ሀዲያ ሆሳዕና ከዚህ ቀደም በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የተሰጠበትን ውሳኔ ተግባራዊ አላደረገም በሚል የዕግድ ውሳኔ ተላልፎበታል።
ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ለ15 ተጫዋቾች ደሞዝ በአግባቡ አለመክፈሉን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፒሊን ኮሚቴ ደሞዛቸው እና ጥቅማጥቅማቸው እንዲከፈል ውሳኔ አሳልፎ እንደነበር አይዘነጋም።
የተወሰነው ውሳኔ ተገቢ አይደለም በማለት ሀዲያ ሆሳዕና ይግባኝ ቢጠይቅም ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ጉዳዩን በድጋሜ ከመረመረ በኋላ የዲሲፒሊን ኮሚቴ ውሳኔ ተገቢ ነው በማለት ውሳኔውን በማፅደቅ በሰባት ቀን ውስጥ የደሞዝ ክፍያቸው እንዲፈፀም ትዕዛዝ እንዳስተላለፈ ይታወቃል። ሀዲያ ሆሳዕና ክለብም ቅሬታ ከቀረበበት አስራ አምስት ተጫዋቾች መካከል የዘጠኝ ተጫዋቾች ክፍያ ቢፈፅምም የብሩክ ቃልቦሬ፣ አማኑኤል ጎበና፣ ሱሌይማን ሀሚዲ፣ ተስፋዬ በቀለ፣ አዲስ ህናፃ እና ደረጄ አለሙን ክፍያ ተግባራዊ ባለማድረጉ ተጫዋቾቹ አቤቱታቸውን አቅርበዋል።
የተጫዋቾቹ ጠበቃ ብርሀኑ በጋሻው እንዳደረሱን መረጃ ከሆነ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጉዳዮን ሲከታተል ቆይቶ ሀዲያ ሆሳዕና እግርኳስ ክለብ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ በሰጠው ቀነ ገደብ ውሳኔውን ተግባራዊ አላደረገም በማለት በዛሬው ዕለት ከቀጣዩ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ጀምሮ የታገደ መሆኑን በደብዳቤ አሳውቋል።
በሌላ ዜና በሀድያ ሆሳዕና እና ከላይ ስማቸውን በጠቀስነው ስድስት ተጫዋቾች ዙርያ በመደበኛ ፍርድ ቤት የተያዘው ጉዳይ የመጨረሻው ብይን በቅርቡ እንደሚሰጥ የተጫዋቾቹ ጠበቃ አቶ ብርሀኑ በጋሻው አያይዘው ነግረውናል።