ሦስተኛው የትኩረታችን ክፍል ደግሞ አሰልጣኞችን የተመለከተ ይሆናል።
👉 አነጋጋሪው የፀጋዬ ኪዳነማርያም አስተያየት
እርግጥ አሁን ላይ የሚታዩ መሻሻሎች ቢኖሩም በሊጉ ወጣት ተጫዋቾች በቂ ዕድል ካለማግኘታቸው በስተጀርባ የሚነሳው አንደኛው ጉዳይ በሊጉ በወጣቶች ላይ ዕምነት አሳድረው ለማጫወት ድፍረት ያላቸው አሰልጣኞች ቁጥር አነስተኛ የመሆኑ ጉዳይ ነው።
አብዛኞቹ የሊጉ አሰልጣኞች በሚያስብል መልኩ የቡድናቸውን ነገ ዛሬ ላይ ከመገንባት ይልቅ ለቀጣዩ ክለብ መስፈንጠርያ የሚሆን የሚታይ ውጤት ለማምጣት በበቁ ተጫዋቾች የመጠቀም ዝንባሌ እንዳላቸው ይታመናል። ታድያ ይህ ከጊዜያዊ ውጤት ባለፈ ለቡድኖች በቀጣይነት ጠብ የሚል ነገር የሌለው “የአጭር ጊዜ እሳቤ” የተጠናወተው አሰራር በእግር ኳሳችን ገዢው ሀሳብ ሆኖ ቀጥሏል።
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በዚህ ሳምንት የሰጡት ሀሳብ ይህን የሚያጠናክር ነው ፤
በጨዋታው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ስላሳዩት ዘላለም አባቴ እና ዮናታን ኤልያስ እንቅስቃሴ ተጠይቀው ሲመልሱ እንዲህ ብለዋል።
“…….እነዚህ ተጫዋቾች ከእኛ ጋር አብረው ሲዘጋጁ ነበር የቆዩት። ግን ከልምድ አንፃር ሙሉ ኃላፊነት ሰጥተን ለማጫወት አልፈለግንም ነበር። አሁን ግን ከሞላ ጎደል የተሻለ ቦታ ላይ ስለምንገኝ በቀሪ ጨዋታም ወጣት ተጫዋቾችን ከመጠቀም የሚከለክለን ነገር የለም። ሌሎች ያልጠቀምንባቸው ልጆችን ጨምሮ በቀጣይ ከክለብ ባለፈ ለሀገርም መጥቀም የሚችሉ ጥሩ ልጆች ናቸው።”
አሰልጣኙ ገና ከውድድሩ ጅማሮ አንስቶ ካላቸው ስብስብ አንፃር በሊጉ ለመቆየት እንደሚጫወቱ በተደጋጋሚ ሲናገሩ የተደመጡ ሲሆን ከዚህ ባለፈ ስብስባቸው የተጫዋቾች ጥራት ችግር እንዳለበት ፤ በተለይ ከወገብ በላይ በሚገኙ የመጫወቻ ስፍራዎች ላይ ውስንነቶች እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩም እንዲሁ ተደምጠዋል። በሌላ ጎን ስንመለከተው እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ነባራዊ ሁኔታዎች ተስፈኛ ወጣት ተጫዋቾችን በድፍረት ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።
እርግጥ በውድድር ዘመኑ እንደነ ቢኒያም ገነቱ ፣ መልካሙ ቦጋለ እና አበባየሁ አጪሶ የመሳሰሉ በቡድኑ የቆዩ ወጣት ተጫዋቾችን በተወሰነ መልኩ ሲጠቀሙባቸው ያስተዋልን ቢሆንም ዘንድሮ ወደ ዋናው ቡድኑ ያደጉ ወጣት ተጫዋቾችንም ለመጠቀም የመጨረሻዎቹን ጥቂት ጨዋታዎች ከመጠበቅ ባለፈ ቀደም ብለው የተሻለ ዕድል ቢሰጧቸው ኖሮ ይበልጥ የሚያስመሰግናቸው ይሆን ነበር።
ተስፈኛ ተጫዋቾች ከግል ክህሎት ባለፈ ኃላፊነት ወስዶ የሚያጫውታቸው አሰልጣኝ ካገኙ እንዴት በፍጥነት ማደግ እንደሚችሉ የአቡበከር ናስር ተሞክሮ በቂ ማሳያ ነው። በመሆኑም አሰልጣኞች ተስፈኛ ተጫዋቾች ለመጠቀም ቅድመ ሁኔታ ከማስቀመጥ ተቆጥበው ይበልጥ ኃላፊነት እየወሰዱ ሊያጫውቷቸው ይገባል።
👉 አማካሪው በሜዳ ጠርዝ…
ከጥቂት ሳምንታት አስቀድሞ ሰበታ ከተማን በቴክኒክ አማካሪነት ለማገዝ የተሾሙት የቀድሞው አሰልጣኝ ደረጀ በላይ በሜዳ ላይ ቡድኑን እየመሩ እየተመለከትን እንገኛለን።
መውረዱን ያረጋገጠውን ሰበታ ከተማ ጥቂት በማይባሉ ጨዋታዎች አሰልጣኝ ብርሃኑ ደበሌ ያለ ረዳት ሲመሩ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን አማካሪ በሚል የቀድሞ የቡድኑ አሰልጣኝ ደረጀ በላይ በቴክኒክ አማካሪነት ወደ ቡድኑ መመለሳቸውን ተከትሎ አሰልጣኝ ብርሃኑ በተወሰነ መልኩ አጋዥ ያገኙ ይመስላል። ምንም እንኳን ባለፉት ጊዜያት ከደመወዝ ጋር በተያያዘ ቡድኑ ልምምድ የሰራባቸው ጊዜያት ጥቂት ቢሆኑም በጨዋታ ዕለት ግን የቴክኒክ አማካሪው አሰልጣኝ ደረጀ በላይ ቡድኑን በሜዳ ጠርዝ ሆነው ሲመሩ እየተመለከትን እንገኛለን።
ቡድኖችን ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ በማሳደግ የተካኑ እንደሆኑ ያስመሰከሩት አሰልጣኝ ደረጀ በላይ በቀጣይ የውድድር ዘመን ከሰበታ ከተማ ጋር የሚቆዩ ከሆነ ቡድኑ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ታድያ በቡድኑ ሲቀጥሉ “የቴክኒክ አማካሪ” በሚለው እና ስለ ሥራ መዘርዝር አብዝተው በሚጨነቁት ምዕራባዊያን ዘንድ እስካሁን የጠራ ግንዛቤ ባልተፈጠረበት ሚና ወይንስ አሁን እየሰሩ እንደሚገኙት በአሰልጣኝነት የሚለው ጉዳይ በራሱ ይጠበቃል።
👉 ጳውሎስ ጌታቸው ፈገግ ማስባላቸውን ቀጥለዋል
አሁን ላይ በሊጉ እያሰለጠኑ ከሚገኙ አሰልጣኞች መካከል እንደ ጳውሎስ ጌታቸው አስገራሚ እና አዝናኝ አስተያየቶችን የሚሰጥ አሰልጣኝ ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው።
በድፍረት አወዛጋቢ የሆኑ ሀሳቦችን በመስጠት የሚታወቁት አሰልጣኙ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድናቸው አዲስ አበባ ከተማ በሲዳማ ቡና ተሸንፎ በሊጉ የመቆየት ተስፋውን ዳግም ጥያቄ ውስጥ ከከተተበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ከሱፐር ስፖርት ጋር በነበራቸው ቆይታ አስገራሚ ሀሳቦችን ሲሰጡ አድምጠናል።
በቀጣይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስለሚጠብቃቸው ጨዋታ የተጠየቁት አሰልጣኙ ተከታዩን ብለዋል ፤ “እኛ የራሳችን ዕድል በራሳችን ነው የምንወስነው ስለሌላው አያገባንም። ትኩረት የምናደርገው የራሳችን ነገር ላይ ነው። ምክንያቱን ዕድሉ እጃችን ላይ እያለ ሌላው ላይ ትኩረት ማድረግ በራሱ ኃጢያት ነው። የራሳችንን ጨዋታ አሸንፈን በሊጉ ለመቆየት እንጥራለን።” በማለት ምላሻቸውን የሰጡ ሲሆን በተመሳሳይ በሲዳማ ቡና መሸነፋቸው በሊጉ የመቆየት ተስፋቸው ላይ ስለሚፈጥርባቸው ተፅዕኖ እና በመጨረሻ ጨዋታቸው ቅዱስ ጊዮርጊስን ስለመግጠማቸው ሲያስረዱ ፤ “ጠብቀነው ነው ምክንያቱም እነሱ 3ኛ ደረጃ ለማስጠበቅ እኛ ደግሞ ካለንበት ለመውጣት የሚረዳን ጨዋታ እንደመሆኑ ጠንካራ ጨዋታ ይሆናል ብለን ጠብቀን ነበር። ቀጣይም ጠንካራ ጨዋታ ቢገጥመንም እንደ አመጣጡ እንመልሰዋለን።” የሚል አስገራሚ ሀሳብ ሰጥተዋል።
👉 “ሁሉም በራሱ ላብ እና በራሱ ድካም….”
ጥቂት ዓመታትን ወደ ኋላ መለስ ብንል በመጨረዎቹ ጥቂት የጨዋታ ሳምንታት ከአቅም በታች መጫወት ፣ መላቀቅ እና ሌሎች መሰል ስሞታዎች የሚቀርብባቸው ጨዋታዎች ቁጥር ቀላል እንዳልነበር እናስታውሳለን። አሁን ላይ ግን ከዚህ አንፃር የሚታዩ እምርታዎችን እየተመለከትን እንገኛለን።
የአዳማ ከተማው ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለም ለዚህ ጉዳይ እውቅና ሰጥቷል። ከጠንካራ የሜዳ ላይ ፉክክር በኋላ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ መልስ በሰጠው አስተያየት ሁሉም ቡድኖች የአቅማቸውን ሰጥተው እየተጫወቱ በመገኘታቸው ደስተኛ መሆኑን ይገልፃል።
“…አሁንም ሰፊ ዕድል ነው ያለን ጨዋታው በጣም ያስደሰተኝ ነገር እስከ መጨረሻው ውጥረት ያለው መሆኑ ሊጉ በጣም ደማቅ ሆኗል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው ነገር የለም፡፡ ሁሉም በራሱ ላብ እና በራሱ ድካም የሚወስደው ዋንጫ ነው ፣ በራሱም ድካም ከመውረድ እና መውጣት የሚድነው በራሱ ስለሆነ ሊጉን በጣም አሳምሮታል፡፡ አሰልጣኞችም በፊት ከነበረው ሌላ ሌላ ነገሮች ተላቀው ሊጉን ያሳመረው ውድድር ነው ፣ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡”