በከነዓን ማርክነህ ብቸኛ ግብ አርባምንጭ ከተማን የረታው ቅዱስ ጊዮርጊስ የአንደኝነት ደረጃውን ከሰዓታት ቆይታ በኋላ ከፋሲል ከነማ መልሶ ተረክቧል።
አርባምንጭ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን ከረታበት ጨዋታ ተካልኝ ደጀኔን በወርቅይታደስ አበበ ፣ ጉዳት ያገኘው ኤሪክ ካፓይቶን ደግሞ በፀጋዬ አበራ በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ከሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ አንፃር ቅጣት ያለበት ፍሪምፖንግ ሜንሱን በደስታ ደሙ ዳግማዊ አርዓያን ደግሞ ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ሜዳ በተመለሰው ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ቀይሯል።
የተነቃቃ አጀማመር በታየበት ጨዋታ ቀዳሚ ደቂቃዎች ቀጥተኛ ኳሶች ወደ ሁለቱ ሳጥኖች በተደጋጋሚ ሲጣሉ የታየበት ነበር ፤ ጨዋታው ግብ ለማስተናገድም እምብዛም አልቆየም። 8ኛው ደቂቃ ላይ ሱለይማን ሀሚድ ከነዓን ያስጀመረውን ጥቃት ካቋረጡት የአርባምንጭ ተጨዋቾች በግንባር የነጠቀውን ኳስ ከነዓን ማርክነህም በግንባር አሳልፎለት እስማኤል ኦሮ አጎሮ ሞክሮ ይስሀቅ ተገኝ ሲያድንበት ራሱ ከነዓን ደርሶ ጎል አድርጎታል።
ከግቡ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጠንቀቅ በማለት የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን መጠባበቅን ምርጫው አድርጓል። አርባምንጮች ደግሞ ጊዮርጊስ ከሜዳው ለመውጣት ሲሞክር ከኳስ ውጪ ጫና በማሳደር እና የተነጠቁ ኮሶችን ወደ ፊት በማድረስ ተንቀሳቅሰዋል። ቡድኑ 15ኛው ደቂቃ ላይ ባደረገው ሙከራ መላኩ ኤልያስ ከቀኝ ያሻገረለትን አህመድ ሁሴን ከሳጥን ውስጥ መትቶ ኢላማውን ሳያገኝ ቀርቷል። የፈረሰኞቹ የመልሶ ማጥቃት ሀሳብ ደግሞ 20ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ ተቃርቦ ነበር። በዚህም ቡድኑ በቀኝ መስመር ፈጣን ጥቃት ሰንዝሮ በቁጥር ብልጫ ጭምር ባገኘው ዕድል አማኑኤል ገብረሚካኤል ከሳጥን ውስጥ አክርሮ የመታው ኳስ ኢላማውን ሳያገኝ ቀርቷል።
ጨዋታው ወደ ውሀ ዕረፍት ሊያመራ ሲል ቻርለስ ሉኩዋጎ የፀጋዬ አበራን ተሻጋሪ ኳስ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ አህመድ የማስቆጠር ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከውሃ ዕረፍቱ መልስም የአርባምንጮች የኳስ ቁጥጥር ይበልጥ ከፍ ብሎ መታየት ቢጀምርም በረጅም ኳሶች በሚቋጨው የጨዋታ ፍሰቱ ቡድኑ በግብ ፊት መረጋጋትን አላሳየም። ከዚህ መሀል 32ኛው ደቂቃ ላይ መላኩ ኤልያስ ያደረሰውን ኳስ አህመድ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ በጥሩ ሁኔታ በደረቱ ቢያወርደውም በረጅም ርቀት የሳተበት አንዱ ነበር።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከእንቅስቃሴ ይልቅ ከቆሙ ኳሶች የተሻለ ጥቃት መሰንዘር ሲችሉ 40ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ ከማዕዘን ምት በግንባር ያደረገው ሙከራ ተጠቃሽ ነበር። የፊት አጥቂው አህመድ ሁሴንን ያነጣጠሩት የአርባምንጭ ኳሶች አጋማሹ ሲቃረብ ጥሩ ዕድል ቢያስገኙም አጥቂው ፍሬያማ መሆን አልቻለም። 42ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ የተላከለትን ረጅም ኳስ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች በአግባቡ ባላራቁበት አጋጣሚ ጥሩ ዕድል ቢያገኝም ሉኩዋጎን አልፎ ለሱራፌል ዳንኤል መስጠትን የመረጠ ሲሆን የሱራፌል ሙከራ በተከላካዮች ተደርቧል።
ከዕረፍት መልስ የአዞዎቹ ረጃጅም ኳሶች የፈጠሩትን ተፅዕኖ ለመቀንነስ ፈረሰኞቹ አማኑኤል ተረፉን በሄኖክ አዱኛ ቦታ ሲተኩ አርባምንጮች ደግሞ የመስመር ጥቃታቸውን ለማሻሻል አሸናፊ ተገኝን በሱራፌል ዳንኤል ለውጠው አስገብተዋል። በእንቅስቃሴ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከአጋማሹ በፊት የነበረው የአርባምንጭ ብልጫ እንዳይቀጥል ማድረግ ሲችሉ በሁለቱም በኩል የፊት አጥቂዎቹን ለማግኘት የሚላኩ ቀጥተኛ ኳሶች ማታየት ጀምረዋል። ከሁለተኛው አጋማሽ ጋር አብሮ የጀመረው ዝናብ መጠናከሩን ተከትሎም ጨዋታው ይበልጥ ከባድ እንዲሆን ያደረገው ሲሆን ቡድኖቹ ግን በሚችሉት መጠን ቀጥተኛ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ከመሞከር አልቦዘኑም።
ወደ ሳጥን በማድረሱ በኩል የተሻለ የተደራጀ ቅርፅ የነበራቸው ጊዮርጊሶች 62ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ወልዴ ከሳጥን ውጪ መትቶ በተከላካዮች ተጨርፎበት በወጣው ኳስ የተሻለውን ሙከራ አድርገዋል። 69ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አማኑኤል በተከላካዮች መሀል የፈጠረውን ያለቀለት ዕድል ቸርነት ጉግሳ ሞክሮ ይስሀቅ ተገኝ አድኖበታል። ከሙከራዎቹ ባሸገርም ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተሻለ ሁኔታ ጨዋታውን በመቆጣጠር እንቅስቃሴው ወደ አርባምንጭ ሜዳ ላይ እንዲያመዝን ማድረግ ችለዋል።
እስከመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ድረስ አድራሻ አልባ በሆኑ ረጃጅም ኳሶች እና የቆሙ ኳሶች በቀጠለው ጨዋታ ተጋጣሚዎቹ በአየሩ እና በሜዳው ሁኔታ ተፈትነዋል። ቀጥሎ ባየነው ከባድ ሙከራ 81ኛው ደቂቃ ላይ አርባምንጮች የጊዮርጊስን መልሶ ማጥቃት ካቋረጡ በኋላ አሸናፊ ተገኝ በአግባቡ ማራቅ ሳይችል ቸርነት ጉግሳ ያገኘውን ዕድል አክርሮ ሞክሮ በይስሀቅ ተገኝ ተመልሶበታል። 84ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ፀጋዬ አበራ ከሳጥን ውጪ አስደንጋጭ ሙከራ አድርጎ በቻርለስ ሉኩዋጎ ቅልጥፍና ድኖበታል።
ጨዋታው ወደ ማብቂያው ሲቃረብ 90ኛው ደቂቃ ላይ ባስመለከተን ክስተት የአርቢትሩን ውሳኔ መቀበል ያልቻለው መላኩ ኤልያስ ሁለት ተከታታይ ቢጫዎችን ተመልክቶ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ጨዋታውም ሌላ ግብ ሳያስተናግድ በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት እንዲቋጭ ሆኗል።
ውጤቱን ተከትሎ የነጥብ ድምሩን 62 ያደረሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሰንጠረዡ አናት ሲመለስ አርባምንጭ ከተማ በ40 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል።