የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 3-0 ኢትዮጵያ ቡና

በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ወሳኝ ድል ካስመዘገበ በኋላ አሰልጣኞች ኃሳባቸውን አካፍለዋል።

አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ – ፋሲል ከነማ

ስለጨዋታው

“ትንሽ ፀሀዩም ኃይለኛ ስለነበር የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ትንሽ ከብዶን ነበር። ሁለተኛው ላይ ግን ጥሩ ነበርን።

ስለሙጂብ እና ሱራፌል ጥምረት

“ሱራፌል እና ሙጂብ ሁሌም አምናም ቢሆን ጥሩ ነበሩ። ዘንድሮም ደግሞ ሙጂብ ባህር ዳር ከመጣን በኋላ ማች ፊትነሱ በጣም ጥሩ ነበር። የሱራፌል ኳሶችም ብዙ ጊዜ እንደዚህ ናቸው። ሙጂብ ብዙ ጊዜ የሚጠቀማቸው የእሱን ኳሶች ስለሆነ ከዚህም በላይ መስራት ይችላሉ።

ስለፍፁም ቅጣት ምቱ መቺ

“የእኛ የፍፁም ቅጣት ምት መቺያችን ያሬድ ነው። ግን ሙጂብ ሐት-ትሪክ እንዲሰራ ፈልገን ነበር። ሙጂብ ደግሞ ሱራፌል እንዲያገባ ስለፈለገ እነሱ በራሳቸው ያደረጉት ነው።

ስለቀጣዩ የጊዮርጊስ ጨዋታ

“እኛ እስካሁን በመጣንበት መንገድ ነው እስከመጨረሻው የምንሄደው። ስለዚህ የሚሆነውን ማየት ነው።”

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለጨዋታው

“ከጀርባ የተከፈቱ ቦታዎች ነበሩ፤ በመጀመሪያው በሁለተኛውም አጋማሽ ያንን ቦታ ነበር የሚፈልጉት ፤ ከኋላ የሚነሱ ሰዎች አሏቸው። ያንን ቦታ በትክክል መሸፈን አልቻልንም። አብዛኛው ቁጥራቸውን ራሳቸው ሜዳ ላይ አከማችተው ነበር የሚጫወቱት።

ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ስላለማድረጋቸው

“ከኋላ ያሉት የነሱ ተጫዋቾች በጣም ዲሲፕሊንድ ሆነው ቦታውን ዘግተዋል። ስለዚህ ቀስ እያልን ወደእነሱ ጎል ለመቅረብ የሚደረግ ሂደት ነበር። በዛ ውስጥ የሚቆራረጡ ኳሶች ነበሩ። በሚጣሉ ኳሶች ለመሄድ አስቸጋሪ ነው። የእነሱ ኋላ ላይ ያሉት አራት ሰዎች ብዙ የሚነቅሉ ስላልሆኑ ቀስ እያለን ለመጠጋት ነበር ያሰብነው። በዛ ውስጥ በሚቋረጡ ኳሶች ተመልሰን ተጠቅተናል።

ስለአማካይ ክፍሉ ድክመት

“ክፍት ቦታዎች ነበሩ። እነዛ ለመጫወት የምንከፍታቸው ቦታዎች ናቸው ፤ የግድ ለመጫወት መክፈት ስላለብን ማለት ነው። በዛ መንገድ ቀስ እያልን ከሜዳችን መውጣት ችለናል። ግን ከዛ በኋላ መሀል ላይ የሚቆረጡትን ኳሶች ያ ለመጫወት የከፈትነውን ቦታ ወዲያው ስለሚጠቀሙ ፣ ያንን የመዝጋት እና የማቆም ፣ መጀመሪያ የምንሄዳቸውን ነገሮች በቀላሉ ያለማበላሸት ነገር ነው። እና የመጡበት መንገድ ብዙም የተለየ አልነበረም። ግን የእኛ ችግር የነበረው መጀመሪያ ለመጫወት የከፈትነውን ቦታ ኳሶቹን ስናጣ በደንብ አለመዝጋታችን ነው።

ስለመጨረሻው ጨዋታ ዓላማ

“እኛ ሁል ጊዜ የቡና ተጫዋቾች ነን። ሁሌም ለቡና ክብር ነው የምንጫወተው። እኛ ስለሌላው ቡድን የሚመለከተን ነገር የለም። የቡናን መለያ ለብሰን ነው የምንገባው። ስለዚህ እስከመጨረሻው ድረስ ለቡና ክብር እንጫወታለን።”

ያጋሩ