የነጥብ ልዩነቱን ወደ አንድ ዝቅ ያድርግ እንጂ ሁለቱም ጨዋታዎቻቸውን የጀመሩበት እና የጨረሱበት ሁኔታ የቻምፒዮንነት ፍልሚያው ያሳደረባቸውን የሥነ ልቦና ጫና ለመገንዘብ ያስችለናል። ነገም እንደሳምንቱ ከጨዋታ በፊት ከፍ ባለ መጋጋል ወደ ሜዳ በመግባት ተጋጣሚዎቻቸውን የሚያስጨንቅ አጀማመር እንደሚያደርጉ ይታመናል። ከተጋጣሚዎች ለሚኖረው የጨዋታም ሆነ የውጤት ብልጫ ግብረ መልስ የሚኖራቸው ምላሽ ግን ነገ ምሽት በሰንጠረዡ አናት ላይ ማን ተቀምጦ ልናይ እንደምንችል የመወሰን አቅሙ ከፍ ያለ መሆኑ ከታክቲካዊ ጉዳዮች በላይ አዕምሯዊ ሁኔታዎች የጨዋታዎቹን ውጤቶች የመወሰን አቅም እንዳላቸው ይነግረናል።

ስለጨዋታዎቹ ይህንን ካልን በማስቀጠል ሦስቱን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርበናል።

አዲስ አበባ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

የእርስ በእርስ ግንኘነት

– በድኖቹ እስካሁን የተገናኙባቸው ሦስት ጨዋታዎች በሙሉ በሲዳማ ቡና አሸናፊነት የተጠናቀቁ ነበሩ። በዚህም ሲዳማ ቡና አምስት ግቦች ሲያስቆጥር አዲስ አበባ ከተማ ሦስት ግቦች አሉት።

የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ፣ ረዳቶች ዳዊት ገብሬ እና ደረጀ አመራ ፣ አራተኛ ዳኛ ዮናስ ማርቆስ

ተጨማሪ ዳኞች – አማን ሞላ እና ተስፋዬ ንጉሴ

ግምታዊ አሰላለፍ

አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል ተሾመ

አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ልመነህ ታደሰ – አዩብ በቀታ – ሮቤል ግርማ

ሙሉቀን አዲሱ – ቻርለስ ሩባኑ – ኤልያስ አሕመድ

እንዳለ ከበደ – ፍፁም ጥላሁን – መሐመድ አበራ

ሲዳማ ቡና (4-1-4-1)

መክብብ ደገፉ

አማኑኤል እንዳለ – ጊት ጋትኩት – ተስፋዬ በቀለ – ሰለሞን ሀብቴ

ሙሉዓለም መስፍን

ሀብታሙ ገዛኸኝ – ዳዊት ተፈራ – ፍሬው ሰለሞን – ይገዙ ቦጋለ

ሳላዲን ሰዒድ

ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የእርስ በእርስ ግንኙነቶች

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ዘጠኝ ጊዜ የእርስ በእርስ ጨዋታዎች አድርገዋል። በውጤቱ ሦስት ጊዜ ሲሸናነፉ ሦስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ቡና 11 ፣ ፋሲል 8 ግቦችን ማስመዝገብም ችለዋል።

የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ ፣ ረዳቶች ትግል ግዛው እና መሐመድ ሁሴን ፣ አራተኛ ዳኛ ባህሩ ተካ

ተጨማሪ ዳኞች – ፍቅሬ ወጋየሁ እና ማዕደር ማረኝ

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)

ሚኬል ሳማኪ

ሰዒድ ሀሰን – አስቻለው ታመነ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ይሁን እንዳሻው

ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – ሱራፌል ዳኛቸው- በረከት ደስታ

ሙጂብ ቃሲም

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

በረከት አማረ

ኃይሌ ገብረትንሳይ – አበበ ጥላሁን – ቴዎድሮስ በቀለ – አስራት ቱንጆ

አማኑኤል ዮሐንስ – አብነት ደምሴ – ታፈሠ ሰለሞን

አላዛር ሽመልስ – እንዳለ ደባልቄ – ዊሊያም ሰለሞን

አርባምንጭ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የእርስ በእርስ ግንኘነት

– ተጋጣሚዎቹ እስካሁን በሊጉ 15 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 10 በማሸነፍ ቀዳሚው ሲሆን አርባምንጭ 2 አሸንፎ በቀሪዎቹ 3 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ 27 ሲያስቆጥር አርባምንጭ 10 ማስቆጠር ችሏል።

የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ፣ ረዳቶች ፋሲካ የኋላሸት እና ይበቃል ደሳለኝ ፣ አራተኛ ዳኛ ተከተል ተሾመ

ተጨማሪ ዳኞች – ሲራጅ ኑርበገን እና ኤልያስ አበበ

ግምታዊ አሰላለፍ

አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)

ይስሀቅ ተገኝ

ወርቅይታደስ አበበ – አሸናፊ ፊዳ – በርናንድ ኦቼንግ – ተካልኝ ደጀኔ

ፀጋዬ አበራ – አቡበከር ሸሚል – እንዳልካቸው መስፍን – ሱራፌል ዳንኤል

አህመድ ሁሴን – በላይ ገዛኸኝ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ቻርለስ ሉኩዋጎ

ሱሌይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ደስታ ደሙ – ሄኖክ አዱኛ

በረከት ወልዴ – ጋቶች ፓኖም

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ከነዓን ማርክነህ – ቸርነት ጉግሳ

ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ