ሀዋሳ ከተማዎች ደካማ በነበሩበት ጨዋታ አስፈላጊውን ሦስት ነጥብ ከመከላከያ መንጠቅ ችለዋል።
መከላከያዎች በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት ከአዳማ ጋር ያለግብ አቻ ከተለያየው ስብስብ አራት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም ክሌመንት ቦዬ ፣ አሌክስ ተሰማ ፣ ዳዊት ማሞ እና ቢኒያም በላይን አስወጥተው በምትካቸው ሙሴ ገ/ኪዳን ፣ ኢብራሂም ሁሴን ፣ ገናናው ረጋሳ እና ባድራ ናቢ ሲላን ተክተው አስገብተዋል ፤ በአንፃሩ በፋሲሎች የተረቱት ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ ባደረጓቸው አምስት ለውጦች መሀመድ ሙንታሪ ፣ ካሎጂ ሞንዲያ ፣ ዳንኤል ደርቤ ፣በቃሉ ገነነ እና ኤፍሬም አሻሞን አስወጥተው በምትካቸው ምንተስኖት ጊንቦ ፣ አዲስዓለም ተስፋዬ ፣ ሄኖክ ድልቢ ፣ ዮሀንስ ሴጌቦ ፣ መስፍን ታፈሰን በቋሚ ተሰላፊነት አስጀምረዋል።
መከላከያዎች ከፍተኛ የጫና ማዕበል በመፍጠር በጀመሩት ጨዋታ ኳሶችን በመቀባበል በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ተደጋጋሚ ምቃቶችን በተለይ ከመስመሮች በሚነሱ ኳሶች ለመሰንዘር ሞክረዋል።
ፈጠን ባለ አጀማመር የጀመረው ጨዋታው በሂደት ግን መቀዛቀዝ ውስጥ ገብቷል ፤ ምንም እንኳን ኢላማውን የጠበቁ ሙከራዎችን መመልከት ባልቻልበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ መከላከያዎች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ ረገድ አንፃራዊ የበላይነት ነበራቸው።
በአጋማሹ አስር የግብ ሙከራዎችን ያደረገው ቡድኑ በተለይ በ36ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ተሾመ በላቸው ያሻገረለትን ኳስ ምንተስኖት አዳነ በሳጥን ጠርዝ በግራ እግሩ የሞከራት እና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።
እጅግ ደካማ የመጀመሪያ አጋማሽ ያሳለፉት ሀዋሳ ከተማዎች ኳሶች መሀል ሜዳ ከተሻገሩ በኃላ የነበራቸው አፈፃፀም እጅግ ደካማ ነበር በዚህም በአጋማሹ ምንም አይነት የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።
ቀዝቃዛ በነበረው ጨዋታ መከላከያዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የመገባደጃ ደቂቃዎች ላይ በመጀመሪያ ኢላማውን በጠበቀ ሙከራ ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል ፤ ግሩም ሀጎብ ከመሀል ሜዳ አካባቢ በረጅሙ የላከውን የቆመ ኳስ ተሾመ በላቸው ከሀዋሳ ተከላካዮች አፈትለኮ በመውጣት አስቆጥሯል።
በ47ኛው ደቂቃ ግሩም ሀጎስ በቀጥታ ከረጅም ርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ ወጣቱ ግብ ጠባቂ ምንተስኖት ከበደ በአግባቡ መቆጣጠር ባለመቻሉ ለጥቂት ከመስመር ላይ ባዳነበት ኳስ ተደጋጋሚ ጫና በመፍጠር የጀመሩት መከላከያዎች በ51ኛው ደቂቃ ላይ አዲሱ አቱላ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ አክርሮ የመታውን ኳስ ምንተስኖት ጊንቦ አድኖበታል።
ነገርግን የሁለተኛው አጋማሽ አጀማመራቸው እንደ መጀመሪያው ቀዝቃዛ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በ58ኛው ደቂቃ አቻ መሆን ችለዋል ፤ ከመከላከያ ግብ ትይዩ ያገኙትን የቅጣት ምት ኳስ ኳስ ብሩክ በየነ በቀጥታ በመምታት የአቻነት ግቧን አስቆጥሯል።
ግብ ካስተናገዱ ወዲህም ቢሆን በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የቀጠሉት መከላከያዎች ከክፍት ጨዋታ ከእንቅስቃሴ እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል ፤ በተለይ በ68ኛው ደቂቃ ምንትስኖት አዳነ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ያደረገውን ግሩም ሙከራ ምንተስኖት አድኖበታል።
በጨዋታው ደካማ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች አሁንም በድንገት ሳይጠበቅ በጨዋታው ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል ፤ 69ኛው ደቂቃ ላይ ኢማኑኤል ላርዬ መሀል ሜዳ ላይ ከተነጠቀው ኳስ በተነሳው የማጥቃት ሂደት ወንድማገኝ ሀይሉ በመከላከያ ተጫዋቾች ትርምስ ታግዞ ቡድኑን መሪ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል።
ከመምራት ወደ አሳዳጅነት የተለወጡት መከላከያዎች አሁንም ከመስመር ከሚነሱ ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር ችለዋል ፤ በተለይም የአቻነቷን ግብ ባስተናገዱ በጥቂት ደቂቃዎች ልዮነት እስራኤል እሸቱ ከምንተስኖት ጊንቦ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ኳሷን አስረዝሟት ሳይጠቀምባት የቀረችው እድል ተጠቃሽ ነበረች።
ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በአንዳንድ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ያስዋልን ሲሆን በተለይም በ82ኛው ደቂቃ ብሩክ በየነ ሳይጠቀምባት የቀረችው አጋጣሚ በጣም አስቆጭ ነበረች።
ሀዋሳ ከተማ ጨዋታውን በድል መወጣታቸውን ተከትሎ በ45 ነጥብ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ በአንፃሩ መከላከያዎች ደግሞ በነበሩበት 34 ነጥብ ወደ 11ኛ ደረጃ ተንሸራተዋል።