ሀዋሳ ከተማ ከመመራት ተነስቶ በማሸነፍ በሦስተኛነት ፉክክሩ ከቀጠለበት ጨዋታ በኋላ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ይህንን ብለዋል።
አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ – መከላከያ
ስለሁለቱ አጋማሾች ልዩነት
“ተነጋግረን ነበር ‘የማይሆኑ ስህተቶች ጎል አካባቢ አትስሩ’ በሚል ነበር። ሁለት መስጠት የማይገቡንን ስህተቶች ሰርተናል። መጀመሪያ ደግሞ መጨረስ የሚገቡንን አልጨረስንም። ውድድር መደማለቁ ሲመጣ የተጨዋቾች አዕምሮ ሁኔታ የተራጋጋ አይሆንም። ጨዋታው ግን ጥሩ ነበር።
20 ሙከራ ቢያደርጉም የግብ ማግባት ችግራቸው ስለመቀጠሉ
“በጭንቅላት ተዘናግቶ መምጣት ነው። አልፈናል ፣ እዚህ ደርደናል ፣ ጊዮርጊስን አዲስ አበባ አያሸንፈውም ወይም ፋሲልን ድሬዳዋ አያሸንፈውም የሚል ደካማ የተጨዋቾች አስተሳሰብ ነው። ያንን ነው የተመለከትኩት ዛሬ። ለምሳሌ ሀዋሳ ለደረጃ ነው የሚጫወተው ግን በከፍተኛ ስሜት ሲጫወቱ የነበሩት እነሱ ናቸው ፤ ያንን አስጠብቆ ለማውጣት። እና የተጨዋቾች የጭንቅላት መዘናጋት የያዝነውን ውጤት ይዘን እንዳንወጣ አድርጎናል።
ስለከሰዓቱ ጨዋታ እና ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ስለሚያደርጉት ጨዋታ
“እንግዲህ ጨዋታውን ማየት ነው። የሚሆኑትን ነገሮች መመልከት ነው። በእኛ እጅ ያለ ስላልሆነ የምንቆጣጠረው ነገር አይደለም። ስለዚህ ያሉትን ሁኔታዎች ማየት ነው።”
አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ
ስለጨዋታው
“እንደባለፈው በሦስት ተከላካይ ጀምረን ነበር። በሦስት ስንጀምር ስህተቶችን እየሰራን ነው። ረጃጅም ኳሶች ይጣሉ ነበር ፤ አሁንም ጀርባን ያለማየት ችግሮች ተከላካዮቻችን ላይ ስለሚታዩ የግድ ያለውን አቋቋም ለማስተካከል ወደ 4-3-3 ነው የቀየርነው። የእነሱን የመስመር ተጫዋቾች በማቆም ከእዛ ደግሞ ከፊትም መጀመሪያም እናንስ ስለነበር አሰላለፍ ስንቀይር ማጥቃቱንም መከላከሉንም ሚዛናዊ አደረግን። በተለይ ከዕረፍት በኋላ ግብ ያስቆጠርነውም ከዛ አንፃር ነው።
ስለብሩክ በየነ የኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር
“በእርግጠኝነት በቀሪው ጨዋታ ላይ አግብቶ ኮከብነቱን ይወስዳል ብዬ አስባለሁ። አንደኛው አቡበከር ነው ፤ አቡበከር አይጫወትም። የሲዳማው ተጫዋች ይገዙም አለ። ሌሎች ደግሞ የሚጫወቷቸውን ቡድኖች ስታይ የማግባት ዕድላቸው ትንሽ ጠበብ ስለሚል እሱ ይሄን ነገር ያሳካል ፤ ይገባዋል ብዬ ነው የማስበው።
ዛሬ የመሰለፍ ዕድል ስላገኘው ምንተስኖት ጊንቦ
“የመጫወት ዕድል ያላገኘው ሌሎቹ ከእሱ የተሻለ ለምድ ስላላቸው ነው። ዕድሉን ሲያገኝ ደግሞ እነሱን መርሳት እንደሚችል ነው ዛሬ ያሳየው። ከልምድ ጋር የተገናኙ በጣም ጥቃቅን ስህተቶች ነው የሚታይበት። ከዛ ውጪ ጊዜ አጠባበቁ ፣ ቡድኑን የሚመራበት መንገድ ፣ ሰዓቱን የሚጠቀምበት መንገድ ወደ ፊት ተስፋ ያለው ግብ ጠባቂ እንደሆነ ነው የሚያሳየው።”