የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 1-1 ድሬዳዋ ከተማ

በሊጉ ለመቆየት ብርቱ ትግል ተደርጎበት ነጥብ በመጋራት ከተጠናቀቀው ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ አሰልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡

አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ

ስለውጤቱ…?

“እኔ ብዙ አልከፋኝም። እንደሚታየው ጉልበት የሚፈጅ ጨዋታ ነው፡፡ ያሉት ተጫዋቾችም የሚችሉትን መስዋዕትነት ስለከፈሉ በውጤቱ ብዙ አልከፋኝም።

ስለነበረው የአጨራረስ አቅም…?

“አጥቂ አብዝተን ነው የገባነው፡፡ ስንጀምር ተደራቢ አማካይ አድርገን አጫውተናል። ብዙ አጥቂዎች ያበዛነው ለማግባት ነበር፡፡ በአስራ አራት በአስራ አምስት ደቂቃ ጎል ተቆጠረብን ፤ ከዚያ በኋላ ባለው መጓጓት ነው ግብ ላናገባ የቻልነው፡፡

ስለነበረው ያለመረጋጋት ችግር…?

“በተለይ ከዕረፍት በፊት የለም ነበር፡፡ ከዕረፍት በኋላ ግን የወሰናቸው ውሳኔዎች ትክክል ነበሩ፡፡ ሶስት ተጫዋቾች ማሳረፍ ስለነበረብን ሶስት ተጫዋቾችን አሳርፈን ገብተን የተሻለ እንቅስቃሴ አሳይተናል፡፡

አብዲሳ ጀማል ስላስቆጠራት ወሳኝ ግብ…?

“በጣም ወሳኝ ናት፡፡ ወደ ጨዋታ የመለሰችን የአብዲሳ ጎል ናት። ተጨማሪም ጎል ለማግባት አጥቅተን ለመጫወት ሞክረናል ፤ ስላልተሳካ ነው እንጂ የአብዲሳ ጎል ወሳኝ ጎል ነች፡፡

አዳማ ከተማ በሊጉ ይቆያል…?

“ሁሌም የምናገረው ነው፡፡ ስጀምር ስድስት ጨዋታ ነው የተሰጠኝ ፤ ስረከብ እንደምቆይ አውቀዋለሁ፡፡ አሁንም ሰፊ ዕድል ነው ያለን። ከጨዋታው በጣም ያስደሰተኝ ነገር እስከ መጨረሻው ውጥረት ያለው መሆኑ ሊጉ በጣም ደማቅ ማድረጉ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው ነገር የለም፡፡ ሁሉም በራሱ ላብ እና በራሱ ድካም የሚወስደው ዋንጫ ነው ፤ በራሱም ድካም ነው ከመውረድ እና መውጣት የሚድነው ፤ ስለሆነም ሊጉን በጣም አሳምሮታል፡፡ አሰልጣኞችም በፊት ከነበረው ሌላ ሌላ ነገሮች ተላቀው ሊጉን ያሳመረው ውድድር ነው። በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡

አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለ ጨዋታው…?

“ሜዳ ላይ ያየነው እንቅስቃሴ ተጫዋቾቼ ያላቸውን መቶ ፐርሰንት ሰጥተዋል ማለት እችላለሁ፡፡ በእንቅስቃሴ ረገድ ግን ያገኘነውን ያለ መጠቀም ችግሮች ነበሩብን ፤ በሁለቱም አርባ አምስት ላይ ከዛ ውጪ የነበረው ነገር በጣም ደስ የሚል ነው፡፡

ስለ ነበረው የጨዋታ አቀራረብ…?

“አነስተኛ የተጫዋች ቁጥር ነው ይዘን የምንሄደው። እነሱ ጥቅጥቅ አድርገው ለመከላከል ይሞክራሉ ስለዚህ ያንን ሰብሮ ለመግባት ችግሮች ነበሩብን፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን የምናገኛቸው የግብ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ በተለይ በመጀመሪያው አርባ አምስት እና ሁለተኛውም አርባ አምስት ላይ ያለ መጠቀም ችግሮች በምንፈልገው ልክ እንዳንሄድ አድርጎናል፡፡

ሄኖክ አየለ ወደ ኋላ እየተሳባ ስለሚጫወትበት መንገድ እና ስለ ተወሰደው ዕርምት…?

“አሁን እኛ ከኋላ ያለን አራት ተከላካይ ወደ ፊት በዕገዛ ደረጃ ካልሆነ ተጠግቶ እንማይጫወት እናውቅ ነበርና ያንን ለማስተካከል ጥረት አድርገናል። ግን እንዳልኩህ ሄኖክ ያለቁ ኳሶችን ይፈልጋል ያንን የማቀበል እጥረቶች ነበሩ። ያ ነው ሄኖክ እንደ በፊቱ ጎል ላይ ያለውን ነገር እንደፈለገ እንዳይሄድ ያደረገው፡፡

ቡድኑ በሊጉ የመቆየት ተስፋው…?

“ዛሬ ላይ እንዲህ ነው ብሎ ማለት አይቻልም፡፡ ልክ አሁን ሻምፒዮን ማን ሊሆን ይችላል ብለን እንደምንለው ሁሉ ላለመውረድ በሚደረገው ሶስተኛው ቡድን ማን ሊሆን ይችላል የሚለውን እከሌ ማለት አይቻልም፡፡ ይሄን የምናውቀው ሰላሳኛ ሳምንት ካለቀ በኋላ እዛ ላይ በምናየው ውጤት ተመስርተን እከሌ ሻምፒዮን ይሆናል፣ ዕከሌ ወርዷል ብለን መናገር እንችላለን፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ ተስፋ አለን፡፡ አሁንም ያላለቁ ዕድሎች አለን። ከፊት ያለውን ጨዋታ በአግባቡ ተጠቅመን ቡድናችንን በ2015 በሊጉ ተሳታፊ ለማድረግ ጠንክረን እንሰራለን፡፡”