ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሰዓታት በፊት የተነጠቀውን የደረጃ ሰንጠረዥ አናትን መልሶ መረከቡን ካረጋገጠበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች ድህረ ጨዋታ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ስለ ድሉ
“ጨዋታው ውጥረት ያለበት ከባድ ጨዋታ ነበር፡፡ በዚህ ላይ ዝናብ ዘንቧል የተሻለ ነገር ለማድረግ ብዙ ዕድሎች አግኝተናል ፣ ያገኘነውን አጋጣሚ ጎል አግብተን ውጤት ይዘን ወጥተናል፡፡
ዝናብ ከመዝነቡ አኳያ ከመጀመሪያው አጋማሽ ሁለተኛው አጋማሽ የተለየ ስለመሆኑ
“የጨዋታው ሁለቱ ምዕራፍ ይለያያሉ፡፡ በመጀመሪያው ደረቅ ነበር። የምንጫወትበት መንገድ በትክክል ነበር ፣ ሁለተኛው ላይ ግን በይበልጥ ጥንቃቄ ያለው ጨዋታ እና ባገኘነው አጋጣሚ ለመጫወት ነበር ያሰብነው ያም ነገር ተሳክቶልን ውጤት ይዘን ወጥተናል፡፡
ስለ ዳግማዊ አርአያ እና ያብስራ ተስፋዬ ቅያሪ ጥቅም
“ለመጫወት የሚመች አልነበረም በጣም ዝናብ ነው። ኳሶችን ኮንትሮል ማድረግም አትችልም። ባለው አጋጣሚ ሽፋን እየሰጡ ወደ ፊት ሄደን ጥሩ ነገር ለማድረግ ፈልገን ነበር። ሁለት ሦስት ኳሶችንም አግኝተን ነበር አልተጠቀምንበትም። እግርኳስ ይሄ ነው ውጤቱን ይዘን ወጥተናል፡፡
ስለ መጨረሻው ወሳኝ ጨዋታ
“የሚቀጥለውም ሌላ ጠንካራ ጨዋታ አለ። ለዚያ ጨዋታ ተዘጋጅተን የተሻለ ነገርም አድርገን ፣ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ስለደረስን ውጤቱን ከእግዚአብሔር ጋር አምጥተን ለማሸነፍ ተዘጋጅተን እንመጣለን፡፡”
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ
ስለ ዘጠና ደቂቃው
“በምንፈልገው ደረጃ ሄዷል ማለት አልችልም፡፡ እንደተጀመረ በተወሰነ መልኩ ጎል ተቆጥሮብናል፡፡ ከዚያ ጎሎችን ለማስቆጠር ጥረት አድርገናል፡፡ አጋጣሚዎችን ፈጥረን ነበር ፣ በሁለተኛው አጋማሽ ዝናብ ከመጣ በኋላ ቶሎ ቶሎ ከሜዳ እየወጣን ለማጥቃት ነበር ጥረት ያደረግነው አልተሳካም፡፡
ቡድኑ ስለነበረበት ድክመት
“ሳጥን ውስጥ ቁጥራችን በምንፈልገው ልክ አልበዛም። ስለዚህ የምንፈልገውን ጎል አላገኘንም፡፡
ስለ መጨረሻ የሊጉ ጨዋታ
“ደረጃችንን ለማሻሻል አሁን ሰባተኛ ደረጃ ላይ ነው ያለነው ነጥቦችን የምንጨምር ከሆነ ከዚህም የተሻለ ደረጃ ይዘን ለመጨረስ ነው የምናቅደው፡፡”