የዕለቱ የመጀመሪያ በነበረው መርሐ-ግብር ሲዳማ ቡና አዲስ አበባ ከተማን በመርታት ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ያለው እድል ሲያሰፋ አዲስ አበባ ከተማዎች ደግሞ በአንፃሩ በሊጉ የመቆየት ተስፋቸው ዳግም አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።
አዲስ አበባ ከተማዎች ሰበታ ከተማን ከረታው ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ በአምስት ቢጫ መሰለፍ ባልቻለው ሪችሞንድ አዶንጎ ምትክ ቢኒያም ጌታቸውን ብቻ ቀይረው የቀረቡ ሲሆን በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች ከወልቂጤ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ሁለት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም ተከላካይ መስመር ላይ ተስፋዬ በቀለ እና ሰለሞን ሀብቴ ወጥተው በምትካቸው ያኩቡ መሀመድ እና መሀሪ መና ወደ መጀመሪያ ተመራጭነት ተመልሰዋል።
ነቃ ባለ ፉክክር የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያ አደገኛ ሙከራ ገና ጨዋታው በተጀመረው በ5ኛው ደቂቃ የተመዘገበ ነበር ፤ የአዲስ አበባው አምበል ሮቤል ግርማ በተወሰነ መልኩ ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም በቀጥታ ከቆመ ኳስ ወደ ግብ የላከው ኳስ በመክብብ እና የግቡ አግዳሚ በመከነበት አጋጣሚ ነበር።
ታድያ በዚህ ሙከራ የጀመረው ጨዋታው ገና በ7ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች መሪ መሆን ችለዋል ፤ ፍሬው ሰለሞን ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ በሩቁ ቋሚ በነፃነት ያገኘው ሙሉዓለም መስፍን ኳሷን ተቆጣጥሮ በደካማው እግሩ ማስቆጠር ችሏል።
ነገርግን አዲስ አበባ ከተማዎች ምላሽ የሰጡት በሰከንዶች ልዮነት ነበር ፤ 8ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር አሰጋኸኝ ጴጥሮስ በረጅሙ በተጣለ ኳስ መነሻውን ባደረገ የማጥቃት ሂደት ሰሲዳማ ሳጥን ውስጥ ፍፁም ጥላሁን ያገኘውን ኳስ በግራ እግሩ በግሩም አጨራረስ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።
የአዲስ አበባ ከተማዎች የአቻነት ግብ ስትቆጠር የሲዳማ ቡናው የመሀል ተከላካይ ያኩቡ መሀመድ ኳሷን ለመከላከል ባደረገው ጥረት ራሱን መቆጣጠር ባለመቻሉ መረቡ በመበጠሱ የተነሳ ጨዋታው ለተወሰኑ ደቂቃዎች ተቋርጦ መረቡ ጥገና ተደርጎለት ነበር ጨዋታው ዳግም የቀጠለው።
እንደ አጀማመሩ መቀጠል ባልቻለው የመጀመሪያ አጋማሽ ምንም እንኳን ሲዳማ ቡናዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ በነበራቸው አጋማሽ የግብ እድሎችን በመፍጠር ረገድ ውስንነት ነበሩባቸው በአንፃሩ ጨዋታውን ለማሸነፍ የተሻለ ፍላጎት ያሳዩት አዲስ አበባ ከተማዎች በአጋማሹ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረት አድርገዋል በተለይም ከሳጥን ውጭ በቀጥታ በሚላኩ ኳሶች የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተመልክተናል።
በጨዋታው 37ኛው ደቂቃ ላይ ገና በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ቢጫ ካርድ የተመለከተው እና ተደጋጋሚ ጥፋቶች እየፈፀመ የነበረው የሲዳማ ቡናው የመሀል ተከላካይ ጊት ጋት በመኳንንት ካሳ ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በመጀመሪያ አጋማሽ የተወሰደባቸውን ብልጫ መቀልበስ የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች አጋማሹን ጫና ፈጥረው ተደጋጋሚ የማዕዘን ምቶችን በማግኘት ነበር የጀመሩት ፤ በአጋማሹም በመጀመሪያ አጋማሽ ተነጥለው የነበሩት የቡድኑ አጥቂዎችን የተሻለ ቁጥር ባለቸው የቡድን አጋሮቻቸው ሲታገዝ ተመልክተናል።
በ70ኛው ደቂቃ ታድያ ሲዳማ ቡና መሪነታቸውን ማሳደግ ችለዋል ፤ ሲዳማ ቡናዎች ከራሳቸው የሜዳ አጋማሽ በረጅሙ የላኩትን ኳስ ሰልሀዲን ሰዒድ በግንባሩ ሸርፎ ከተከላካይ ጀርባ ለመሮጥ ለተዘጋጀው ሐብታሙ ገዛኸኝ ያሳለፈለትን ኳስ ሐብታሙ በግሩም ቅልጥፍና በማስቆጠር ቡድኑን ዳግም መሪ አድርጓል።
ከግቧ መቆጠር በኃላ ሦስት ነጥቡ የግድ ይላቸው የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ውጤቱን ለመቀልበስ ይህ ነው የሚባል ጥረት ለማድረግ የተቸገሩ ሲሆን በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች ጨዋታውን በመቆጣጠር በእጃቸው የገባውን ነጥብ ለማስጠበቅ ያደረጉት ጥረት በስተመጨረሻው ፍሬ አስገኝቶላቸዋል።
ጨዋታው በሲዳማ ቡና የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ሲዳማ ቡናዎች ነጥባቸውን ወደ 47 በማሳደግ በነበሩበት 3ኛ ደረጃ ሲቀጥሉ ከሰሞኑ በሊጉ የመቆየት እድላቸውን አለምልመው የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች በ32 ነጥቦች ወደ 12ኛ ደረጃ ተንሸራተዋል።